ዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ : የህፃናት ተላላፊ በሽታዎች ህክምና ስፔሻሊስት
መስከረም ላይ ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ልናደርግ የምንችላቸው ጥንቃቄዎች በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡
በተለይ ትምህርት ቤት ሲሄዱ የትምህርትም የምገባ ፕሮግራምም ተጠቃሚ ለሆኑ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ልጆች በጥንቃቄ ትምህርት መጀመራቸው አስገዳጅ ይሆናል፡፡
ያላየኋቸው ነጥቦች ስለሚኖሩ ውይይቱ እንዲቀጥል እጋብዛለሁ፡፡
1. የአለም የጤና ድርጅት (WHO) የማስኮች አጠቃቀም ምክር
ለህፃናት ተማሪዎች
– እድሜያቸው 5 አመት እና ከዛ በታች ለሆኑ ህፃናት ካላቸው የእድገት ደረጃ እና በአግባቡ መጠቀም ችሎታ አንፃርማስክ እንዲያደርጉ አይመከርም፡፡ ይህ ምክር የበሽታ መጋለጥ ሳይኖር ቀርቶ ሳይሆን ከተግባራዊነት አንፃር ነው፡፡
– እድሜያቸው ከ 6 – 11 አመት ለሆኑ እና ምክር ተግባራዊ ለሚያደርጉ ህፃናት፣ በተለይ ከፍተኛ ስርጭት ባለባቸውቦታዎች፣ ርቀትን ጠብቆ ለማስተማር በሚቸገሩ ማስተማርያዎች በተለይ በመንግስት ትምህርት ቤቶች፣ ተጓዳኝህመም ላለባቸው ልጆች ወይም ተመሳሳይ ተጓዳኝ ህመም ያላቸው የቤተሰብ አባላት ላሏቸው ልጆች ማስክ እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡
– እድሜያቸው 12 አመት እና ከዛ በላይ ለሆኑ ልጆች ልክ እንደ አዋቂዎች በሁሉም ጊዜያት ማስክ ማድረግ አለባቸው፡፡
2. የተማሪዎችን ቁጥር መቀነስ፣ በሚቻልባቸው አጋጣሚዎች የመማርያ ክፍሎች ወንበሮችን ማራራቅ፣ ወይ በፈረቃ (ጠዋት እና ከሰአት) ወይ ደግሞ አንድ ሙሉ ቀን ትምህርት ከዛ አንድ ሙሉ ቀን እረፍትን ተግባራዊ ማድረግ ስርጭትን ይቀንሳል፡፡
3. በትራንስፖርቶች (አውቶቡሶች፣ ታክሲዎች፣ ባቡሮች) ላይ ያለውን ተጋላጭነት ለመቀነስ (አማራጮች ባሉባቸው አጋጣሚዎች) በፊት ሩቅ ተጉዘው ትምህርት ለሚከታተሉ ህፃናት (በተለይ በአዲስ አበባ) በጊዜያዊነት ወይም በቋሚነት ቀረብ ወዳለ ትምህርት ቤት መቀየርን እንደ አማራጭ ማየት ይኖርብናል፡፡
4. ከፍተኛ ስርጭት ባለባቸው ቦታዎች በየተወሰነ ወቅት (ለምሳሌ በወር አንዴ) አቅርቦትን ባገናዘበ ለሁሉም ተማሪዎች የኮቪድ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ እድሜያቸው ከ10 አመት በታች ለሆኑ ህፃናት የህመም ምልክቶች በጣም አናሳ ስለሆኑ ሳይታወቅ አስተላላፊ እንዳይሆኑ የህመም ስሜት ኖራቸውም አልኖራቸውም በፕሮግራም መመርመር ጥሩ ነው፡፡
5. የ e-learning (online learning) ተግባራዊ ማድረግ ለሚችሉ በጣም ጥቂት ት/ቤቶች ፍቃድ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ሁኔታዎች መስተካከል የሚችል መመሪያ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ One size does NOT fit all.
6. አምስት ቁጥር ላይ ከጠቀስኩት ጋር ተያይዞ የሚወጡት ህጎች በየሳምንቱ ባለው የበሽታ ስርጭት ጋር ተያይዞ ዝቅ ሲል ላላ ያሉ መመርያዎችን ማሳለፍ ከፍ ሲል እስከ ትምህርት ማቆም ድረስ ለመወሰን ዝግጁነት ያስፈልጋል፡፡
7. ተጓዳኝ ህመሞች ያሉባቸውን አስተማሪዎች ወይም ሌሎች የት/ቤት ሰራተኞች የቢሮ ስራዎች ላይ ወይም ሌሎች አማራጮች ላይ መመደብ ያስፈልጋል፡፡
8. በቤቶቻችን የህፃናት ተንከባካቢዎቻችን እድሜቸው የገፉ (በተለይ ከ60 አመት በላይ እድሜ ያላቸው) ከሆኑ ወይም ተጓዳኝ ህመሞች ያሉባቸው የቤተሰብ አባላት ከሆኑ ተለዋጭ ተንከባካቢዎች ማግኘት ሲቻል መቀየር ስርጭትን ይቀንሳል፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት ውይይት ማስጀመርያ እንጂ ሁሉንም ሁኔታዎች የሚያገናዝቡ ነጥቦች አይደሉም፡፡
የጤና ወግ
በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።
………………………………………………………………………………………………………………………..
ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።
በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።
የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።
በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣ በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ