የደም ማነስ በሽታ የሚከሰተው በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ ቀይ የደም ህዋሳት ቁጥር ሲያንስ ወይም በውስጣቸው የሚገኘው ሄሞግሎቢን የሚባለው ሞለኪውል መጠን ሲያንስ ነው።
ቀይ የደም ህዋሳት በደማችን ውስጥ ከሚገኙ ብዙ አይነት ሌሎች ህዋሳት አንደኛው ሲሆኑ ዋነኛ ስራቸው በደም ስራችን ውስጥ ኦክስጅንን ከቦታ ቦታ ማዘዋወር ነው። ሁሉም የሰውነት ክፍሎቻችን ይህንን ኦክስጅን ከምግብ የምናገኘውን ንጥረ ነገሮች ወደ ኃይል (ጉልበት) ለመቀየር ይጠቀሙበታል።
ስለዚህ የደም ማነስ በሚኖርበት ጊዜ የሰውነታችን ህዋሳት በሙሉ በቂ ኃይል ስለማያገኙ ድካም ፣ አቅም ማጣት እና የመሳሰሉ ምልክቶች እናያለን።
የደም ማነስ ህመም ብዙ ሰዎችን ያጠቃል። ይሄ ችግር በተለይ እንደኛ ሀገር ባሉ ታዳጊ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት ላይ በብዛት ያታያል። ህፅናት፣ እርጉዝ ሴቶች እና በእድሜ የገፉ ሰዎች ለችግሩ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። እንደ ዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት መረጃ በዓለም ላይ ካሉ ሰዎች 25% የሚደርሱት ወይም ከአራት አንዱ ሰው የደም ማነስ በሽታ አለበት። ይህም ወደ 1.62 ቢልየን ሕዝብ ማለት ነው።
50% ያህሉ ለትምህርት ያልደረሱ ህፃናት የደም ማነስ ህመም አለባቸው፣ እንዲሁም ከእርጉዝ ሴቶች መሃል 40% የሚደርሱት ለደም ማነስ ህመም የተጋለጡ ናቸው። ይህም በእርግዝና እና ወሊድ ጊዜ ለተለያዩ ህመሞችና አልፎም ለሞት ሊያጋልጣቸው ይችላል። ምንጭ የ ዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት
በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው የደም ማነስ በቀይ የደም ሴሎች (ህዋሳት ) ቁጥር ማነስ ወይም በውስጣቸው የሚገኘው ሄሞግሎብን መጠን ማነስ የሚመጣ ነው።
ይህ ደግሞ በሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች ይከሰታል።
1 ሰውነታችን በቂ የሆነ ቀይ የደም ሴል (ህዋሳት ) ሳያመርት ሲቀር – መቅኒ (bone marrow ) ቀይ የደም ሴሎች (ህዋሳት) የሚመረቱበት ቦታ ነው ። ለግንባታው የሚያስፈልጉት ንጥረ ነገሮች (አይረን /Iron፣ ቪታሚን ቢ 12 /Vitamin B 12፣ ፎሊክ አሲድ Folic acid በ በቂ ሁኔታ ካላገኘን የምርት መጠናቸው ስለሚቀንስ የደም ማነስ ይከሰታል።)
2 ቀይ የደም ህዋሳት በተለያዩ ምክንያቶች ቶሎ ቶሎ የሚሞቱ ከሆነ – ቀይ የደም ሴሎች በአማካይ 120 ቀን/3 ወር ያህል ይኖራሉ። ከዛ መቅንያችን በሚያመርተው በአዲስ ሴሎች /ህዋሳት ይተካሉ ። ለዚህም ነው አንድ ጤነኛ ሰው ሌላ ችግር እስከሌለበት ድረስ በየሶስት ወሩ ደም ቢሰጥ ችግር የለውም የሚባለው። የተለያዩ አይነት በሽታዎች (ለምሳሌ ወባ፣ Sickle cell disease) ቀይ የደም ህዋሳት ከላይ ከተገለጸው ግዜ ቀድመው ቶሎ እንዲሞቱ በማድረግ የደም ማነስ በሽታ እንዲፈጠር ያደርጋሉ።
3 የደም መፍሰስ – ከአደጋ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ከፍተኛ የደም መፍሰስ፣ ሴቶች ከወር አበባ ጋር ተያይዞ ብዙ ደም የሚፈሳቸው ከሆነ ወይም በወሊድ ጊዜ የሚከሰት ከፍተኛ የደም መፍሰስ ለአጣዳፊ እና ዘላቂ የደም ማነስ ሊያጋልጥ ይችላል።
የደም ማነስ በተለያዩ ምክንያቶች የሚመጣ ስለሆነ ምልክቶቹ እንደ ምክንያቱ ሊለያዩ ይችላሉ።
በዋነኝነት ግን እነዚህ ምልክቶች ይታያሉ
- የድካም ስሜት
- አቅም ማጣት
- የትንፋሽ ማጠር
- የከለር መገርጣት ወይም ነጭ መሆን
- አንዳንዴ ደግሞ እንደ በሽታው አይነት የአይን እና ቆዳ ከለር ቢጫ መሆን
- የማዞር ስሜት
- ራስ ምታት
- የትኩረት ማጣት – በተለይ ህጻናት ላይ ትምህርት የመማር አቅማቸውን እና የማስታወስ ችሎታቸውን ይጎዳል።
አንዳንድ ጊዜ ምንም ምልክት ላይኖር ስለሚችል በላብራቶሪ በምርመራ ብቻ ሊታወቅ ይችላል።
በላብራቶሪ የደም ምርምራ የደም ማነስ አለ ምንለው መቼ ነው ? -ምንጭ WHO
እንደ አለም ጤና ጥበቃ ድርጅት አገላለጽ በላብራቶሪ የደም ምርመራ የደም ማነስ አለ የምንለው ለወንዶች የሄሞግሎቢን መጠን ከ13 mg/dl በታች ሲሆን ለሴቶች ደግሞ ከ 12 mg/dl በታች ሲሆን ነው።
ይህ ቁጥር እንደ እድሜያችን፣ የእንቅስቃሴያችን አይነት እና የምንኖርበት ቦታ ሊለያይ ይችላል ለምሳሌ እንደ ሀገራችን ባሉ ከፍተኛ ወይም ተራራማ ቦታዎች በሚበዙበት ቦታ የሄሞግሎቢን መጠን ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።
በምርመራ ወቅት ከሄሞግሎቢን በተጨማሪ የደም ማነስን ሊያመጡ የሚችሉ ምክንያቶች ምርመራ ሀኪምዎ ሊያደርግልዎት ይችላል ። ለምሳሌ የቫይታሚን ቢ12፣ የፎሊክ አሲድ መጠን እና የአይረን (የብረት ንጥረ ነገር)/ አብሮ ሊመረመር ይችላል።
የደም ማነስ እንዴት ይታከማል ?
የደም ማነስ በግዜ ካልታከመ ዘላቂ ችግር ሊያመጣ ይችላል። ህክምናውም እንደ ምክንያቱ ይለያያል።
በመግቢያው እንዳየነው ህፃናት ከአይረን (የብረት ንጥረ ነገር) በተያያዘ ለሚከሰት የደም ማነስ በጣም ተጋላጭ ናቸው ። ይሄ ደግሞ አካላዊ እና አእምሮኣዊ እድገታቸውን ይጎዳዋል። በተለይ በትምህርት ዕድሜ ላይ ያሉ ህፃናት ትምህርት የመቅሰም ችሎታቸውን ይቀንሰዋል። ስለዚህ ተገቢ የሆነ መደበኛ ምርመራ ህፃናት ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይሄ ምርመራ በወላጆች ወይም በትምህርት ቤት በኩል ሊደረግ ይችላል።
የአይረን እጥረት ያለባቸዉ ከምግብ ጋር ወይም በእንክብል መልክ ንጥረ ነገሩን እንዲያገኙ በማድረግ ህክምና ማግኘት አለባቸው።
የአይረን ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦች ለምሳሌ
- ቀይ ስጋ
- አሳ
- ባቄላ
- spinach (ጥቁር ጎመን)
- አተር የመሳሰሉት የደም ማነስን ለመከላከል ይጠቅማሉ ።
እንደሁኔታው ሀኪማችን የአይረን እንክብሎችን ሊያዝልን ይችላል።
በተጨማሪም እንደ ብርቱካን ኢንጆሪ ቃሪያ እና ቲማቲም ያሉ ከፍተኛ ቫይታሚን ሲ ያለባቸው ምግቦች ደግሞ ከምግብ የምናገኘውን አይረን ወደ ሰውነታችን ተብሏልቶ እንዲገባ ያግዛሉ።
እንደኛ በዓሉ ታዳጊ ሀገራት ውስጥ ያንጀት ውስጥ ጥገኛ ተዋሲያን ሌላው የደም ማነስ ምክንያቶች ናቸው። በተለይ ህፃናት ላይ ለዚህ የሚሆን ተገቢ ምርመራ ማድረግ እና ህክምናውን ማግኘት አለባቸው። ይህንንም ለመከላከል የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በየስድስት ወሩ በትምህርት ቤት ላሉ ህፃናት የአንጀት ጥገኛ ተዋንያንን የሚከላከሉ መድሃኒቶችን ይሰጣል። እርጉዝና የሚያጠቡ እናቶች ደግሞ ለደም ማነስ በጣም ከፍተኛ ተጋላጭ ስለሆኑ እነሱም ተገቢውን ክትትልና ህክምና ማግኘት አለባቸው በርግዝና ወቅት የአይን እጥረትና የፎሊክ አሲድ እጥረት ለደም ማነስ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ዋንኞቹ ናቸው
ለዚህም ተብሎ በርግዝና ወቅት አይረን እና ፎሊክ አሲድ የያዙ እንክብሎች በመደበኛነት ይሰጣሉ። በርግዝና ወቅት ተገቢውን ክትትል ማድረግ እና መድሃኒቶችን ሰዓት ጠብቆ መውሰድ የእናትንም የልጅንም ጤና ይጠብቃል።
የደም ማነስ በሌሎችም ተጓዳኝ ህመሞች ምክንያት ለምሳሌ የኩላሊት ህመም የተለያዩ የካንሰር ህመሞች ጋር ተያይዞ ሊመጣ ስለሚችል ሃኪም ጋ በመሄድ ተገቢውን ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።
የደም ማነስ በድንገት በደረስ አደጋ ወይም በልጅ መውለድ ወቅት በሚፈስ ከፍተኛ የደም መጠን ከተከሰተ ለሕይወት አስጊ ሊሆን ይችላል። በዚህ ወቅት ደምን የመተካት ሕክምና ይደረጋል። ብዙዎች በተለይ እናቶች የደም መተካት ሕክምና ባለማግኘት ለሞት ይዳረጋሉ።
ጤነኛ የሆናችሁና ደም መስጠት የምትችሉ ሰዎች በመደበኛነት ደም ብትለግሱ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ትታደጋላችሁ። ሰውነታችሁ በየሶስት ወሩ አዲስ ቀይ የደም ሴሎችን /ህዋሳትን እያዘጋጀ የሰጣችሁትን ደም ስለሚተካ ደም በመለገሳችሁ ምንም ተጓዳኝ ችግር አይከተልም።
የጤና ወግ
በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።
………………………………………………………………………………………………………………………..
ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።
በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።
የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።
በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣ በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ