የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ (Antepartum hemorrhage/bleeding)
በፌበን በየነ (ጎንደር ዩ/ህ/ጤ/ሳ/ኮ የህክምና ተማሪ- C2)
Approved by: Dr. Misikir Anberbir (Gynecologist/Obstetrician)
የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ ማለት አንዲት ሴት እርግዝናዋ 28 ሳምንት ከሞላው በኋላ ልጅዋን እስክትወልድ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚያጋጥም በማህፀን በኩል የሚከሠት የደም መፍሰስ ነው።
ይህ ክስተት በእርግዝና ጊዜ ከሚታዩ አደገኛ ምልክቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን ከእርግዝና ጋር ተያይዞ ከሚመጣ ግፊት አና ኢንፌክሽን ጋር በመሆን ለእናቶች ሞት ምክንያት በመሆን ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ስለዚህም ማንኛዋም እርጉዝ ሴት የደም መፍሰስ ሲያጋጥማት ከእንግዴ ልጁ ጋር በተያያዘ እና በሌሎች ምክንያቶች ሊሆን ስለሚችል በአፋጣኝ አካባቢዋ ወደሚገኝ የጤና ተቋም እንድትሄድ ይመከራል።
የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ በማህፀን በኩል ከሚያጋጥመው የደም መፍሰስ ጋር ተያይዞ በሆድ አካባቢ ህመም እና እንደምጥ ያለ ስሜት ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን የተያያዥ ምልክቶች አለመኖር አደገኝነቱን አይቀንሰውም።
የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል ነገር ግን በዋነኝነት በሶስት እንከፍላቸዋለን ።እነርሡም :-
- የእንግዴ ልጁ ከፅንሱ ሲቀድም ወይም የእንግዴ ልጁ የማህፀኑን በር ሸፍኖ ሲገኝ (placenta previa)
- የእንግዴ ልጁ ከማህፀን ግድግዳው ሲላቀቅ (placental abruption)
- ሌሎች (ኢንፌክሽን፣ ፖሊፕ ፣ የማህፀን በር ካንሰር ፣ ወዘተ… )
ለቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ ተጋላጭ የሆኑት እነማን ናቸው?
*እድሜያቸው ከፍ ብሎ የሚያረግዙ ሴቶች (በተለይ 35 አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ)
*ከእርግዝና በፊትም ሆነ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚመጣ የደም ግፊት ያለባቸው ሴቶች
*በቅድመ ወሊድና ያለጊዜው የሚያጋጥም የእንሽርት ውሀ መፍሰስ ያጋጠማቸው ሴቶች (preterm premature rupture of membranes)
*ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች
*ከዘህ በፊት በነበሩ እርግዝናዎች ላይ የደም መፍሰስ ያጋጠማቸው ሴቶች
*ከዚህ ቀደም በኦፕሬሽን የተገላገሉ ሴቶች
*ሁለት(መንትያ) እና ከዚያ በላይ ፅንስ የተሸከሙ ሴቶች
*በእርግዝና ወቅት በሆድ አካባቢ የሚደርሱ አደጋዎች እና የመሳሰሉት…
የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ የሚያጋጥማቸው ሴቶች በተቀረው የእርግዝና ጊዜያቸው፣ በወሊድ ወቅት እና ከወሊድ በኋላ በእናትየውም ሆነ በልጁ ላይ ብዙ ችግሮች ሊያመጣ ይችላል። በፅንሱ ላይ ከሚያመጣቸው ችግሮች መካከል በማህፀን ውስጥ የፅንስ መሞት (intrauterine fetal death) እና የፅንስ እድገት መገደብ ይካተታሉ።
በእናትየው ላይ ከሚከሰቱት ችግሮች መካከል ደግሞ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ:-
*የድህረ ወሊድ የደም መፍሰስ (postpartum hemorrhage)
*ከወሊድ በኋላ የእንግዴ ልጁ ክፍል በማህፀን ውስጥ መቅረት
*ያለጊዜው የሚመጣ ምጥ እና ወሊድ
*በኦፕሬሽን የመውለድ እድልን መጨመር
*ተገቢው ሕክምና ካልተገኘ ደግሞ ማህፀኑን በቀዶ ህክምና እስከማጣት እና እስከሞትም ሊያደርስ ይችላል።
ስለዚህም እናቶች በአቅራቢያቸው በሚገኝ ጤና ጣቢያም ሆነ ሆስፒታል በመሄድ መደበኛ የሆነ የቅድመ ወሊድ ክትትል በማድረግና በተጨማሪም የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ ሲያጋጥማቸው በአፋጣኝ ህክምና በማግኘት በእነርሱም ሆነ በልጃቸው ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ችግሮች ቀድሞ መከላከል ይችላሉ።
References
- Addisu Assefa MD, Yitbarek Fantahun MD, Eyasu Mesfin MD. (July 2020). Maternal and perinatal outcome of APH at three teaching hospitals in Addis Ababa, Ethiopia. Ethiopian Journal of reproductive health. Volume 12(2),8.
- William’s obstetrics 24th edition
የጤና ወግ
ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።
የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።
https://linktr.ee/Yetena_Weg