ከ ጤና ወግ

የኮሮና ቫይረስ ወደ ሃገራችን ከገባ ጀምሮ መንግስት፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ህዝብና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቫይረሱን ለመከላልከል የተለያዩ እቅዶች አውጥተው በመተግበር ላይ ይገኛሉ። እስካሁንም ሊበረታቱ የሚገባቸው በጎ እርምጃዎች እየተከናወኑ ነው። በጥቂቱ ለመግለጽ ያህል 

  1. የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ያወጣው ከውጭ ሃገር የሚገቡ መንገደኞች ላይ እየተተገበረ ያለው የ14 ቀን የለይቶ ማቆያ ውሳኔ (quarantine measure) ቫይረሱ እንዳይስፋፋ የራሱን አስተዋጾ አድርጓል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ከሚያወጣቸው እለታዊ የኮሮናቫይረስ የላብራቶሪ ውጤቶች እንደታየው ለይቶ ማቆያው ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች ወደ ማህበረሰቡ ሳይቀላቀሉ በፊት በመለየት ቫይረሱ በመገደኞቹ አማካኝነት የመተላለፍና የመስፋፋት እድል እንዳይኖረው አድርጓል። 
  2. የኢትዮ ተሌኮም በአገልግሎቶቹ ላይ ያደረገው የዋጋ ቅናሽ ሌላው የሚመሰገን ውሳኔ ነው። ይህ እርምጃ በተለይ ማህበረሰቡ አካላዊ መራራቅን እየተገበረ ባለበት በዚህ ጊዜ ትልቅ ጥቅም አለው፤ የተደረገው ቅናሽ ቤተሰብ ከወዳጅ ዘመድ ጋር በአካል ሳይገናኝ በመጠነኛ ዋጋ በስልክ መነጋገር ይችላል። ይህም በአካል መራራቅ ሊያደርስ የሚችለውን ማህበረሰባዊ ጫና ይቀንሰዋል።
  3. የሃይማኖት ተቋማት ምእመኑን በቤት እንዲቆይና ከቤት እንዲጽልይ መፍቀዳቸው በጣም ጥሩ ውሳኔ ነው። የብሮድካስቲንግ ሃላፊዎች ሃይማኖታዊ ስርጭቶቹ በቴሌቪዥን እንዲተላለፍ ማድረጋቸው ለሚልዮኖች በጣም ጠቃሚ ሆኗል። ከሃይማኖታዊ ጠቀሜታው ባለፈ በሃይማኖት መምህራን የሚሰጠው ትምህርት ህዝቡን በማረጋጋትና ይህን አስቸጋሪ ጊዜ በተሻለ መንፈሳዊ ሰላም እንዲሰማቸው ትልቅ አስተዋጾ ያደርጋል። 
  4.  በመንግስት በኩል የተጀመረው የተቸገሩትን መርዳት እንዲሁም ባለሃብቶች በዚህ ጉዳይ ከመንግስት ጋር በተለያዩ ሁኔታዎች በቅንጅት መስራታቸው በጣም የሚመሰገን ነው። 

እነዚህና ሌሎች ያልጠቀስናቸው እርምጃዎች በእጅጉ ሊበረታቱ እና ሊመሰገኑ ይገባል፤ ከምንም በላይ ይህንን ወረርሽኝ ልንታደገው የምንችለው የተለያዩ አካላት ከጤና ጥበቃ ጋር በቅንጅት ሲሰሩ ነው። አሁንም ተመሳሳይ ተግባሮች በተለያዩ ዘርፎች እንዲቀጥሉ እንጠይቃለን። 

ለዛሬው በአልን ምክንያት በማድረግ አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል የምንለው መሰረታዊ ጥንቃቄዎች በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥሉ ነው። አመት በአል በባህሪው አካለዊ መራራቅን በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል፤ ነገር ግን ያለንበትን አሳሳቢ ሁኔታ በመረዳት ህዝቡ የበለጠ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እንመክራለን። በለተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ቫይረሱ በሃይማኖታዊ ስብሶች በቀላሉ ተስፋፍቷል። ለምሳሌ በአሜሪካን ሃገር የቤተክርስቲያን ፓስተር ፕሮርግራሙን ለመሰረዝ ባለመፈለጉ በቫይረሱ ሞቷል። ከዚህም የባሰው በፈረንሳይ አንድ ቤተክርስትያን ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ክርስትያኖች የተካፈሉበት ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ በነበረ አንድ ቫይረሱ ያለበት ሰው የተቀሩትን የፕሮግራሙ አባላት ቫይረሱን አስተላልፏል፤ በዚህም ሳይበቃ እዛ የነበሩት አባላት ቫይረሱን ወደ ተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል አስተላልፈው ባጠቃላይ 2500 የሚሆኑ ሰዎች ኮሮና ቫይረስ ሊይዛቸው ችሏል።  

በተመሳሳይ በህንድ አንድህራ ፕራዴሽ በሚባል ክልል ውስጥ በነበረ የእስልምና ሃይማኖታዊ ስነስርአት ጋር በተያያዘ የተከሰተውን የቫይረሱን መስፋፋት ለማስቆም ከስነስርአቱ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች በመፈለግ መንግስት እስካሁን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከተለያየ ቦታ ሰብስቧል። ከተማው ወደ 50 ሚልዮን ሰዎች የሚኖሩበትና የተጨናነቀ ከተማ ነው፤ ይሄም ቫይረሱን ለማስፋፋት ያለውን አስተዋጽኦ መረዳት ቀላል ነው። የተለያዩ ስብስቦች (clusters) ቫይረሱን በቀላሉ ሲያስፋፉ ታይቷል። ስብስቦቹ ከቤተሰብ እስከ ሃይማኖታዊና የተለያዩ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ስብሰባዎች፣ የልደት፡ የሰርግና የለቅሶ ስብሰባዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የቫይረሱ ስርጭት እንደየስብሰባው የቁጥር ብዛት ይወሰናል። በህንድ የታየው ሃገሪቱ ቫይረሱ ከተሰራጨባቸው ስብስቦች ከፍተኛው ነው።  እንዲሁም በቺካጎ የቀብር የልደትና የቤተክርስትያን ስነስርአቶች ምክንያት ቫይረሱ ወደተለያዩ ሰዎች ተላልፏል፤ አንድ ቫይረሱ ያለበት ሰው ወደ ለቅሶ ቤት በመሄዱ ምክንያት ከአንድ ሰው ወደሌላኛው እየተላለፈ ባጠቃላይ 16 ሰዎች ትይዘው ሶስቱ ሞተዋል። 

ከነዚህ ምሳሌዎች ሃገራችን ትምህርት መውሰድ አለባት፤ የሃይማኖት ስነስራቶች፣ የልደት፡ የሰርግ፡ የለቅሶና ማናቸውም አይነት ስብስቦች እንዲሁም የበአል ቤተሰብ ጥየቃ በዚህ ሰአት መታሰብ በፍጹም የለበትም። የቫይረሱ ስርጭት በእንደዚህ አይነት ዝግጅቶች በቀላሉ ሊፈነዳ እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል፤ ይህም ከሃገራችን ኢኮኖሚያዊና ነበራዊ ሁኔታ አንጻር የማንወጣው ከባድ አደጋ ውስጥ እንደሚከተን መረዳት አለብን፤ የበአል ግብይት ከተቻለ ማስቀረት ቢቻል ወይም መጨናነቅ በሌለባቸው ቦታዎችና ሰአታት በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ማስኮችን በማድረግ ሊሆን ይገባል። 

በዚህ በአል በተለይ እድሜያቸው የገፋ ሰዎችን ከቤት ባለማስወጣትና ምንም አይነት ቤተሰባዊና በአላዊ ጉብኝት ባለማድረግ የወላጆችን ጤና መጠበቅ አለብን። ለሃገር የሚከፈል መስዋእትነት በጦር ሜዳ ብቻ አይደለም፤ ጤናችንን በመጠበቅና በዛውም የቤተሰባችንን ጤና በማስጠበቅ በፈረንሳይ በህንድና በአሜሪካ የታየው እኛም ሃገር እንዳይደገም በማድረግ ለሃገር ተቆርቋሪነታችንን እናሳይ። ሃገራችንና ህዝባችን የማይወጡት አደጋ መስፋፊያ መንገድ አንሁን። የህክምና ባለሞያዎች እያደረጉ ያለውን ህይወታቸውን መስዋእት እስከማድረግ የሚያደርስ መስዋእትነት በዜሮ አናባዛው። የምንችለውን እና ከዛም በላይ እንሞክር። ምንም ተጨማሪ መስዋእትነት ሳንከፍል በሽታውን ሊያስፋፉ ከሚያስችሉ ማናቸውም ድርጊቶች በመቆጠብና አካላዊ መራራቅን በመተግበር ጀግንነታችንን እናሳይ። 

መንግስት ይህንን የበአል ጊዜ በተለየ ሁኔታ ተመልክቶ ከህዝብ ጋር በመተባበር በከተማም ሆነ በገጠር በተለያዩ ቦታዎች መሰረታዊ ጥንቃቄዎች መተግበራቸውን እንዲያረጋግጥ እንመክራለን። ከላይ የተጠቀሱት ሃገሮች ላይ ከተከሰተው እኛ በማስተዋል ትምህርት መውሰድ አለብን፤ ችግሩ እኛ ላይ እስኪመጣ መጠበቅ የለብንም።  መንግስት ይሄን ለማስፈጸም የተለያዩ ድርሻ አካላትን በማስተባበር አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያረግ እናምናለን። 

የጤና ወግ

በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።  

………………………………………………………………………………………………………………………..

ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።

በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።

የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።

በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣  በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ 

Share this: