በረድኤት ወልደሩፋኤል(በቅ/ጳ/ሚ/ሜ/ኮ የ5ኛ አመት ተማሪ)  

By Rediet Wolderufael, C2 (5th year) medical student, SPHMMC

Approved by: Dr. Misikir Anberbir (Gynecologist/Obstetrician) 

 

 

የወር አበባ ጊዜ ህመም (Dysmenorrhea) ማለት ከየወር አበባ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ህመም ሲሆን፤ በብዛት የሆድ ቁርጠት እና የወገብ (የታችኛው ጀርባ) ህመም ስሜት አለው። በአንዳንዶች ላይ የታፋ ህመም ፣ ተቅማጥ፣ የማቅለሽለሽ ስሜት፣ ማስመለስ፣ ራስ ምታት እና ድካም ምልክቶች ሊኖሩት ይችላል።

የወር አበባ ከሚያዩ ሴቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በየወሩ ከ 1 እስከ 2 ቀን ድረስ ሕመም ያጋጥማቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሕመሙ የለዘበ ነው። ይሁን እንጂ ለአንዳንድ ሴቶች ይህ ሕመም በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ በወር ውስጥ ለበርካታ ቀናት የተለመደውን እንቅስቃሴያቸውን እንዳያከናውኑ ይከለክላቸዋል።

 

ሁለት አይነት የወር አበባ ጊዜ ህመም አሉ። እነዚህም፦

• ከበሽታ ጋር ያልተያያዘ የወር አበባ ጊዜ ህመም (Primary Dysmenorrhea) እና

• ከበሽታ ጋር የተያያዘ የወር አበባ ጊዜ ህመም (Secondary Dysmenorrhea)

 

ከበሽታ ጋር ያልተያያዘ (Primary Dysmenorrhea) የሚከሰተው ፕሮስታግላንዲን በተባሉ ከማህፀን ግድግዳ ላይ ባሉ ተፈጥሯዊ ኬሚካሎች ምክንያት ነው። እነዚህ ኬሚካሎች (ፕሮስታግላንዲኖች) የማህፀን ጡንቻዎችና የደም ሥሮች እንዲኮማተሩ ያደርጋሉ። ‍ይህ መኮማተር ለህመሙ መንስኤ ይሆናል። የነዚህ ፕሮስታግላንዲኖች (ኬሚካሎች) መጠን የወር አበባ የመጀመሪያ ቀናት ላይ ከፍተኛ ስለሆነ ሕመሙም ከፍተኛ ነው። የደም መፍሰስ እየቀጠለና የወር አበባ እየፈሰሰ ሲሄድ የፕሮስታግላንዲኖች መጠን ይቀንሳል። ሕመምም ከመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት በኋላ የሚቀንሰው ለዚህ ነው። ይህ የወር አበባ ጊዜ ህመም የሚጀምረው አንዲት ልጅ የወር አበባ ማየት ከጀመረች ብዙም ሳይቆይ ነው። ብዙ ሴቶች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ የወር አበባ ጊዜ ህመም እየቀነሰ ይመጣል። ይህ ዓይነቱ ሕመም ከወሊድ በኋላም ሊሻሻል ይችላል።

 

ከበሽታ ጋር የተያያዘ (Secondary Dysmenorrhea) የሚከሰተው በመራቢያ አካላት ላይ በሚከሰት የጤና እክል ምክንያት ነው። ሕመሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ከተለመደው የወር አበባ ቁርጠት የበለጠ ጊዜ ይቆያል። በተጨማሪም ሕመሙ የሚጀምረው የወር አበባ ከመጀመሩ ከጥቂት ቀናት በፊት ሊሆን ይችላል። ሕመሙ እየተባባሰ ሊሄድና የወር አበባ መፍሰስ ካቆመ በኋላ ላይጠፋ ይችላል።

 

የወር አበባ ጊዜ ህመም እንዴት ማከም እንችላለን?

የወር አበባ ጊዜ ህመምን በርካታ የቤት ውስጥ ዘዴዎች ፣ የሕመም ማስታገሻ እና የሆርሞን ህክምና(hormonal therapy) በመጠቀም ማከም ይቻላል።

 

የቤት ውስጥ ዘዴዎች

1. ሙቀት-በታችኛው ሆድ ላይ ማሞቂያ ፓድ ወይም ሙቅ ውሃ የያዘ ጠርሙስ በመጠቀም ማሞቅ ህመምን በእጅጉ ሊቀንስ ይችላል። የሕመም መቀነስ አቅሙም ከማስታገሻ መድሃኒት ጋር ተወዳዳሪ ሲሆን የማስታገሻ መድሃኒት እና ሙቀትን በጋራ መጠቀም የበለጠ ህመም የማጥፋት አቅም አለው። በጣም ሞቃት በሆነ የማሞቂያ ፓድ ወይም ትኩስ የውሃ ጠርሙስ ቆዳን ከማቃጠል መቆጠብ አስፈላጊ ነው፤ በግምት 40ºC (ለሰስ ያለ) ሙቀትን መጠቀም ይመከራል። ሙቀቱ አስፈላጊ ሆኖ በሚታሰብበት ጊዜ ሁሉ ልንጠቀመው እንችላለን።

2. የአካል ብቃት እንቅስቃሴ- በሳምንቱ ውስጥ አብዛኛውን ቀን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ከማረግ ባለፈ ሕመምን የሚያግዱ ኬሚካሎችን ለማምረት ይረዳል። ለዚህም እንደ መራመድ፣ የሶምሶማ ሩጫ ፣ ሳይክል መንዳት ወይም መዋኘት የመሳሰሉት የኤሮቢክ እንቅስቃሴዎች ይመከራሉ።

3. እንቅልፍ- ከወር አበባ በፊትና ወቅት በቂ እንቅልፍ መተኛት አስፈላጊ ነው። ጥሩ እረፍት ማግኘት የወር አበባ ጊዜ የሚያጋጥምን ህመም ለመቋቋም ሊረዳ ይችላል።

 

የሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች

• የሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች (NSAIDs)-ህመምን እና ትኩሳትን የሚቀንሱ መድሃኒቶች ሲሆኑ፤ ከየወር አበባ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሕመምን በመቀነስ ረገድ በጣም ውጤታማ የሆኑ መድኃኒቶች ናቸው። አንዳንድ የሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች (NSAIDs) ያለ ሐኪም ማዘዣ መገኘት ይችላሉ፤ ከነዚህም አይቡፕሮፌን(Ibuprofen) በዋናነት ይጠቀሳል። እነዚህ መዳኒቶች (NSAIDs) የደም መፍሰስ ወይም ሌሎች የወር አበባ ምልክቶች እንደጀመሩ ወይም ከጀመሩ ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት ባለ ጊዜ በቋሚ ፕሮግራም ከተወሰዱ በጣም ውጤታማ ናቸው ። የደም መፍሰስ ችግር፣ አስም፣ አስፕሪን አለርጂ፣ የጉበት ጉዳት፣ የኩላሊት ጉዳት፣ የአንጀት ቁስል፣ የጨጓራ ቁስል እና የመሳስሉት ተያያዥ በሽታ ያለባቸው ሰዎች እነዚህን የሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች (NSAIDsን) መውሰድ የለባቸውም። በተጨማሪም ስለ የወር አበባ ጊዜ ህመምን ማስታገሻ ጉዳይ ሃኪም ማማከር ይኖርባችዋል።

 

የሆርሞን ህክምና (hormonal therapy)  

• የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች (ኪኒኖች) እና ሌሎች የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች (ለምሳሌ፡ መርፌ፣ ሉፕ (IUD) እና የቆዳ ስር የሚቀመጠው የወሊድ መከላከያ (ኢምፕላንት) የወር አበባ ጊዜ ህመም ላላቸው ሴቶች ውጤታማ ህክምናዎች ናቸው። እነዚህ መድሀኒቶች ፕሮስታግላንዲንን (ማህፀን እንዲኮማተር የሚያደርገው ኬሚካል) የሚያመርተው የማህፀን ግድግዳ በመቀነስ ሕመም፣ ቁርጠትና የወር አበባ መፍሰስ እንዲቀነስ ያደርጋሉ። ይህ ዘዴ በተለይ እርግዝናን መከላከል ለሚፈልጉ ሴቶች በጣም ጠቃሚ ነው ። ነገር ግን የወሲብ ግንኙነት የማያረጉ ሴቶችም ሊጠቀሙበት ይችላሉ። አብዛኛውን ጊዜ የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ ህክምናን ከሁለት እስከ ሶስት ወር ከተጠቀሙ በኋላ ከፍተኛ ለውጥ ይኖራቸዋል።

 

• ሉፕ (IUD)- ሌቭኖርገስትሬል (ሚሬና) የተባለውን ሆርሞን የያዘው ሉፕ (IUD) ከላይ እንደተጠቀሱት የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች እና ሌሎች የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች የወር አበባ ጊዜ ህመምን 50 በመቶ ሊቀንስ ይችላል።

በተጠቀሱት ዘዴዎች ሕመሙ በበቂ ሁኔታ ካላስታገሰ ምን ማድረግ እንችላለን?

1. ለየወር አበባ ጊዜ ህመም በጣም ውጤታማ የሆኑ ህክምናዎች የሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች(NSAIDs) ፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ ኪኒኖች እና ሌሎች የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ናቸው። ከእነዚህ የሕክምና ዓይነቶች አንዱ በሁለት ወይም በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሕመሙን በበቂ ሁኔታ ካላስታገሰው ሌላ ሕክምና ሊሰጥ ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንዲት ሴት የሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች (NSAIDs) ሞክራ የወር አበባ ጊዜ ህመም ካልታገሰ፣ በሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች ምትክ ወይም በተጨማሪ የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ ልትወስድ ትችላለች።

 

2. ከላይ የተጠቀሱት መንገዶች ሕመምን በሚገባ ካላሻሻሉ ቀጣዩ እርምጃ ከበሽታ ጋር የተያያዘ (Secondary Dysmenorrhea) ሊሆን ስለሚችል የወር አበባ ጊዜ ህመም መንስኤዎችን መመርመር እና ማከም ነው። ለዚህም ህክምና ቦታ በመሄድ ተገቢውን ምርመራ እና ህክምና ማግኘት ተገቢ ነው።

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg