By : Helina Kebere- Year III Addis Ababa University – School of Medicine

ዉድ አንባቢ፣ እስኪ እንደመነሻ አንድ ነገር ባሃሳብዎ ያሰላስሉ። በልብዎ አስር የሚያውቋቸውን ሰዎች ይቁጠሩ፤ ከመካከላቸው ምን ያህሉ የአዕምሮ ህመም ያለባቸው ይመስልዎታል?

የአዕምሮ ጤና ማለት የአንድ ሰው ያለውን አቅም ለመጠቀም፣ በዕለት ተለት ኑሮው የሚያጋጥመውን ውጥረት ለመቋቋም እንዲሁም በሚኖርበት ማህበረሰብ ፍሬያማ አስተዋፅኦ ለማበርከት የሚያስችለው የስነ-ልቦና ሁኔታ ላይ መሆን ማለት ነው። ይህ የስነ-ልቦና ሁኔታ ከተለመደው መስተጋብር ውጪ የሆኑ በአዕምሮ ላይ በሚፈጠሩ ጫናዎች ማለትም ባልተስተካከለ የትምህርት ወይም የስራ ሁኔታ፣ በቤተሰብ ውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች ብሎም በእርስ በርስ ግንኙነቶች ላይ በሚኖሩ ውጥረቶች ሊረበሽ ይችላል፡፡

የአዕምሮ ህመም ተቀባይነት ባላቸው መመዘኛዎች መመርመርና መታከም የሚችል የጤና እክል ነው። ይህም ተገቢውን ህክምና ካላገኘ የአንድ ሰው አስተሳሰብ፣ ጸባይና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል።

የአዕምሮ ጤና መረበሽ ለረጅም ጊዜ ሳይስተካከል ከቆየ የአዕምሮ ህመም ሊያስከትል ቢችልም፣ አሳሳቢ የአዕምሮ ጤና ኖሯቸው የአዕምሮ ህመም የሌለባቸው ግለሰቦች እንዲሁም ጥሩ የአዕምሮ ጤና ሁኔታ ላይ የሚገኙ የአዕምሮ ህሙማን በመኖራቸው ሁለቱን ስያሜዎቸ አንድ ትርጓሜ እንዳላቸው አድርጎ መውሰድ ተገቢ አይደለም። 

ያሉት ክፍተቶች ምንድን ናቸው?

እ.ኤ.አ. 2001 የአለም የጤና ድርጅት እንዳስቀመጠው ከእያንዳንዱ አራት ሰው አንዱ በህይወት ዘመኑ በአዕምሮ ወይም ኒውሮሎጂያዊ ህመም ይጠቃል፡፡ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ኢትዮጲያ ውስጥ ቁጥሩ ወደ 12% ዝቅ ይላል፡፡ ይህም ማለት ቀደም ብለው ከቆጠሯቸው አስር ሰዎች አንድ ወይም ሁለቱ አሁን ወይም ወደፊት የአዕምሮ ህመም ተጠቂ ይሆናሉ ማለት ነው። ለአንዳንዶቻችን ለመቀበል እንደሚከብድ ይሰማኛል። ለህመሙ ስለሰጠነው ትርጓሜና ስላለን የግንዛቤ ማነስም እንደ ትችት ሊወሰድ ይችላል። ቀጥሎ ከነዚህ ጉድለቶች የሚነሱ ችግሮችን እንመለከታለን።

ያልተገባ ብያኔ መስጠት (Stigma)

የአዕምሮ ህሙማን ሰውነታቸው ውስጥ የሚካሄደውን ኬሚካዊ አለመመጣጠን እና የአስተሳሰብ፣ የስሜትና የጸባይ መዛባትን ከመቋቋም ባለፈ ህብረተሰቡ ከሚሰጣቸው እንደ ጠበኛ ናቸው፣ ተጠያቂ አይደሉም፣ አደገኛ ናቸው አይነት ያልተገባ ብያኔ ጋር የመኖር ጫና አለባቸው፡፡ ይህም እንደ ፍራቻና ንዴት ላሉ አሉታዊ አመለካከቶች (Prejudice) እና መገለል (Discrimination) ይዳርጋቸዋል። እነዚህ ተዳምረው ለሌላው ሰው ከሚሰጠው ያነሰ መብትና እድል እንዲሰጣቸው ስለሚያደርጉ ጥሩ ስራ፣ ኑሮና ማህበራዊ ህይወት ሳይኖራቸው ለመኖር ይገደዳሉ።

ተገቢውን ህክምና አለመሻት

ማህበረሰብ ላይ የተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች እንደ ስኪዞፍሬኒያ (Schizophrenia) እና የስሜት መዋዠቅ (Bipolar Disorder) ያሉ ከፍተኛ የአዕምሮ ህመሞች (Severe Mental Disorders) የባለሞያ እርዳታ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው ያሳያሉ። ሆኖም መንፈሳዊ ምክንያት እንዳላቸው ስለሚታመን ወይም ልዩ የአዕምሮ ህክምና እንዳለ ስለማይታወቅ ሕሙማንና ቤተሰቦቻቸው ወደ ባህላዊ ህክምናና ሃይማኖታዊ ቦታዎች መሄድ ይቀናቸዋል።

ዘመናዊ ህክምናን ላለመጠቀም የግንዛቤ ማነስ ብቸኛው ምክንያት አይደለም። ከዘመናዊ ጋር ሲነጻጸር ለባህልና ሃይማኖታዊ ህክምና የሚወጣው ወጪ ያነሰ ነው። የባለሙያዎቹ የአኗኗር ዘይቤ ከዘመናዊ ህክምና ባለሙያዎቸ ይልቅ ከማህበረሰቡ ጋር የተሻለ ቁርኝት መኖሩም ለባለሞያዎቹ ከፍ ያለ አመኔታ እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል። ዘመናዊ ህክምና በቶሎ ፈውስን ያስገኛል የሚል የተሳሳተ አመለካከትም አለ። ይህ በማይሆን ጊዜ ሕሙማን የተለያዩ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊኖሯቸው የሚችሉ ክኒኖችን ለረጅም ጊዜ ከመውሰድ በባህላዊ ሃኪም የሚሰጡ እንደ ክታብ ያሉ ምልክታዊ መከላከያዎችን መጠቀምን ይመርጣሉ።

ከፍተኛ የአዕምሮ ህመሞች (Severe Mental Disorders) ባሏቸው ምልክቶች ክብደት ምክኒያት ችላ ባይባሉም እንደ ድባቴ (Depression) ያሉ እክሎች ግን ጭራሽ እንደ ህመም ስለማይወሰዱ እርዳታ ፍለጋ ብዙም አይስተዋልበትም። በመሆኑም የስነ-አዕምሮ ህክምናን መሻት ግለሰቦች ትክክለኛ ላልሆነ ህክምና ከተጋለጡ በኋላ እና ምናልባትም ራሳቸውን ለማጥፋት ከሞከሩ በኋላ የሚታሰብ አማራጭ ነው፡፡

በቂ ያልሆነ ተደራሽነት

ተገቢ ህክምናን በጊዜው ማግኘት የአዕምሮ ህመም እንደማንኛውም በሽታ ታክሞ እንደሚድን ስለሚያረጋግጥ ተያይዘው የሚመጡ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ይቀንሳል። ነገር ግን በሀገራችን ያሉት 40 የስነ-አዕምሮ ሃኪሞች እና 14 የስነ-ልቦና ባለሙያዎች ከ100 ሚሊየን በላይ ለሚሆን ህዝብ ተመዛዛኝነታቸው እጅግ ትንሽ ከመሆኑ ባለፈ ባለሙያዎቹ የሚገኙት በከተሞች በመሆኑ ለአብዛኛው ሰው ተደራሽነት የላቸውም። በመሆኑም በክልል ወረዳ ደረጃ ወደ 60 የሚጠጉ ተቋማት በስነ-አዕምሮ ነርሶች የሚመሩ ናቸው። በአዲስ አበባና አካባቢዋ የአዕምሮ ህክምናን የሚሰጡ 10 የተመላላሽ፣ ተኝቶ ህክምናና ልዩ ህክምና ተቋማት ይገኛሉ። በክልል ከተሞች የተኝቶ ህክምና አገልግሎት የሚገኘው በጅማና መቀሌ ሲሆን ማስተናገድ የሚችሉት ጥቂት ሰው ነው። ተመላላሽ ህክምና ከአዲስ አበባ ውጪ የሚሰጠው በስድስት የክልል ከተሞች (አዳማ፣ ሀረር፣ ሀዋሳ፣ ጅጅጋ፣ ጅማና መቀሌ) ብቻ ነው። 

መድሃኒት መጠቀም መቆጣጠር የሚያስቸግር ባህሪንና አካላዊ እንቅስቃሴን የማገድን አስፈላጊነት ይቀንሳል። ቢሆንም የመድሃኒት አቅርቦት አስተማማኝ ባለመሆኑ መታከም የሚችሉ ሁኔታዎች ከፍተኛ ደረጃ ደርሰው ህሙማን ለራሳቸውና በአቅራቢያቸው ላሉ ሁሉ አደጋ ሲሆኑ ይስተዋላል።

እነዚህ ችግሮች ተዳምረው የአዕምሮ ጤንነት የማህበረሰብ ጤና ትኩረት ማግኘት የሚገባው ጉዳይ ሆኖ ሳለ ከስራና ማህበራዊ ህይወት የተገለሉ፣ በቤታቸው ወይም ሌሎች ቦታዎች ተዘግቶባቸው ሲብስም መብታቸው እየተጣሰ ያሉ ብሎም በመንገድ ላይ የሚኖሩ በርካታ የአዕምሮ ህሙማን እንዲኖሩ ምክንያት ሆነዋል።

ምን ማድረግ እንችላለን?

የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር በኢትዮጲያ ለመቀነሱ አንድ ምክንያት ሊሆን የሚችለው ብዙውን ህዝብ ያማከሉ ጥናቶች አለመደረጋቸው ነው። ሌላው ደግሞ ማህበራዊ ኑሮዋችን የተሳሰረ በመሆኑ ሰዎች የተለያየ ውጥረት ሲደርስባቸው ከአካባቢያቸው ድጋፍ ለማግኘት አለመቸገራቸው እንደሆነ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ይህንን ማህበረሰባዊ ትስስር እንደግብዓት መጠቀም ያሉብንን ችግሮች ለመቅረፍ ያግዛል።

ማህበረሰባዊ ተቋማትን መጠቀም

ቀድሞ እንደተገለፀው የአዕምሮ ህሙማን ምልክቶችን ሲያዩ በመጀመሪያ የሚጎበኙት የእምነት ቦታዎችና የባህል ህክምና ባለሙያዎችን ነው። እነዚህ የህብረተሰቡ አካላት ስለህመሞቹ የተሻለ ግንዛቤ የሚያስገኙና የህመም ምልክቶችን መለየት የሚያስችሉ ስልጠናዎች ቢሰጧቸው የአገልግሎቶቻቸውን ጥራት መጨመርና ተገቢ ያልሆነ ህክምናን መቀነስ ያስችላል። ከዚህም በተጨማሪ ተሰሚነትና ተዓማኒነት ያላቸው በመሆኑ ከአገልግሎታቸው ጎን ለጎን በስነ-አዕምሮ ባለሙያዎች የሚሰጡ ህክምናዎችን እንዲከታተሉ በመምከር የተሻለ እንክብካቤን ማድረስ ይችላሉ።

የአዕምሮ ህመም የቆየባቸው እና ህክምና ተቋማት ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ የቆዩ ግለሰቦች ማህበራዊ መስተጋብሮችን እስኪላመዱ የመልሶ መቋቋም አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል። ይህንን ማህበርና ፅዋ የመሳሰሉ ተቋማት ላይ ተሳትፎ እንዲያረጉና የእምነት ቦታዎች እንዲሄዱ በማበረታታት ማገዝ ይቻላል።

ለልዩ ህክምና የሚወጣው ወጪ መብዛት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ሲሆን የቁጠባ ተቋማት (እድር፣ እቁብ) የተቸገሩ ቤተሰቦችን በገንዘብ በመርዳት የራሳቸውን ሚና መጫወት ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም የስነ-ልቦና ድጋፍ መስጠት ላይ መሳተፍም ሌላ አማራጭ ነው።

እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች የመፍትሄ አካል ለማድረግ በመጀመሪያ በግልፅ የሚታየውን የተሳሳተ አመለካከትና ማግለል ማስተካከል አለብን። ይህ በዋነኝነት የሚሰራው የአስተሳሰብ ለውጥን በማምጣት ነው። ለሰዎች ቀጥታ ትምህርትን ከመስጠት ይልቅ የማህበረሰብ መሪዎች (የእድር ሊቀመንበሮች፣ የሃይማኖት አባቶች…) የተሻለ ተሰሚነት ስለሚኖራቸው ለነሱ ቀድሞ ግንዛቤ በማስጨበጥ ለቀረው ማህበረሰብ የማድረስ ስራ ለነሱ መተው የተሻለ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ህሙማኑን የተቋሞቻቸው አካል በማድረግ ከሌሎች ሰዎች ጋር አገናኝተው የተጋነነ ልዩነት እንደሌላቸው በማሳየት ካልተገባ ብያኔ መታደግ ይችላሉ።

ሌሎች መፍትሄዎች…

የልዩ ባለሙያና ተቋማት ቁጥርን ለመጨመር ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ከዚህ ጎን ለጎን ከታካሚዎች ጋር በቅርበት የሚሰሩ የስነ-አዕምሮ ስልጠና የሌላቸው ባለሙያዎች (ጠቅላላ ሀኪሞችን፣ ጠቅላላ ነርሶችን፣ የጤና መኮንኖችንና ጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን) ህሙማንን ማከም እንዲችሉ እና መምህራን በትምህርት ቤቶች ውስጥ የተማሪዎችን ምልክቶች ገምግመው ለህክምና ለመላክ እንዲችሉ ስልጠና መስጠትም ተደራሽነትን ያሻሽላል።

Covid-19 እና የአዕምሮ ጤና

Covid-19 በዋነኝነት የአካል ጤንነትን የሚያውክ ዕክል ቢሆንም የአዕምሮ ጤና ላይ ተፅዕኖ ሊያደርግ ይችላል። እንደ ከመጠን ያለፈ ጭንቀት (General Anxiety Disorder) እና ኦብሰሲቭ ኮምፐልሲቭ ዲስኦርደር (Obsessive Compulsive Disorder) አይነት ህመም ያለባቸው ሰዎች በወረርሺኙ ምክኒያት ምልክቶቻቸው ሊባባሱ ይችላሉ። የአዕምሮ ህመም የሌለባቸው ግለሰቦች ላይም አለመረጋጋትን በመፍጠር የጤና መታወክ ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህም መገናኘት አስቸጋሪ ቢሆንም በመደዋወልና ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ድጋፍ መሰጣጠት ተገቢ ነው።

ባሳለፍነው ዓመት ግንቦት ወር በዶክተር ማጂ ሃይለማሪያም አነሳሽነት በስልክ የማማከር አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል የስልክ መስመር ለማስጀመር የተጀመረ ዘመቻ ነበር። ይህም የአዕምሮ ህሙማን በወጡት የመራራቅ መመሪያዎች ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ ከሚሰጧቸው ሰዎች ርቆ በመቆየትና ሀኪሞቻቸውን ማግኘት ባለመቻል ሊከሰቱባቸው የሚችሉትን አደጋዎች ይቀንሳል። ለመመላለስ የማይመች አካባቢ ለሚኖሩና በሌሎች ምክኒያቶች ህክምና ቦታ መሄድ ላልቻሉ ሰዎች የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማረጋገጥም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ነው።

በመጨረሻም አካላዊ ጤናና የአዕምሮ ጤና የሚወራረሱ በመሆናቸው የአዕምሮ ጤናን በመጠበቅ በሽታ የመከላከልን አቅም ማዳበር እንዲሁም አመጋገብን በማስተካከልና እንቅስቃሴን በማዘውተር የአዕምሮ ጤናን መንከባከብ ይገባል እላለሁ። ሠላም!

ዋቢ

  1. Federal Ministry of Health. (2012). Ethiopian National Mental Health Strategy. መስከረም 5, 2013. ከ https://www.mhinnovation.net/resources/national-mental-health-strategy-ethiopia የተገኘ
  2. Atalay, A., Menilik, D, and Mesfin, A. 1995. Mental health in Ethiopia EPHA Expert Group report. EJHD.
  3. Selamu, Medhin & Asher, Laura & Hanlon, Charlotte & Medhin, Girmay & Hailemariam, Maji & Patel, Ankit & Thornicroft, Graham & Fekadu, Abebaw. (2015). Beyond the Biomedical: Community Resources for Mental Health Care in Rural Ethiopia. PLoS ONE. 10. e0126666. 10.1371/journal.pone.0126666. 
  4. World Health Organization. 2001. Mental Disorders affect one in four people. https://www.who.int/whr/2001/media_centre/press_release/en/. መስከረም 5 2013 የታየ

ይሄ  አስተማሪ  የህክምና ፅሁፍ የቀረበው  የጤና ወግ እና የ ኢትዮጵያ ሕክምና ተማሪዎች ማህበር ባዘጋጁት የህክምና ተማሪዎችን የመረጃ አስበሰብ እና ህብረተሰቡን የማስተማር አቅማቸውን ለማዳበር ለታለመ የበጎ ፍቃድ ውድድር ነው። እያንዳንዱ ፅሁፍ በ ጤና ወግ የታየ እና እርማት ተደርጎበት የቀረበ ነው ።