በዶ/ር ነህሚያ አንዳርጋቸው (በሚሌኒንየም የኮቪድ ህክምና ማዕከል ጠቅላላ ሀኪም)
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መባቻ ከነበረው የፈርንጆቹ ዲሴምበር 2019 ወዲህ ግዙፍ የሚባሉት የመድሃኒት አምራች ድርጅቶች እንዲሁም የተወሰኑ ሃያላን መንግስታት በሚያስደንቅ ርብርብ እንዲሁም እጅግ በጣም አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ የኮቪድ 19 ክትባትን ለመፈብረክ ችለዋል። ይህ ዜና በወረርሽኙ ለተናጋችው አለማችን እንደ ትልቅ መልካም ዜና ቢወሳም አብሮት ግን በርካታ ጥያቄዎችን እና ግርታዎችን አስከትሎ መጥቷል። በዚህ ጽሁፍም የኮቪድ 19 ክትባት ግርምትን እንዲሁም ተያያዥ ጥያቄዎችን እያየን የምንሄድ ይሆናል።
የኮቪድ 19 ክትባት አጭር ዳራ
የኮቪድ 19 ክትባትን በውስን መልኩ፤ ማለትም ለወታደራዊ ኃይሏ እንዲሁም ለወረርሽኙ እጅግ በጣም ተጋላጭ ለነበሩ የጤና ባለሞያዎቿ በመስጠት ቀዳሚነቱን የወሰደችው ቻይና ስትሆን ይህም የሆነው እ.ኣ.ኣ በጁን 2020 ነበር። ከአንድ ወር በኃላም ሩሲያ ‘ስፑትኒክ‘ ብላ የሰየመችውን ክትባት ለወረርሽኙ እንዲውል እንደፈቀድች አስታወቀች። ነገር ግን በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት የነብረው የነዚህ ክትባቶች ስርጭት የተገደበ ከመሆኑም በላይ ክትባቶቹ የነበራቸው የበሽታ መከላከል አቅም ለተቀረው ዓለም በተፈለገው መጠን ግልጽ አልነበረም። በቀጣይነትም በርካታ ድርጅቶች የምርምር ስራዎቻቸውን በማጠናቀቅ ፈቃድ ለማግኘት እሽቅድድማቸው ጦፈ። በዲሴምበር 2፤ 2020 የፋየዘር ባዮንቴክ ክትባት በሃገረ እንግሊዝ ፈቃድን በማግኘት በምእራባዊው አለም የመጀመሪያው ክትባት ሆኗል። በአሁኑ ሰአትም 20 አይነት ክትባቶች በአለማችን ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን በጠቅላላው ደግሞ 330 የክትባት አይነቶች አሁንም በምርምር ሂደት ላይ ይገኛሉ።
በአህጉራችን እንዲሁም በሃገራችንም የአስትራዜኒካ ክትባት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የክትባት አይነት ነው። ይክ ክትባት እንዲሰጥ የሚመከረውም ከ8 እስከ 12 ሳምንታት ልዩነት ባላቸው ሁለት ዙሮች ነው። የአለም ጤና ድርጅት እንደሚጠቅሰው ይህ ክትባት የህመም ምልክትን ከሚያሳይ የኮቪድ 19 ኢንፌክሽን በ64 ፐርሰንት የመከላከል አቅም አለው። ይህም ማለት የአስትራዜኒካን ክትባት ከወሰዱ መቶ ሰዎች ውስጥ 64ቱ በኮቪድ 19 አይያዙም፤ቢያዙም ደግሞ ምንም አይነት የህመም ምልክት አያሳዩም ማለት ነው። በተጭማሪም እንደ አስትራዜኒካ ፈብራኪዎች ማብራሪያ፤ ክትባቱ ከባድ የኮቪድ ህመምን የመከላከል አቅሙ ከ99 ፐርሰንት በላይ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ስለኮቪድ 19 ክትባት መታወቅ ያለባቸው ቁልፍ ነጥቦች
- የኮቪድ 19 ክትባቶችን በመጠቀም በኮቪድ 19 ቫይረስ የሚከሰተውን ህመም መከላከል ይቻላል። እስከሞት ድረስ ሊያደርስ የሚችለውን ጠንካራ የህመም ደረጃንም በሚገባ ይከላከላል።
- የኮቪድ 19 ክትባቶች የሰዎችን ቫይረሱን የማሰራጨት እድል ይቀንሳሉ። ይህም የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት ትልቅ ሚና ይኖረዋል።
- የኮቪድ 19 ክትባትን የወሰደ ሰው ሊሰማው የሚችሉ የተወሰኑ ተጓዳኝ ምልክቶች ይኖራሉ። ለምሳሌ የድካም ስሜት፤ ራስ ምታት፤ ብርድ ብርድ ማለት እንዲሁም ቁርጥማት ሊጠቀሱ ይችላሉ። እነዚህ ምልክቶች ክትባቱን በወሰዱ ሰዎች ላይ የሚጠበቁ ሲሆን በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚጠፉ ይሆናል። የህመም ማስታገሻ መድሀኒቶችም በቀላሉ ምልክቱን ለማጥፋት ያግዛሉ።
- አንድ ሰው ሙሉ ለሙሉ ተከትቧል ለማለት ከመጨረሻው ክትባት በኋላ ሁለት ሳምትታን ይፈጃል። ይህም ማለት የባለሁለት ደረጃ ክትባትን ለወሰዱ ሰዎች ሁለተኛውን ክትባት ወስደው ሁለት ሳምንታት ካለፉ በኋላ ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ከክትባቱ ከሚገኘው ሙሉ ጥቅም ተቋዳሽ መሆን ይቻላል። በተጓዳኝ ክትባቱን አንድ ሰው ክትባቱን ከተከተበበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሁለት ሳምንት ባልው ጊዜ ውስጥ፤ የኮቪድ ህመም ተጋላጭነቱ ካልተከተበ ሰው ጋር ሲነጽጸር ልዩነት አይኖረውም ማለት ነው።
ከኮቪድ ክትባት ጋር የተያያዙ ልዩ ሁኔታዎች
- በተለያዩ ሁኔታዎች የበሽታ መከላከል አቅማቸው የቀነሰ ግለሰቦች ላይ (ምሳሌ፤ የካንሰር ህመም ኪሞቴራፒ ታካሚዎች፤ የኤችአይቪ ታማሚዎች) የኮቪድ 19 ክትባት ውጤታማነት ሊቀንስ ይችላል። ውስን ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የበሽታ መከላከል አቅማቸው የወረደ ሰዎች ክትባቱን በመውሰድ የሚያገኙት የመከላከል አቅም በአንጻራዊነት የተገደበ እንደሆነ ነው። ነገር ግን ይህ ርእስ ተጨማሪ ጥናት እንደሚፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ያወሳሉ። ከዚህ ጎን ለጎንም የበሽታ መከላከል አቅማቸው የደከመ ሰዎች፤ ምንም እንኳን የቀነሰ ሊሆን ቢችልም፤ ከመከተብ ጥቅም እንደሚያገኙ አውቀው ክትባቱን እንዲወስዱ ይመከራል።
- በእርግዝና ላይ የሚገኙ ሴቶች እና የኮቪድ 19 ክትባት ጉዳይ ከልዩ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱን ድርሻ ይይዛል። ክትባቱ ለእርጉዝ ሴቶች ያለው ጥቅም ምንም እንኳን ግልጽ ቢሆንም በጽንስ ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ በቂ መርጃ የለም። እስካሁን ድረስ ክትባቱን በእርግዝና ወቅት በወሰዱ እናቶች እና ጨቅላዎች ላይ የተደረጉት ጥናቶች ያመላከቱት ‘ከባድ‘ ሊባል የሚችል ተጓዳኝ ተጽእኖ ባይኖረም ያለረጅም ጊዜ ጥናት ስለክትባቱ ድህንነት በእርግጠኝነት መናገር እንደሚያስቸግር የዘርፉ ባለሙያዎች ይተነትናሉ።
- የኮቪድ 19 ቫይረስ አይነቶች እየተበራከቱ እንደመጡ ይታወቃል። ክትባቶቹም ይህ ጽሁፍ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ ከእነዚህ የቫይረሱ አይነቶች የመከላከል አቅማቸው ጥሩ እንደሆነ ተገልጹዋል።
- አንድ አንድ የአለማችን ሃገራት 3ኛ ዙር ክትባት (ቡስተር ዶዝ) ለተወሰኑ የማህበረሰቡ አካላት መጀመራቸውን አስታውቀዋል። ይህም የሆነው በተለይም በእድሜ የገፉ ሰዎች ላይ የሚኖረውን የበሽታ መከላከል አቅም መዳከም ጋር ተያይዞ ክትባቱ በሁለት ዙር በቂ ስራ ላይሰራ ይችላል ከመባሉ ጋር ተያይዞ ነው። ይህንንም ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አንድ አንድ ሃገራት በመጪዎቹ ወራት እድሜያቸው ከ 75 ዓመት በላይ ለሆኑ ግለሰቦች 3ኛ ዙር ክትባት ለመስጠት ወጥነዋል።
ምንጭ፡
cdc,gov/coronavirus
astrazeneca.com