ሔቨን ምክሩ በሪሁን(የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የ5ተኛ ዓመት የሕክምና ተማሪ)
የሳንባ ምች ምንድነው?
የሳንባ ምች በሳንባ ውስጥ የሚገኙትን የአየር ከረጢቶች በፈሳሽ ወይም መግል እንዲሞሉ የሚያደርግ የሳንባ ኢንፌክሽን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ ደም ፍሰት የሚደርስን በቂ ኦክስጅን ለመተንፈስ ከባድ ይሆናል ፡፡
የሳንባ ምች መንስኤዎች
✔️ ባክቴርያ
✔️ ቫይረስ (COVID-19 ን ጨምሮ ሌሎች ጉንፋንን የሚያስከትሉ አንዳንድ ቫይረሶች የሳንባ ምች ሊያስከትሉ ይችላሉ)
✔️ ሌላኛው የሳንባ ምች መንስኤ ደግሞ ፈንገስ ነው። (ይህ ዓይነቱ የሳንባ ምች ህመም ብዙውን ጊዜ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው ወይም በሽታ የመከላከል አቅማቸው በተዳከመ ሰዎች ላይ ይታያል፡፡)
የሳንባ ምች ተላላፊ ነው?
በቫይረስ እና በባክቴሪያ የሚከሰተው የሳንባ ምች በማስነጠስ ወይም በሳል ጊዜ ባክቴሪያው ወይም ቫይረሱ በቀላሉ ወደ አየር በመቀላቀል ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል። እንዲሁም በእነዚህ ባክቴሪያዎች ወይም ቫይረሶች ከተበከሉ ቁሶች ጋር በሚኖር ንክኪ ህመሙ ሊተላለፍ ይችላል።
የፈንገስ የሳንባ ምች ግን ከሰው ወደ ሰው አይዛመትም።
ለሳንባ ምች ህመም ተጋላጭ እነማን ናቸው?
የሳንባ ምች ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃ ይችላል፡፡ ነገር ግን በይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ሁለቱ የዕድሜ ክልሎች፦
ዕድሜያቸው 2 ዓመት ወይም ከዚያ በታች የሆኑ ህፃናት እና ዕድሜያቸው 65 ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ናቸው።ሌላው ደግሞ፦
🔹ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች
🔹እንደ አስም፣ የስኳር ህመም ወይም የልብ ህመም ያሉ ተጓዳኝ ህመም ያሉባቸው ሰዎች
🔹የተዳከመ በሽታ የመከላከል አቅም ያላቸው ሰዎች ለምሳሌ በኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ የተያዙ ፣ የካንሰር መድኃኒቶችን (ኬሞቴራፒን) የሚወስዱ፣ ወይም ከዚህ ቀደም የንቅለ ተከላ ህክምና የተደረገላቸው ሰዎች
🔹በቅርቡ እንደ ጉንፋን ያሉ የመተንፈሻ አካላት በሽታ የያዛቸው ሰዎች
🔹በቅርብ ጊዜ ወይም አሁን በሆስፒታል ውስጥ የተኙ ሰዎች በተለይም በመተንፈሻ መሳሪያ (ventilator) ላይ ከሆኑ
🔹እንደ ጭስ እና ሌሎች ሳንባን ሊጎዱ የሚችሉ ኬሚካሎች የተጋለጡ ሰዎች
🔹በስትሮክ ምክንያት ወይም በተለያዩ ምክንያቶች የመዋጥ ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች፤እንዲሁም በመድኃኒቶች፣በአልኮል መጠጦች ወይም በሌሎች አደንዛዥ ዕጾች ምክንያት ራሳቸውን የሚስቱ ሰዎች የበሉት ምግብ ወይም ምራቃቸው በአየር ቧንቧ አድርጎ ወደ ሳንባቸው በመሄድ ለሳንባ ምች ሊያጋልጣቸው ይችላል።
የሳንባ ምች ምልክቶች
የሳንባ ምች ምልክቶች እንደ የኢንፌክሽኑ መንስኤ፣ እንደ ዕድሜ እና አጠቃላይ ጤና ሁኔታ ላይ በመመርኮዝ ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ የተለመዱ ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ:
🔹አክታ ያለው ሳል
🔹ትኩሳት ፣ ላብ ወይም ብርድ ብርድ ማለት
🔹መደበኛ እንቅስቃሴዎችን በሚያደርጉበት ጊዜ ወይም በእረፍት ጊዜ እንኳን የሚከሰት የትንፋሽ እጥረት
🔹ሲተነፍሱ ወይም ሲያስሉ የሚብስ የደረት ህመም
🔹የድካም ስሜት
🔹የምግብ ፍላጎት ማጣት
🔹ማቅለሽለሽ ወይም ማስታወክ
🔹በእድሜአቸው የገፉ እና በሽታ የመከላከል አቅማቸው ደካማ የሆኑ ሰዎች ከተለመደው በታች የሆነ የሰውነት ሙቀት ሊኖራቸው ይችላል፡፡
የሳንባ ምች ምርመራ እና ህክምና
የደም ምርመራዎች፣የደረት ኤክስሬይ(Chest X-ray)፣በደም ውስጥ ያለውን የኦክስጂን መጠን መለካት፣ የአክታ ምርመራ፣ በሳንባ አካባቢ ፈሳሽ ቋጥሮ ከሆነ በመርፌ ናሙና ተወስዶ ምርመራ ይደረጋል። እንዳስፈላጊነቱ ሲቲ ስካን እና ብሮንኮስኮፒም ሊታዘዝ ይችላል።
ተገቢውን ህክምና ካገኙ የሳንባ ምች አብዛኛውን ጊዜ ሌላ ጉዳት ሳያስከትል ሊድን ይችላል ፡፡
ሕክምናው በሳንባዉ ምች ዓይነት ፣ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እና በአጠቃላይ ጤና ሁኔታ ላይ የሚመረኮዝ ይሆናል ፡፡
▪️ፀረ-ባክቴሪያዎች(አንቲባዮቲኮች) አብዛኛዎቹን በባክቴሪያ የሚመጡ የሳንባ ምች ህመምን ማከም ይችላሉ ፡፡ የታዘዘሎትን አንቲባዮቲኮች ሳይጨርሱ ቀድመው ማቆም ኢንፌክሽኑ ሙሉ በሙሉ እንዳይወገድ በማድረግ ህመሙ ተመልሶ እንዲያገረሽ እድል ይሰጠዋል። በተጨማሪም ለማከም አስቸጋሪ የሆኑ መድሀኒት የተላመዱ ባክቴሪያዎችን ሊያስከትል ይችላል።ስለዚህ ምንም እንኳን የዳኑ ቢመስሎትም መድሀኒቶን ሳይጨርሱ አያቋርጡ።
▪️የአንቲባዮቲክ መድኃኒቶች በቫይረሶች ላይ አይሰሩም ፡፡ ብዙዎቹ በቫይረስ የሚመጡ የሳንባ ምች ህመሞች ከአንድ እስከ ሶስት ሳምንታት ውስጥ በቤት ውስጥ እንክብካቤ በራሳቸው ይድናሉ ፡፡ብዙ ዕረፍትን በማግኘትና ብዙ ፈሳሾችን በመጠጣት እንዲሁም እንደአስፈላጊነቱ ህመምን እና ትኩሳትን ለማስታገስ ሀኪም እንደ ፓራሲታሞል ፣ አይቢዩፕሮፌን ወይም አስፕሪን ያሉ መድሃኒቶችን እንዲወስዱ ሊመክር ይችላል ፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች ፀረ-ቫይረስ መድሀኒቶች ሊያስፈልጉ ይችላሉ።
▪️ፀረ-ፈንገስ መድሃኒቶች የፈንገስ የሳንባ ምች ህመምን ለመዋጋት ያገለግላሉ። ኢንፌክሽኑን ለማጣራት ይህንን መድሃኒት ለብዙ ሳምንታት መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
▪️ምልክቶቹ በጣም ከባድ ከሆኑ ወይም ሌሎች ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ካሉ ሆስፒታል መተኛት አስፈላጊ ይሆናል፡፡
የሳንባ ምች ምን የከፋ ነገር ሊያስከትል ይችላል?
🔹ባክቴሪያዎች ከሳንባ ወደ ደም ፍሰት ውስጥ በመግባት ኢንፌክሽኑን ወደ ሌሎች አካላት ሊያሰራጩ ይችላሉ ፣
🔹በቂ ኦክስጅንን ለመተንፈስ መቸገር፤ በዚህ ጊዜ የመተንፈሻ ማሽንን መጠቀም ያስፈልጋል ፡፡
🔹በሳንባ ዙሪያ ፈሳሽ መከማቸት
🔹በሳንባ ውስጥ መግል መያዝ
🔹የቀደመ የጤና እክል ካለ የሳንባ ምች ሌሎቹን ህመሞች ሊያባብሳቸው ይችላል፡፡
የጤና ወግ
ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።
የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።