By: Befekadu Molalegn Abebe(GP)
ፍቃዱ ሞላልኝ (ጠቅላላ ሀኪም)
Reviewed/Approved by: Dr. Fitsum Tilahun (Editor at Yetena Weg/ Nephrologist)
አሁን አሁን በመንገድ ላይ ስንሄድ በሚኒባስ ውስጥ የኩላሊት ታማሚዎች ተኝተው ሁለቱም ኩላሊቶቻቸው መስራት አቁመው ፤ በሳምንት 2-3ጊዜ የኩላሊት እጥበት እየተደረገላቸው እንደሆነና ለዘላቂ መፍትሄ የውጪ ሀገር ህክምና እንደሚያስፈልግ እየተገለፀ የገንዘብ እርዳታ መጠየቁን ከለመድነው ሰነባብተናል።
ነገር ግን ስንቶቻችን ነን ስለ ኩላሊት እጥረት ምንነት የምናውቀው?
የኩላሊት እጥበት ምንድን ነው?
የኩላሊት እጥበት ማለት ሁለቱም ኩላሊቶች ስራቸውን በአግባቡ ማከናውን ሳይችሉ ሲቀሩና መወገድ ያለባቸው መርዛማ ንጥረነገሮች ሳይወገዱ ቀርተው በደም ውስጥ በመጠራቀማቸው ጉዳት እንዳያደርሱ የሚወገዱበት፣ ወደሰውነት ተመልሰው መግባት ያለባቸው ንጥረነገሮች ደግሞ የሚመለሱበት እና የኩላሊትን የማጣራት ስራ በተወሰነ መልኩ የሚተካ የህክምና ዘዴ ነው።
የኩላሊት እጥበት ለሁሉም የኩላሊት ታካሚዎች ይደረጋል?
የኩላሊት እጥበት ለሁሉም የኩላሊት ታማሚዋች የማይደረግ ሲሆን የራሱ የሆነ የታማሚ የመመዘኛ መስፈርቶችም አሉት። ከእነዚህም ውስጥ በአንድ የኩላሊት ህመምተኛ ላይ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ምልክቶች ሲታዩ ይደረጋል።
በሰውነት ውስጥ የ ‘ዩርያ’ ንጥረነገር መከማቸትና በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ጉዳት ማድረስ። ለምሳሌ- የንቃተህሊና መቀነስ፣የልብና የሳንባ ሽፋን ጉዳት
ለሌሎች የህክምና መንገዶች ለውጥ የሌለው የሰውነት የውስጥ ፈሳሽ መብዛት
የሰውነት ማእድናት (ፓታስየም፣ፎስፈረስ፣…) መጠን መዛባት
የሰውነት የአሲድ መጠን መዛባት
የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና የሰውነት ክብደት ማሽቆልቆል
የኩላሊት እጥበት የማይደረግላቸው የኩላሊት ህመምተኞች ይኖሩ ይሆን?
አዎ። ከላይ የተዘረዘሩት ምልክቶች ቢኖሩም የኩላሊት እጥበት ላይደረግ የሚችልባቸው ጊዜያት አሉ።
ለምሳሌ
ምንም አይነት የደም ስር ማግኘት ካልተቻለ
ከፍተኛ የሆነ የልብ ድካም ካለ
ደም ያለመርጋት ችግር ያለባቸው ሰዎች
ከፍተኛ የሆነ የመርፌ ፍርሀት ካለ (Needle Phobia)
በኩላሊት እጥበት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች
የደም ግፊት መውረድ ወይም መጨመር
የልብ ድካም እና የአመታት ስርአት መዛባት
የጡንቻ ህመም
አለርጂ (በእጥበቱ ወቅት ጥቅም ላይ ለሚውሉ ኬሚካሎች አለርጂ ሊያጋጥም ይችላል)
ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት
የራስ ምታት
የነጭ የደም ህዋሳት ቁጥር መቀነስ
የደም አርጊ ህዋሳት(platelets) ቁጥር መቀነስ እና መድማት
ማሳከክ
ከእጥበት በኋላ ድካም
የማየት እና የመስማት ችግር
ትኩሳት(ከኢንፌክሽን ጋር የተያያዘም ያልተያያዘም ሊሆን ይችላል)
ነገር ግን የኩላሊት እጥበት የመደረጉና ያለመደረጉ የመጨረሻው ውሳኔ ቢደረግ የሚገኘውን ጥቅምና የጎንዮሽ ጉዳት ፣ ባይደረግ ደግሞ የሚከተለውን መዘዝ እንዲሁም ሌሎች የህክምና አማራጮች መኖርና አለመኖራቸውን በማመዛዘን በሀኪሙ እና በታካሚው የጋራ መግባባት የሚደረግ ነው።
ግን እስከ መቼ??
ይህ እንግዲህ በኩላሊት ህመሙ መንስኤ ላይ የሚመሰረት ነው። ማለትም የኩላሊት ህመሙ በድንገተኛ/ጊዜያዊ/ አሁናዊ የኩላሊት ጉዳት(Acute Kidney Injury) ለምሳሌ በመድሃኒቶች በሚከሰት የኩላሊት ጉዳት፣ በመርዝ( በእባብ በመነደፍ)፣ ወዘተ የመጣ ከሆነ እጥበቱ ጊዜያዊ እና ኩላሊት ወደቀደመ የስራ ብቃት እስኪመለስ ድረስ ብቻ ይሆናል።
ነገር ግን የቆየ የኩላሊት ህመም(Chronic Kidney Disease) ምክንያት ለምሳሌ በስኳር፣በደምግፊት፣በቤተሰብ በሚተላለፉ ወይም በዘረመል ላይ በሚፈጠር ችግር ምክንያት እና ወዘተ የሚደረግ እጥበት ከሆነ የኩላሊት ንቅለ ተከላ እስከሚደረግ ወይም እስከ ህልፈተህይወት ድረስ ዘላቂ ይሆናል።
የኩላሊት እጥበት ላይ ላለ ታካሚ ምን መደረግ አለበት?
የእጥበቱ ሂደት ብዙ የጎንዮሽ ጉዳቶች ያሉት፣ ረዥም፣አድካሚ እና አሰልቺ፣የእለት ተእለት እንቅስቃሴን ሊገድብ የሚችል እንዲሁም ውድ ከመሆኑ አንፃር ታካሚዎች የተስፋ መቁረጥ፣ የመበሳጨት፣ አለፍ ሲልም ህክምናውን ያለመቀጠል ስሜት ሊያሳዩ እንደሚችሉ ቀድሞ ማወቅ ፣ መዘጋጀትና አስታማሚዎች ለራሳቸውም ለታካሚዎችም ያልተቋረጠ የስነልቦና ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪ የኩላሊት ንቅለ ተከላው ሊደረግ የሚችልበትን አማራጭ ማፈላለግም ሁነኛ መፍትሄ ነው።
ታካሚዎችም ራስን በስነልቦና በማበርታት ሀኪም የሚሰጠውን መመርያ በመቀበል መተግበርና ሰውነታቸው የሚያሳየው አዳዲስ ምልክቶች ሲኖሩ በቶሎ ለሀኪም ማሳወቅ ይገባል።
የጤና ወግ
ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።
የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።
https://linktr.ee/Yetena_Weg