የደም ግፊት መጨመርን ሙሉ ለሙሉ ማዳን (ወይም እንዳይኖር ማድረግ) አይቻልም፡፡ ነገር ግን በጣም ከፍ ያለ የደም ግፊትን በህክምና መቀነስ እና መቆጣጠር ይቻላል፡፡ በጣም አነስተኛ (መጠነኛ) የሆነ የደም ግፊት መጨመርን ጤናማ በሆነ የአኗኗር ዘይቤ በመምራት ልንቆጣጠር እንችላለን፡፡

የደም ግፊት መጨመርን እንዴት ማከም ይቻላል?

የደም ግፊት መጨመር ካለብዎ ከጤና ባላ ሙያ ጋር መማከር ይኖርቦታል። ተጨማሪ የሚይስፈልግዎትን ምርመራ ከተደረገልዎት ብኌላ ከእርስዎ አኗኗር ጋር የሚሄድ የህክምና መንገድ ይመረጥሎታል።

ጤናማ የሆነ የህይወት ዘይቤ መከተል በጣም ወሳኝ የሆነ የህክምናው አካል ነው፡፡ የደም ግፊት መጨመርን መቆጣጠር ያስችላል፡፡ ከእነዚህ ጤናማ የህይወት ዘይቤ መካከል የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ አነስተኛ ቅባት እና ጨው ያለባቸውን ምግቦች መመገብ፣ በቀን ውስጥ ለወንዶች ከሁለት ለሴቶች ደግሞ ከአንድ ብርጭቆ በላይ የአልኮል መጠጥ አለመጠጣት እና መደበኛ የሆነ በጤና ባለሙያ የተደገፈ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ይገኙበታል፡፡ ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ ደግሞ የጤና ባለሙያዎ እንዲያቆሙ ይመክሮታል ምክንያቱም ሲጋራ ማጨስ ድንገተኛ የሆነ የልብ ድካም እና ጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ (ስትሮክ) ሊያስከትል ይችላል፡፡

የደም ግፊትዎን ለመቆጣጠር መድኋኒቶችም ሊያስፈልጉ ይችላሉ፡፡ በርካታ የደም ግፊትን ለመቆጣጠር የሚረዱ መድኋኒቶች አሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የተለያዩ አይነት የደም ግፊት መድኋኒቶችን በአንድ ላይ መጠቀም ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ እነዚህን መድኋኒቶች ምንም አይነት ህመም ባይሰማዎት እንኳን በታዘዙት መሰረት መውሰድ አለቦት፡፡ ምክንያቱም ምንም የበሽታ ምልክት ሳይኖር ራሱ ከፍተኛ የደም ግፊት ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል ነው፡፡

የደም ግፊት መጠኔን ለመቆጣጠር ሌላ ተጨማሪ ምን ማድረግ አለብኝ?

የሚከተሉትን በማድረግ ራሶትን ሊረዱ ይችላሉ፡-

. መደበኛ የሆነ የህክምና ምርመራ ማድረግ

. ሁሉንም መድኋኒቶች በታዘዙት መሰረት መውሰድ (ጤነኛ እንደሆኑ ቢሰማዎትም)

. አመጋገብዎንና የሰውነት እንቅስቃሴን በሚመለከት የጤና ባለሙያዎን ምክር መከተል

. ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ ማቆም . ከአንድ ብርጭቆ በላይ አልኮል በቀን ውስጥ አለመጠጣት

. ሁሉንም የቤተሰቦን አካላት በህክምናዎ ዕቅድ ውስጥ ማሳተፍ

ምንጭ Click here

ምንም አይነት ጥያቄ ወይም ችግር ካጋጠሞት የጤና ባለሙያዎን ከማማከር ወደ ኋላ አይበሉ፡፡ ከህክምናው ዕቅድ ጋር ከተባበሩ የደም ግፊት መጠኖን በበቂ ሁኔታ መቆጣጠርና ሊደርሱ የሚችሉ ከፍተኛ ጉዳቶችን መከላከል ይችላሉ፡፡

መድኋኒቶቹ የጎንዮሽ ጉዳት ቢያስከትሉብኝስ?

የራስ ምታት፣ ማዞር፣ ድካም፣ የልብ ምት ሲጨምር መታወቅ፣ የእግር እብጠት፣ የወሲብ ህይወትዎ ላይ ጉዳት እና የመሳሰሉት አይነት የጎንዮሽ ጉዳቶች ካሉ ለጤና ባለሙያዎ ማሳወቅ አለቦት፡፡ የሚወስዱትን የመድኋኒት መጠን ማስተካከል ወይንም ደግሞ ለእርሶ በሚስማማ በሌላ መድኋኒት መተካት ይቻላል፡፡

ምንጭ

Source : The National Kidney Foundation.

ይህን የጤና መረጃ ከአሜሪካን የኩላሊት ህክምና ማህበር ድረ ገፅ ላይ ምንጭ አድርገን ስናቀርብ ፅሁፉን በመተርጎም የተባበርንን የሶዶ ክርስትያን ሆስፒታል ሀኪም ዶ/ር ይስሀቅ ገዛኸኝን ( Twitter: @IsaacG94778262 )  ከልብ እናመሰግናለን ።

If you want to read the original article in English please click here