በዶ/ር ናታን ሙሉብርሃን (የድንገተኛ እና ፅኑ ህክምና ስፔሻሊስት)

የክረምቱን መግባት ተከትሎ ሊባባሱ ከሚችሉ የመተንፈሻ አካላት ህመም አንዱ አስም ነው። አስም የታችኛው የአየር ቱቦን የሚያጠቃ ህመም ሲሆን በተራዘመ የጊዜ ሂደት (chronic) የአየር ቱቦ መቆጣት ሳቢያ የሚከሰት ነው። በአለማችን ላይ 300 ሚሊዮን ሰዎች የአስም ህመም ታማሚ ሲሆኑ በአጣዳፊ የአስም ህመም ምክንያት እጅግ ብዙ ሰዎች በየአመቱ ድንገተኛ ክፍል ለህክምና ይሄዳሉ። የአስም መባባስ  በድንገት የሚመጣ ህመምና በታችኛው የአየር መተላለፊያ ቱቦ ውስጥ የሚገኙ ጡንቻዎች በድንገት ሲኮማተሩና የአየር ቱቦ ሲጠብ የሚከሰት ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ የአየር ቱቦ ልባስ መቆጣትና ማበጥ እንዲሁም በአየር ቱቦ ውስጥ የንፍጥ መሳይ ፈሳሽ (አክታ) በብዛት መመንጨትና መጠራቀም ተያይዘው ይከሰታሉ። የአስም መባባስ በኢንፌክሽን፣ አለርጂ፣ በቅዝቃዜ፣ በመድሃኒቶች፣  በቃር፣ በሲጋራ ጭስ…ወዘተ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል።

የአስም መባባስ ታማሚው እንደሚያሳየው ምልክቶችና የደም ኦክስጅን መጠን ቀላል፣ መካከለኛ፣ ከፍተኛ እና ለህይወት አስጊ ደረጃ ብለን እንመድበዋለን።

የተባባሰ አስም ምልክቶች 

    . ለመተንፈስ መቸገር፤ 

    . በቂ አየር እያገኙ እንዳልሆነ መሰማት፤ 

    . ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፤

    . በኃይል መሳል ( አክታ ሊኖረው ይችላል)

    . አየር ሲያስወጡ እንደ ፉጨት ያለ ወይም ሲር ሲር የሚል ድምጽ፤

    . የደረት አካባቢ ህመም፤

    .በጣም የተባባሰ ከሆነ ትንፋሽ መቆራረጥ፤

 

የተባባሰ አስም የመጀመሪያ እርዳታ 

    . ታማሚውን ያረጋጉት፤ 

    . ታማሚው በሚፈልገው  አኳሃን እንዲቀመጥ ያድርጉ፤

    . መስኮትና በር በመክፈት ንጹህ አየር እንዲያገኙ ያድርጉ፤ 

    . የሚነፋ የአስም መድሃኒት የሚጠቀሙ ከሆነ እርሱን እንዲወስዱ ያግዙዋቸው፤

    . ወደ አንቡላንስ በመደወል፣ እርዳታን ይጥሩ፤

    . የአስም በሽታ የተባባሰበትን ሰው ወደ ህክምና ተቋም እንዲሄድ ያድርጉ፤

    . መተንፈስ ካቆመ እስትንፋስ መስጠት ይጀምሩ

የተባባሰ አስም ህክምና

    . ወደ ህክምና ተቋም ሲደርሱ የተለያዩ የደም ምርመራ፣ የሳንባ የስራ አቅም ምርመራ፣ ራጅ…እንደ አስፈላጊነቱ ይታዘዛል።

    . የተለያዩ መድሃኒቶችን እንደ  ኦክስጅን፣ የአየር ቱቦ ጡንቻዎች እንዲከፈቱ የሚያግዙ የሚነፉ መድሀኒቶች፣ ሲቴሪዮድ (steroid)፣ እንደ አስፈላጊነቱም የኢንፌክሽን ማከሚያ መድሀኒቶች..ከሐኪም ምርመራ በኃላ ይታዘዛ

    . እንደ አስሙ ሁኔታና ደረጃ ክትትል ስለሚፈልግ ወደ ጽኑ ህክምና ክፍል እንዲገቡ ሊደረግ ይችላል።

    . ህመሙ በቂ እረፍት ስለሚፈልግ ጭንቀትን ማስወገድ ይኖርብናል።

 የአስም መባባስን እንዴት እንከላከል?

    . ለአስም ተብሎ የታዘዘ መድሃኒት ካለ በትክክል መውሰድ፣ 

    . ሲጋራ፣ ሺሻ ከማጨስ መቆጠብ

    . አስሙን ሊያባብ ከሚችሉ እንደ አበባ ብናኝ፣ አቧራ፣ ሽቶ ወዘተ..መራቅ፤

    . በቀዝቃዜ ወቅት ወደ ውጪ አለመውጣት ወይም ሙቀት ሊሰጡ የሚችሉ አልባሳትን መጠቀም

    . የአስም መባባስ ምልክቶች ካዩ ወዲያው ወደ ህክምና መሄድ፤

    . ተጨማሪ ክትባቶች እንደ ኢንፍሉየንዛ ያሉ ከሀኪሞ ጋር በመማከር በወቅቱ መውሰድ።