በኤልሳቤጥ አባይ – በጥቁር አንበሳ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የPC 1 ህክምና ተማሪ
በጥር 30,2020 የአለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ባወጣው መረጃ መሠረት በአለም ውስጥ ከ 264 ሚሊዮን በላይ በሁሉም የድሜ ክልል ያሉ ሠዎች በድባቴ ይጠቃሉ ። ድባቴ በማንኛውም ዕድሜ ፣ ዘር ፣ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የትምህርት ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችን ሊያጠቃ ይችላል
በተለይ በአሁኑ ሰዐት በወረርሽኙ ምክንያት ሁሉም ሰዎች ቤት እንዲቆዩ በተገደዱበት ጊዜ ብዙ ሠዎች የድባቴ ህመም ሊያጋጥማቸው ይችላል።
ለመሆኑ ድባቴ ምንድን ነው?
የድባቴ ከተለመደው የስሜት ለውጥ እና በለት ከለት የህይወት ፈተናወች ምክንያት ከምናሳየው የስሜት መልስ ይለያል። ድባቴ በአንድ ሰው አስተሳሰብ ፣ ስሜት እና በተግባር ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሀዘን ፣ ገለልተኛነት እና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ተለይቶ የሚታወቅ የአእምሮ ሁኔታ ነዉ። ድባቴ ደስታን በሚያመጡ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ማጣትን ያመጣል። የአንድን ሰው ሀሳቦች ፣ ባህሪ ፣ ተነሳሽነት ፣ ስሜቶች እና ደህንነትንም ይለውጣል፡፡ ድባቴ ያጋጠማቸው ሰዎች የመጥፎ ስሜት ፣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይኖራቸዋል እናም በአንድ ሰው የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፣ ከፍ ሲልም ራስን የማጥፋት ሀሳቦችን ሊኖሯቸው ይችላል።
የድባቴ ህመም ዓይነቶች
1.ከባድ የድብርት ህመም /ድባቴ (major depression disorder) – ከባድ የሀዘን ወይም የፍላጎት ማጣት፣ የጭንቀት ስሜት ፣ ድካም ፣ በእንቅልፍ ላይ ለውጦች ፣ ክብደት መቀነስ ፣ትኩረት ማጣት፣ የከንቱነት እና የጥፋተኝነት ስሜቶች ፣ በተለመዱ እንቅስቃሴዎች ላይ ፍላጎት ማጣት ፣የሞት እና ራስን የማጥፋት ሀሳቦች ለሁለት ሳምንት በየቀኑ በሚባል ደረጃ ይታያሉ (ክብደት መቀነስ እና ራስን ከማጥፋት ሀሳብ ውጭ) ።
2. የማያቋርጥ ድባቴ (dysthymia) – ቢያንስ ለሁለት ዓመታት (1 አመት ለህጻናት) የሚታይ ሥር የሰደደ የድብርት ዓይነት ነው። በነዚህ ሁለት አመታት ህመሙ ያለባቸው ሰወች ያለ ድብርት ምልክቶች ከሁለት ወራት በላይ አይቆዩም።
3, የሚረብሽ የስሜት መለዋወጥ (disruptive mood dysregulation) – ህመሙ ያለባቸው ሰዎች ቁጣ ፣ መገንፈል ፣ንዴት እና መበሳጨት የሚያመጣ የድባቴ አይነት ነው።
4.ቅድመ– የወር አበባ ዲስፎሪክ ህመም (Premenustral dysphoric disorder) – የድባቴ ምልክቶቹ ከወር አበባ በፊት ባለው ሳምንት በግልጽ በሚታይ ወይም በምርመራ ሊታወቅ በሚችል መልኩ ይታያል ይህም ስራ የመስራት አቅምን ይቀንሳል ፤ማህበራዊ ወይም ቤተሰባዊ ትስስርን ይጎዳል።
5.በመድሀኒቶች ምክንያት የሚመጣ ድባቴ (substance /medication induced depressive disorder) – አደንዛዥ እፅ ፣ መርዝ፣የአዕምሮ በሽታ መድኃኒቶችን በመብላት፣በመርፌ ወደ ደም ዝውውር በማስገባት ፣ወይም በመሳብ ጊዜ የሚከሰት ድባቴ ነው።
6. በሌሎች ህመሞች ምክንያት የሚመጣ ድብርት (depression due to other medical conditions) – ለምሳሌ፦ Parkinson ፣ Huntington ፣ stroke ፣ traumatic brain injury ለድባቴ ተጋላጭነትን ይጨምራሉ።
7. Other specified and unspecified depression disordrs – ዋናዋነዎቹን የድባቴ ምልክቶች የሚያሟሉ ነገር ግን ከላይ የተገለፁትን የድብርት አይነቶች ሙሉ መስፈረት የማያሟሉ።
የድባቴ ህመም መንስኤዎች
- ሐዘን-የሚወዱትን ሰው በ ሞት ማጣት
- ህመም (እንደ የታይሮይድ በሽታ ፣ የአዲሰን በሽታ ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ የትኩረት እጦት / hyperactivity Disorder (ADHD)፣ ካንሰር ፣ የጉበት በሽታ )
- የገንዘብ ጫና- የገንዘብ ማጣት የሚፈጥረው ጭንቀት (በተለይ አሁን ላይ እንደበፊቱ ሥራ ሥለማይሰራ)
- አስጨናቂ የሕይወት ክስተቶች – ( አካላዊ ፣ ወሲባዊ ወይም ስሜታዊ በደሎች )
- የተወሰኑ የህክምና መድኃኒቶች – (ለካንሰር፣ለልብ፣Parkinson፣ seizure ህመሞች የሚወሰዱ መድሀኒቶች)
- ስነ-ባህሪ ( genetics ) – እናት ወይም አባት ድብርት ካለባቸው ልጃቸው የመያዝ እድሉ ይጨምራል
- አካባቢያዊ – አስጨናቂ የልጅነት ገጠመኞች
- ባህላዊ እምነቶች – ወንዶች ማልቀስ የለባቸውም አይነት ማህበራዊ ጫናዎች
- ጉርምስና – የጉርምስና ዕድሜ በስሜትና በባህሪ ከፍተኛ ለውጦች የሚታይበት እድሜ ነው።
- ገጽ ብቸኝነት – አንድ ሰው ከቤተሰብ ወይም ከጓደኞች ጋር የማይገናኝ ከሆነ ወይም ከቤተሰቡ ጋር ጊዜ የማያሳልፍ ከሆነ ወይም ቤተሰብ ከሌላቸው
- ልጅ መውለድ – በእርግዝና ወይም ከወሊድ በሗላ በሚለዋወጡ ተፈጥሯዊ ኬሚካሎች ምክንያት እንዲሁም ልጅ ከወለዱ በሗላ በሚመጣው የሀላፊነት ስሜት ምክንያት ድብርት ሊያጋጥም ይችላል።
- የአካል ጉዳተኞች እና ቤተሰቦቻቸው ለድብርት የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ ነው
የድባቴ ህመም ምልክቶች
የድብርት ምልክቶች ከሰው ወደ ሰው ሊለያዩ ይችላሉ ፣ ግን በብዙ ሰዎች ሊታዩ የሚችሉ የተለመዱ ምልክቶች አሉ፡፡
1.ሀዘን፣ጭንቀት ፣ ወይም ‘ባዶነት’ ስሜት
2. ተስፋ መቁረጥ/ጨለምተኝነት
3. ያልተገባ የጥፋተኝነት ስሜት ፣ጥቅም አልባነት ፣ረዳት አልባነት ስሜት
4 በፊት የሚወዱት እና የሚያስደስት ነገር ላይ ፍቅር መቀነስ ወይም መጥላት
5 ድካምና የሃይል ማነስ
6 የትኩረት ማነስ ወይም አለማስተዋል
7 የእንቅልፍ እጦት ወይም ከልክ በላይ ማንቀላፋት
8.የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና የክብደት ለውጥ
10. ስለ ሞት ወይም እራስን ስለ ማጥፋት ማሰብ ወይም ራስን ለማጥፋት መሞከር
11. ራስምታት ፣ ህመም ፣ ድካም ወይም ትክክለኛ የሆነ አካላዊ ምክንያት የሌለው ወይም በህክምና የማይድን የምግብ መንሸራሸር ችግር
መች ነዉ እርዳታ መጠየቅ ያለብን ?
ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች ቢያንስ ለሁለት ሳምንት ያክል እራስዎት ላይ ካዩ እርዳታ መጠየቅ ይኖርብዎታል። በማንኛውም ጊዜ እራስዎን የመጉዳት ወይም ራስን የማጥፋት ስሜት የሚሰማዎት ከሆነ በአስቸኩአይ እርዳታ ያግኙ ።
የት ነው እርዳታ መጠየቅ ያለብን ?
የሚቀርቡት እና ልያናግሩት የሚችሉት የ ቅርብ ጓደኛ ወይም ዘመድ ካለ እርዳታ ለማግኘት ለመጠየቅ አይፍሩ ; በቀጣይነት ግን ሁልጊዜም የ ስነ አእምሮ ሕክምና ባለሙያ እገዛ ማግኘት ይኖርብዎታል ።
የድባቴ ህመምን እንዴት መቋቋም ይቻላል
- መደበኛ የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግ ንቁ ለመሆን ይሞክሩ
- ከቤተሰብ / ጓደኞች ጋር ይገናኙ – መገለል ድብርትን ያባብሳል። ጊዜ ይፍጠሩ እና ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር ይገናኙ በአካል ካልተቻለ በስልክ ያግኙ። ከጓደኞችዎ ወይም ከቤተሰብዎ ጋር ጠንካራ ትስስር ይፍጠሩ።
- የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ይምረጡ – በጣም የሚወዱትን እና ስሜትዎን ሊያሻሽል የሚችል ነገር ለማድረግ ይጣሩ ለአብነት፦በተፈጥሮ ውስጥ የተወሰነ ጊዜ ያሳልፉ ፣ የቤት እንስሳትን ይንከባከቡ ፣ በጎ ፈቃድ ስራዎች ይስሩ ፣ ይደሰቱበት የነበሩትን የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ (ወይም አዲስ መዝናኛ) መርጠው በመተግበር ጭንቀትዎን ይቀንሱ። ከሚያምኑት ሰው ጋር በመሆን በመልመጃዎች ወይም በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎችዎ በመሳተፍ እና ደስ ሊያሰኝዎት በሚችሉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ ጭንቀትን መቀነስ ይችላሉ ፡፡
- በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ይሞክሩ – እንቅልፍ እና ስሜት በቅርብ የሚዛመዱ እንደመሆናቸው ጥሩ እና በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ይሞክሩ፡፡ በአልጋ ወይም ሌላው ቀርቶ በመኝታ ክፍልዎ ውስጥ ሥራ መሥራት ከመዝናናት ይልቅ አልጋዎን ከጭንቀት ጋር እንዲያዛምዱት ሊያደርግ ስለሚችል ለመተኛት ብቻ አልጋዎን ይጠቀሙ።
- በጣም ወሳኝ የሆኑ የህይወት ውሳኔዎችን እስኪሻልዎት ያራዝሙ
- ከባድ ስራዎችን ወደ ትናንሽና መስራት ወደሚችሉት መጠን ይከፋፍሉ ፣ ቅድሚያ መሰጠት ያለባቸው ስራዎች ይለዩ እና የሚችሉት ያክል ብቻ ይስሩ
- እራስዎን በእራስዎት በመጠጥ ወይም በባለሙያ ባልታዘዘ መድኃኒት ለማከም አይሞክሩ።
ዋቢ መጽሐፍ
David G.Myers, 2010, Psychology, 9th Ed. Diagnostic and statical manual of metal disorders , 5thEd G.E.Stelmach & P.A.Varoon, Advances in psychology 21, The self in Anxiety stress and depression , Edited by Ralf Schewazer
https://www.who.int/news-room/factssheets/detail/depression
ይሄ አስተማሪ የህክምና ፅሁፍ የቀረበው የጤና ወግ እና የ ኢትዮጵያ ሕክምና ተማሪዎች ማህበር ባዘጋጁት የህክምና ተማሪዎችን የመረጃ አስበሰብ እና ህብረተሰቡን የማስተማር አቅማቸውን ለማዳበር ለታለመ የበጎ ፍቃድ ውድድር ነው። እያንዳንዱ ፅሁፍ በ ጤና ወግ የታየ እና እርማት ተደርጎበት የቀረበ ነው ።