በዶ/ር ትዕግስት ስለሺ (የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት እና የልብ ሰብ ስፔሻሊቲ ፌሎው)
የሪውማቲክ የልብ ህመም በአለም ላይ እስከ 30 ሚሊዮን በሚጠጉ ሰዎች አብዛኞቹም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ባሉ ሃገራት ይገኛል ። ከእነዚህም መካከል በአመት ዉስጥ ወደ 275,000 ሰዎችን ለሞት ይዳርጋል።
በአብዛኛው ከ 5 እስከ 15 አመት የእድሜ ክልል ዉስጥ ያሉ ህፃናት እና ታዳጊዎችን የሚያጠቃ ሲሆን ከፆታ አንፃር ሴቶችን የበለጠ ለጉዳት ይዳርጋል።
ሃገራችን ከአለም ከፍተኛ የሆነ የሪዉማቲክ የልብ በሽታ መስፋፋት ካለባችዉ ሃገራት መካከል ተጠቃሽ ናት። ከ 1000 ህፃናት እና ወጣቶች ዉስጥ ከ 14-38 ያህሉ ይህ ህመም እንዳለባችው ጥናቶች ያመላክታሉ። ይህም ከአለም ከፍተኛ የሚባል ቁጥር ነዉ።
ህመሙ እንዴት ይከሰታል?
የሪዉማቲክ የልብ በሽታ በአግባቡ ካልታከመ በባክቴሪያ ከሚመጣ የቶንሲል ህመም ጋር ተያይዞ የሚከሰት መሆኑን ጥናቶች አረጋግጠዋል። ይህም ሰውነትን ከህመም የሚከላከሉ ሴሎች ኢንፌክሽኑን ለማጥፋት በሚያደርጉት ጥረት ከባክቴሪያዎች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸዉን የሰውነት ክፍሎች ( ለምሳሌ ቫልቭ፣ የልብ ጡንቻዎች፣ የልብ ሽፋን ፣ መገጣጠሚያና ቆዳችን) ላይ ጉዳት ያደርሳሉ። ይህም የመጀመሪያ ደረጃ ጉዳት ሲሆን አጣዳፊ ሪዉማቲክ የልብ በሽታ (Acute rheumatic fever) ይባላል።
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
በታካሚዉ ላይ የመገጣጠሚያ እብጠት እና ህመም፣ የቆዳ ሽፍታ፣ የልብ ድካም፣ አግባብ ያልሆነ የሰውነት እና የእጅ እንቅስቃሴ የመሳሰሉ ምልክቶች ይታያሉ። ይህም ህመም የቶንሲል ኢንፌክሽኑ ከዳነ ከሳምንታት በኃላ የሚመጣ ነዉ። በአግባቡ ካልታከመ እና ተመሳሳይ ኢንፌክሽን ከተደጋገመ ስር የሰደደ የሪዉማቲክ የልብ በሽታ( Chronic rheumatic valvular heart disease) የሚባለዉ ህመም ይከሰታል።
ስር የሰደደ ሲባል በልብ ዉስጥ ያሉት በሮች ( ቫልቭ) ላይ ጠባሳ በመፍጠር እንዲድሩ እና በአግባቡ እንዳይንቀሳቀሱ ያደርጋል። የቫልቮች በአግባቡ አለመስራት የደም መርጋት፣ የልብ ምት መዛባት እና የልብ ድካም ያስከትላል። ታካሚዉ ላይ ከሚታዩ ምልክቶች መካከል ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት፣ የትንፋሽ መቆራረጥ ፣ የሰውነት እብጠት፣ ፈጣን የሆነ የልብ ምት መሰማት እና ሳል ይጠቀሳሉ።
ህመሙን እንዴት እንከላከለው?
ይህንን ህመም በቀላሉ መከላከል ይቻላል። የመጀመሪያዉ የመከላከያ ደረጃ የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመቀነስ ህፃናት የሚኖሩባቸውንም ሆነ የሚማሩባቸውን ክፍሎች ያልተፋፈጉ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ለዚህም ትምህርት ቤቶች ትልቁን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል።
የቶንሲል ህመም ሲከሰት በአግባቡ ማሳከም የሚያስፈልግ ሲሆን ይህም የልብ ቫልቭ (በር) ጉዳትን ያስቀራል። ይህም ሳይሆን ቀርቶ ታካሚዉ የልብ ቫልቭ ጉዳት ቢገጥመዉ ወደ ስር የሰደደ የልብ ህመም እንዳይሸጋገር በሃኪም የሚታዘዙ መደሃኒቶችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል።
የሪውማቲክ የልብ በሽታ እስከ 70 ከመቶ የሚሆኑ ያልታከሙ ታማሚዎችን ለሞት ስለሚዳርግ ማንኛዉም የጉሮሮ ህመም፣ ትኩሳት ፣ የመገጣጠሚያ እብጠት እና ህመም ፣ የቆዳ ሽፍታ ሲኖር ሃኪም ማማከር እና ተገቢዉን ህክምና ማግኘት አስፈላጊ ነዉ። የጫናውን ያህል ትኩረት ያላገኘው የሪውማቲክ የልብ በሽታ የታዳጊ ህፃናትና ወጣቶችን ህይወት በስቃይ የተሞላ ከማድረጉም ባሻገር ለህልፈት የሚዳረገው ቁጥርም የትየለሌ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡት ይገባል።