በዶ/ር ተስፋዬ ብርሃኑ(ጠቅላላ ሐኪም- ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መምህር)
Edited by Dr.Mahlet final year resident at SPHMMC
መግቢያ
የአልዛይመር በሽታ ከ60-70% የሚሆነውን ዲመንሺያ በተለምዶ
“የመርሳት ችግርን” የሚያመጣ የተግባረ-አንጎል(Neurocognitive) የጤና እክል ዓይነት ነው። የዲመንሺያ በሽታ የማስታወስ፣ የማሰብ እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን የመፈፀም ችሎታን የሚያስተጓጉሉ የአንጎል ጤና እክሎች የወል መጠሪያ ስም ነው። ኩላሊት፣ ጉበት፣ እና ልብ ተፈጥሮአዊ የሕይወት ዑደት እንዲቀጥል ተግባራቸውን ማከናወን ሳይችሉ ቀርተው የመጨረሻ ደረጃ ሕመም ሲከሰት ኩላሊት፣ ጉበት፣ ወይም ልብ ድካም ተከሰተ
እንደምንለው ሁሉ አንጎላችንም በመደበኛው ጊዜ ሲያከናውናቸው የነበሩትን ተግባራት ለምሳሌ ከውስጥም ከውጭ ካሉ የስሜት ሕዋሳት የደረሱትን መልእክቶች ተቀብሎ አናቦና አገናዝቦ ትርጉም ሰጥቶ ግብረመልስ ሳይሰጥ ሲቀር ወይም ከነበረው ትውስታ ጋር አሰናስሎና አቆራኝቶ ምላሽ መስጠት ሳይችል ሲቀር እና አለመስራቱ በዘላቂነት ችግር እየፈጠረ ሄዶ በኑሯችን እንዲሁም በማኅበራዊ እንቅስቃሴያችን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሲያስከትል የአንጎል ድካም(Brain failure) ተከሰተ እንላለን ይህንንም ኹነት ዲመንሺያ በሚል የወል ስያሜ እንጠራዋለን። ማገናዘብ(Cognition) ማለት በአስተሳሰብ፣ በተሞክሮ እንዲሁም በስሜት ህዋሳት፣ እውቀትን እና መረዳትን የማግኘት
የአዕምሮ ሂደት ነው።
የአልዛይመር በሽታ ምንድነው?
የአልዛይመር በሽታ ዋነኛ የዲመንሺያ መንስኤ ሲሆን የማስታወስ፣ የመማር እንዲሁም የማገናዘብ (Cognitive)
የአንጎል ተግባራትን በማስተጓጎል የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴንና ማኅበራዊ መስተጋብር የሚጎዳ
የነርቭ ሕዋሳት የጤና እክል ሲሆን በአንጎል ውስጥ አሚሎይድ እና ታው የሚባሉ የፕሮቲን ጥምዞች ክምችት ጋር የተያያዘ ነው።
የአልዛይመር ሕመም እንዴት ይከሰታል?
የነርቭ ሕዋሳትን ደግፎ እና አረጋግቶ ተግባራቸውን እንዲከውኑ የሚያስችላቸው መዋቅራቸው እንዲጸና የሚያግዙ ጥቃቅን ቦይ መሰል ውቅሮች አሉ። እነዚህን ውቅሮች ደግሞ የሚደግፉ እና የሚያረጋጉ ታው የሚባሉ ጥምዝ ፕሮቲኖች አሉ። በአላዛይመር ጊዜ ታው የሚባሉት ፕሮቲኖች በኬሚካላዊ ሂደት ተግባራቸውን ሳያከናውኑ ሲቀሩ የነርቭ ሕዋሳት መዋቅር ይላላሉ ከዚያም
ሊበታተኑ ይችላሉ። በተጨማሪም ታው የተሰኙ ጥምዝ ፕሮቲኖች በኬሚካላዊ አጸግብሮት ሳይወገዱ ቀርተው በነርቭ ሕዋሳት
መካከል በብዛት ሊከማቹ ይችላሉ። ይህም በነርቭ እና በነርቭ መካከል የሚደረጉ መልእክት ልውውጦች እንዲስተጓጎል ያደርጋል።
በጥቅሉ የአልዛይመር በሽታ የነርቭ ሕዋሳትን ጤናማ የሚያደርጉ 3 ሂደቶችን ማለትም ተግባቦት፣ አጸግብሮታዊ ኹነት እና ጥገናን ያስተጓጉላል። በዚህም ምክንያት በአንጎል ውስጥ ያሉ አንዳንድ የነርቭ ሕዋሳት ሥራቸውን ያቆማሉ፣ ከሌሎች የነርቭ ሕዋሳት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያጣሉ፤ በመጨረሻም ይሞታሉ። የእነዚህ የነርቭ ሕዋሳት ጥፋት እና ሞት የማስታወስ ችሎታን ማጣት፣ የስብዕና ለውጦች መከሰት፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን በማካሄድ ላይ ችግሮች እና ሌሎች የበሽታውን ገፅታዎች ያስከትላል።
የአላዛይመር በሽታ የሥርጭትና ክስተት መጠን
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ55 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የዲመንሺያ በሽታ ሲኖርባቸው ከ60% በላይ የሚሆኑት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ ይኖራሉ። በየዓመቱ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ አዳዲስ የዲመንሺያ ሕሙማኖች አሉ።
ዲመንሺያ እና አልዛይመር በሽታ በዓለም ደረጃ 7ኛ የሞት መንስኤ ሆኖ ሲቀመጥ በኢትዮጵያ ደግሞ 21ኛ ደረጃን ይዟል። በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአረጋውያን ዘንድ ለሚከሰቱት የአካል ጉዳት እና ጥገኝነት ችግሮች ዋነኛ መንስኤ ነው።
ለአልዛይመር በሽታ የሚያጋልጡን ነገሮች ምንድን ናቸው?
- እድሜ ከ65 ዓመት በላይ መሆን፦ የመርሳት በሽታ ከእርጅና ጋር እየጨመረ ይሄዳል። በኢትዮጵያ ባለፉት 3 አስርት አመታት ውስጥ የእድሜ ጣሪያ ከ45 ወደ 4 አመት ከፍ ያለ ሲሆን እስከ ምእተ አመት አጋማሽ ድረስ 74 አመት ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም የዲመንሺያን የስርጭት እና ክስተት መጠን
ሊጨመረው እንደሚችል ይገመታል። (እስከ 9% የሚሆኑት የዲመንሺያ ተጠቂዎች እድሜያቸው ከ65 በታች በመሆኑ በሁሉም ዕድሜ ክልል ያለ ሰው በዲመንሺያ ሊጠቃ እንደሚችል ልብ ይሏል።)
- የዘረ መል ተጋላጭነት
- ስኳር፣ ደም ግፊት፣ የደም ቧንቧና የልብ በሽታዎች
- ከልክ ያለፈ አልኮል ተጠቃሚነት
- ሲጋራ ማጨስ
- የጭንቅላት ጉዳት (በአደጋ ምክንያት)
የአልዛይመር በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
፭ቱ “አ“ዎች ከአልዛይመር በሽታ ጋር ተያይዘው የሚታዩ ምልክቶችን በቀላሉ ያስታውሱናል።
አለማስታወስ(Amnesia)፣ የቅርብ ጊዜ ክስተቶችን ለማስታወስ ስለሚቸገሩ በዝርዝሮች ወይም በቀን መቁጠሪያ ላይ የበለጠ ይተማመናሉ። በሽታው እየቆየና
እየባሰ ሲሄድ ትዝታዎችን ወደ ንቃተ-ህሊና(Consciousness) ለማምጣት ይቸገራሉ።
አለመጥራት(Anomia)፦ ለቋንቋ አጠቃቀም እና ተግባቦት አስፈላጊ የሆኑትን ቃላት፣ ጽንሰ-ሀሳቦች ወይም ቁጥሮች የማስታወስ ችሎታን የሚያግዝ የረጅም ጊዜ ማህደረ ትውስታ(Long term memory) ሲታጎል ይከሰታል። ታካሚዎች የለመዷቸውን የምግብ፣ የእቃ፣ ወይም የሌሎች
ነገሮችን ስም በቀጥታ ለመጥራት ይቸገራሉ።
አለመግባባት(Aphasia)፦ የንግግር ቋንቋን ወይም ንግግርን የመረዳት፣ የማንበብ እና የመጻፍ ችሎታን ማጣት ያመለክታል። ታካሚዎች የተረዱትን ለመናገር ለመጻፍ እንዲሁም የሚነገራቸውን ሆነ የተጻፈውን ለመረዳት ይቸገራሉ። በጥቅሉ ተግባቦታቸው ይጎዳል።
አለመተግበር(Apraxia)፦ አንድ ሰው ይህን አድርግ ሲባል ትዕዛዙን ተረድቶ እና ለመፈጸም ፍቃደኛ ሆኖ እንዲሁም ጡንቻዎቹ ጤናማ ሆነው ግን ተግባራትን ወይም እንቅስቃሴዎችን ማከናወን አለመቻልን ያመለክታል። ለምሳሌ ጠጉር ለማበጠር መቸገር
አለመለየት(Agnosia)፦ ምንም እንኳን የስሜት ህዋሳቶች በመደበኛነት የሚሰሩ ቢሆኑም የዲመንሺያ ሕሙማን ዕቃዎችን፣ ሰዎችን፣ ድምጾችንና ሽታዎችን ለመለየት አስቸጋሪ ወይም የማይቻል ሆኖ ያገኙታል። ለምሳሌ ዓይናችንን ጨፍነን ቁልፍ መዳፋችን ላይ ቢደረግ ቁልፍ መሆኑን እናውቃለን ዲመንሺያ ያለባቸው ግን ለመለየት ይቸገራሉ። እንዲሁ በዕይታም ነገሮችን ለመለየት ይቸገራሉ። ልክ እኛ
ከጎን ያለውን ስዕል ምን እንደሆነ ለይተን ለማወቅ እንደተቸገርነው ሁሉ።
የአልዛይመር በሽታ ምርመራ
አንድ ታካሚ የዲመንሺያ እንዲሁም የአልዛይመር በሽታ አለበት ወይስ የለበትም የሚለውን ለማወቅ የአእምሮ ጤና እክሎች ምርመራ እና ስታትስቲክስ መመሪያ 5ኛ ዕትም(DSM-5) ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን በዋናነት
እንጠቀማለን። ዲ.ኤስ.ኤም-5 እነዚህን የማገናዘብ(Cognitive) ተግባራት ማሽቆልቆል እና የመማር/የማስታወስ እክልን የአልዛይመር በሽታ ዋና መገለጫዎች አድርጎ በመስፈርቱ ላይ አስቀምጧቸዋል።
የአእምሮ ጤና እክሎች ምርመራ እና ስታትስቲክስ መመሪያ 5ኛ ዕትም(DSM-5) መስፈርቶች |
⮚ ምልክቶች
⮚ የማስታወስ/የመማር ማሽቆልቆል እና ከሌሎቹ የማገናዘብ(Cognitive) ጎራዎች መካከል አንዱ ከቀነሰ • ትኩረት/Attention • ከዋኔያዊ ክህሎት/Executive function • መማር/ማስታወስ/Learning/Memory • ቋንቋ/Language • አስተውሎታዊ እንቅስቃሴ/Perceptual–motor • ማኅበራዊ ግንዛቤ/Social cognition |
⮚ በዘላቂነት ችግር እየፈጠረ ሄዶ በኑሮ እንዲሁም በማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሲያስከትል |
⮚ ልብ ይበሉ፦ የአእምሮ ጤና እክል የተከሰተው በአልዛይመር በሽታ ምክንያት ነው ብሎ
ከመደምደም በፊት ሌሎች የአእምሮ ጤና እክሎች እና ጊዜያዊ የአእምሮ ጤና መታወክ(Delirium) መለየት ይገባል። |
የአልዛይመር በሽታ ደረጃዎችን የሚጠቁሙ መገለጫዎች
መጠነኛ(Mild)፦ በመሳሪያ የታገዙ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ መቸገር ለምሳሌ ሂሳብ መክፈል፣ ምግብ ማዘጋጀት፣ ቤት ማስተካከል፣ መገብየት፣ መጓጓዝ፣
መለስተኛ(Moderate)፦ መሠረታዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ መቸገር ለምሳሌ መመገብ፣ መልበስ፣ መጸዳዳት፣ መንቀሳቀስ፣ ንጽሕና መጠበቅ
ከፍተኛ(Severe)፦ በሁሉም የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴዎች ላይ ደካማ መሆን፤ ሙሉ በሙሉ በሌሎች ሰዎች ላይ ጥገኛ መሆን። ለተለያዩ ተጓዳኝ በሽታዎች በተለይ ለሳንባ ምች፣ ለሽንት ቦይ ኢንፌክሽንና ለሌሎችም ተጋላጭ በመሆን ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ።
የአልዛይመር ሕመም አብዛኛውን ጊዜ ሂፖካምፐስ(Hippocampus) የተባለውን በቅርብ የተከሰቱ ኹነቶችን ለማስታወስ የሚረዳ መሃከለኛ የአንጎል ክፍል በመጉዳት ይጀመርና ቀስ በቀስ ከጎኑ ወዳሉት
የአንጎል ክፍሎች (Temporal and parietal lobes) ይሰራጫል። ከዛም የፊተኛውን(Frontal lobe) ጎድቶ ወደ ኋለኛው የአንጎል ክፍል(Occipital lobe) በመሠራጨት ተግባረ-አንጎልን ያስተጓጉላል። ለዚህም ነው ምልክቶች ቀስ በቀስ በዓይነት እየጨመሩና እየባሱ የሚሄዱት።
የሕክምና አማራጮቹ ምንድናቸው?
ለአልዛይመር ሕመም ምልክቶቹን ለመቀነስ ከሚታዘዙ መድኃኒቶች በስተቀር ይህ ነው የሚባል ፈዋሽ መድኃኒት እስካሁን አልተገኘም። ነገር ግን ከበሽታው ጋር የሚኖሩትን እና የሚንከባከቧቸውን ሰዎች ለመርዳት ብዙ ማድረግ
ይቻላል። የአልዛይመር ሕመም ያለባቸው ሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ለማከናወን እና ደኅንነታቸውን ለማሻሻል በሚከተለው መንገድ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ።
- በአካል ንቁ ይሁኑ።
- ጤናማ ይመገቡ።
- ማጨስን እና አልኮል መጠጣትን ያቁሙ።
- ከሐኪምዎ ጋር መደበኛ ምርመራ ያድርጉ።
- አስፈላጊ ነገሮችን ለማስታወስ እንዲረዳዎ የእለት ተእለት ስራዎችን እና ቀጠሮዎችን ይፃፉ።
- በትርፍ ጊዜዎ የሚወዷቸውን ነገሮች ያድርጉ።
- አእምሮዎን ንቁ ለማድረግ አዳዲስ መንገዶችን ይሞክሩ።
- ከጓደኞች እና ቤተሰብ ጋር ጊዜ ያሳልፉ እና በማኅበራዊ ህይወት ውስጥ ይሳተፉ።
- በጊዜ ሂደት፣ ለራስዎ ወይም ለገንዘብዎ ጠቃሚ ውሳኔዎችን ማድረግ ከባድ ሊሆን ስለሚችል አስቀድመው ያቅዱ።
- ውሳኔዎችን በሚያደርጉበት ጊዜ እርስዎን ለመደገፍ የሚያምኗቸውን ሰዎች ይለዩ።
- ለእንክብካቤ እና ድጋፍ ምርጫዎችዎ እና ምርጫዎችዎ ምን እንደሆኑ ለሰዎች ለመንገር ቅድመ እቅድ ይፍጠሩ።
- ከቤት ሲወጡ አድራሻዎትንና የአደጋ ጊዜ ተጠሪዎን የሚገልጽ መታወቂያ ይዘው ይምጡ።
- ለእርዳታ ቤተሰብ እና ጓደኞችን ያግኙ።
- እርስዎን እንዴት ሊረዱዎት እንደሚችሉ ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር ይነጋገሩ።
- የአካባቢ ድጋፍ ክበቦችን ይቀላቀሉ።
ዋቢዎች
- Uptodate 2023
- World health organization websites
- Harrison principles of internal medicine 21st Edition
https://www.worldlifeexpectancy.com/country-health-profile/ethiopia