By Bethlehem Tesfasilassie Kibrom(General Practitioner)
ቤተልሄም ተስፋስላሴ ክብሮም(ጠቅላላ ሀኪም)
Reviewed/Approved by: Dr. Dawit Alemayehu(Pediatric Orthopedician)
ከላይ የምትመለከቱት የእግር አፈጣጠር ችግር የተፈጥሮ የእግር መቆልመም ችግር (club foot) ተብሎ ይጠራል። አንድ ወይም ሁለቱም እግሮች ወደ ውስጥ እና ወደ ታች ዞረው የመወለድ ችግር ነው።
ስለየተፈጥሮ የእግር መቆልመም ችግር አንዳንድ መረጃዎችን እንመልከት።
- የተፈጥሮ የእግር መቆልመም ችግር (Clubfoot) በእግር ላይ በጣም የተለመደ የአካል ጉዳት ሲሆን ከ1000 ሕፃናት ውስጥ በአንዱ ህፃን ላይ የሚከሰት ነው ።
- በኩር ልጆች እና ወንዶች ላይ በብዛት ይታያል።
- አብዛኛውን ጊዜ ከሌሎች የጤና ችግሮች ጋር የተያያዘ አይደለም። መንስኤዉም በትክክል አይታወቅም።
- በግማሽ ያህሉ ተጎጂዎች ላይ ሁለቱም እግሮቻቸው ይህ ችግር ይታይባቸዋል። የተጎዳው እግር ከሌላው ያጠረ ሊሆንም ይችላል።
- በሽታው ወላጆቹ ባደረጉት ወይም ባላደረጉት ነገር የሚከሰት አይደለም። ስለዚህ ወላጆች ራሳቸውን መውቀስ አይገባቸውም! በተጨማሪም ተገቢው ህክምና ከተደረገ ውጤቱ ጥሩ ነው።
ይህ አይነት ትክክል ያልሆነ የእግር አፈጣጠር ችግር የሚመጣው በአብዛኛው ግዜ በጡንቻዎች ፣ ጅማቶች እና አጥንቶች ላይ በሚፈጠር ያልተለመደ እድገት ምክንያት ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ በየአመቱ 5,000 የሚገመቱ ህጻናት ይህ የእግር ችግር ይታይባቸዋል ተብሎ ይገመታል።
ለየተፈጥሮ የእግር መቆልመም ችግር አጋላጭ ይሆናሉ የሚባሉት ሁኔታዎች ምንድናቸው?
- በቤተሰብ ውስጥ ተመሳሳይ ችግር ካለ
- በእርግዝና ወቅት የሽርት ውሀ መቀነስ
- የልጁ የጀርባ አጥንት አፈጣጠር ችግር ካለ (spina bifida)
- ሌላ የአፈጣጠር ችግር ካለ
- በእርግዝና ወቅት ሲጋራ ማጨስ
ምርመራው ምን ይመስላል?
ምርመራው ህፃኑ በሚወለድበት ጊዜ በአካል ምርመራ ወይም ከመወለዱ በፊት በአልትራሳውንድ ምርመራ ወቅት ሊደረግ ይችላል።
መታከም ይችላል ወይ?
አዎን!!! ይህ ችግር በህፃናት የአጥንት እስፔሻሊስት ሀኪሞች ይታከማል። እነዚህ ሀኪሞች ሀገራችንም ውስጥ አሉ!
ሕክምናዎቹ ምንድን ናቸው?
ህክምናው ደረጃ በደረጃ የሚደረግ ሲሆን ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ዋናው ሕክምና (የ Ponseti ዘዴ ተብሎ የሚጠራው) የልጅዎን እግር በእርጋታ ወደ ተሻለ ቦታ መምራት እና መወጠርን ያካትታል። ሁሉም ለማለት በሚቻል ሁኔታ የሕክምና ዕቅዶች የሚጀምሩት በጀሶ (cast)ችግር ያለበትን እግር በማሸግ በሂደት ወደ ትክክለኛው የእግር አጥንት አቀማመጥ መመለስ ነው። ከውስጥ፣ ከኋላ እና ከታችኛው ክፍል ላይ ያሉትን አጭር እና ጥብቅ ጅማቶች በመዘርጋት እግሩ ደረጃ በደረጃ ይስተካከላል። በዚህም ምክንያት ለውጥ በአንድ ግዜ ላይታይ ይችላል። ስለሆነም ወላጆች ወይም አስታማሚዎች ተስፋ ባለመቁረጥ ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በትብብር ሊሰሩ ያስፈልጋል።
በትንሹ እስከ አምስት ዙር በጀሶ የማሸግ ህክምና ይደረጋል። ከ 2 አመት በታች ላሉ ህፃናት በዚህ ዘዴ ብቻ ችግሩ ሊስተካከል ይችላል። ህክምና ሳይደረግላቸው ቆይተው ከ 2 አመት በላይ የሆናቸው ህፃናት በጀሶ ማሸግ ብቻውን ስኬታማ ላይሆን ስለሚችል ቀዶ ጥገና ማድረግ ተገቢ ሊሆን ይችላል። (የልጅዎ እድሜ ከፍ ያለ ቢሆንም ህክምና እዳለው በመገንዘብ ወደ ህክምና ተቋማት ይምጡ!)
የእግር ማሰርያ
የልጁ እግር ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ሲስተካከል፣የእግር ማሰሪያው ደግሞ የተደረገው እርማት ቦታውን እንዳይለቅ ይጠብቃል። ያለዚህ ማሰሪያ ችግሩ እንደገና ይመለሳል። እነዚህ ማሰሪያዎች በቀን 23 ሰአታት ለሁለት ወራት ይለበሳሉ። ከዚያም በቀን 12 ሰአታት (እንቅልፍ እና ማታ) እስ
ከ መዋለ ህፃናት እድሜ ድረስ ይደረጋሉ።
የህክምና ውጤቱ እንዴት ነው?
የተፈጥሮ የእግር መቆልመም ችግር ያላቸው ልጆች ህክምና ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚቻል ሁኔታ የተሳካ ነው። አብዛኛዎቹ ልጆች በመደበኛ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ ይችላሉ፣ በተለመደው እድሜ መራመድን ይማራሉ፣ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እና ከህክምና በኋላ መደበኛ ጫማዎችን መልበስ ይችላሉ። 1 የተጎዳ እግር ብቻ ያላቸው ልጆች በትንሹ አጠር ያለ እግር ሊኖራቸው ይችላል።.
ሕክምናው መቼ ይጀመራል?
ሕክምና ብዙውን ጊዜ ልጅዎ ከተወለደ ከ 1 እስከ 2 ሳምንታት ውስጥ ይጀምራል።
በቀጣይ የሚወለደው ልጅ ላይ የመከሰት እድሉ ምን ያህል ነው?
ወላጆች ቀደም ሲል ሌላ የተፈጥሮ የእግር መቆልመም ችግር ያለው ልጅ ካላቸው ተከታይ ልጅ የመጎዳት እድሉ 10% ነው።
ተመልሶ ሊከሰት ይችላልን?
አንዳንድ ጊዜ በተለይም ህክምናውን በትክክል ካልተከታተሉ ተመልሶ ሊመጣ ይችላል። ይህ ከተከሰተ ህክምናው እንደገና መጀመር አለበት።
ባይታከምስ?
ይህ ጥያቄ ቀደም ሲል የተመለከትነው ምስል ላይ ያየነው ህፃን ባይታከምስ ብሎ እንደመጠየቅ ነው። የህፃኑ እግር ቆሞ ለመራመድ የሚያስችለው አይደለም። የእግር ማጠርን ያስከትላል። ህፃኑ ለመራመድ ቢሞክር ህመም ይኖረዋል። ረጅም ርቀት መጓዝ ያቅተዋል። ስለዚህ ይህ ልጅ ሲያድግ ለመንቀሳቀስ በሌሎች ሰዎች ወይም መርጃ መሳሪያዎች ላይ ጥገኛ መሆን ያስፈልገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ይህ ችግር ባይታከም ለሌሎች ተጨማሪ የአጥንት ህመሞች ያጋልጣል። ይህም በህይወት ጥራት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።
ክሊኒኮች ህክምና ለመስጠት ጥሩ ዝግጅት ቢያደርጉም ብዙ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን ለህክምና አያመጡም። ለዚህ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ የሚከተሉትን ናቸው።
- የተሳሳተ አመለካከት፡- እርግማን ነው ብሎ ማሰብ
- ፍርሃት፣ መገለል ይደርስብኛል ብሎ ማሰብ
- የኢኮኖሚ ጉዳይ፡- የሕክምና ወጪ እና የመጓጓዣ ወጪዎች መሸፈን አለመቻል
- ህክምና እንዳለ አለማወቅ
- የህብረተሰቡ የግንዛቤ እጥረት
- የህክምና አገልግሎት እጦት
- የህብረተሰቡ እና የቤተሰብ ድጋፍ እጦት
- ህክምናው የት እንደሚገኝ እና ስለሌሎች የጤና አገልግሎቶች ግንዛቤ ማጣት
ስለዚህ ህብረተሰቡ ትክክለኛውን መረጃ ከባለሙያዎች በመውሰድ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ሊቀርፍ ይገባል ስል ፅሁፌን አጠናቅቃለው።
አመሰግናለሁ!
የጤና ወግ
ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።
የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።
https://linktr.ee/Yetena_Weg