Written by- PINEAL ABEBE MITIKU (C-Ⅱ)
Reviewed by – ዶ/ር ቅድስት ገ/ፃዲቅ (የፅንስና ማህፀን ስፔሻሊስት ሃኪም)
የጉርምስና ዕድሜ ልጆች በአካላዊ እና ስነልቦናዊ ዑደት ወደ ወጣትነት የሚያድጉበት ጊዜ ነው። ሴቶች የጉርምስና እድሜ የሚጀምሩት በአማካኝ በ11አመት ሲሆን፣ ወንዶች ደግሞ በ12 አመት ነው። የጉርምስና ለውጦች ቁመት መጨመር፣ የሰውነት ስብጥር መለወጥ እና የመራቢያ አቅምን ማጎልበትን ያካትታሉ።
ለሴቶች የጉርምስና ወቅት ዋናው ምልክት የወር-አበባ መታየት ሲሆን ይህም በአማካይ ከ12 እስከ 13 አመት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚከሰት ነው። ለወንዶች የመጀመሪያው የዘር ፈሳሽ (spermarche) በአማካኝ በ13 አመታቸው ይከሰታል።
ስነ-ልቦና፣ ማህበራዊ አካባቢ፣ አመጋገብ እና አጠቃላይ የጤና ሁኔታ በጾታዊ ብስለት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አላቸው።
በጉርምስና እድሜ ላይ የሚታዩ ስነ- ልቦናዊ ለውጦች
በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በአካላዊ ገፅታ ላይ አስደናቂ ለውጦች ብቻ ሳይሆን፣ በስነ-ልቦና እና በማህበራዊ ተግባራት ላይ ፈጣን ለውጦች ይታያሉ።
በእነዚህ አመታት ውስጥ ታዳጊዎች በረቂቅ የማሰብ እና እቅድ አውጥተው የረጅም ጊዜ ግቦችን የማዘጋጀት ችሎታቸው ይጨምራል። በአጠቃላይ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ሊታዩ የሚችሉ አንዳንድ ችሎታዎች የሚከተሉት ናቸው ፦
– ረቂቅ የሆነ የማሰብ ችሎታን ያዳብራሉ
– በፍልስፍና ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ጉዳዬች ላይ የማሰብ ችሎታቸው ይጨምራል
– ራሳቸውን ከእኩዮቻቸው ጋር ያወዳድራሉ
የወላጆች እና የልጆች ግንኙነት
በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች በራሳቸው ውሳኔ ማድረግ የሚጀምሩበት ጊዜ በመሆን ይታወቃል። ይህም በአንጎል ውስጥ ባሉ የእድገት ለውጦች ምክንያት ይፈጠራል።
በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ በቤት የበለጠ ግላዊነት እና ከወላጆች ጋር ትንሽ ጊዜ የማሳለፍ አዝማሚያ ይታይባቸዋል። የወላጆችን ምክር እና ውሳኔ አሰጣጥን አለመቀበል ይጀምራሉ። ምንም እንኳን እነዚህ ባህሪያት ለቤተሰቦቻቸው እና ለወላጆች ተግዳሮት ሊፈጥር ቢችልም መደበኛ የስነ-ልቦና እድገት አካል ናቸው።
የወላጆች ድርሻ ምንድነው?
በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆችን እያጋጠሟቸው ስላሏቸው ለውጦች በግልጽ መናገር ለማንኛውም ወላጅ ፈታኝ ሊሆን ይችላል።
ሰውነታቸው እንዴት እንደሚለወጥ ማብራራት እና ወደፊት ምን እንደሚጠብቃቸው እንዲገነዘቡ መርዳት የልጅን ጭንቀት ሊያቃልል ይችላል። ከአካላዊ ለውጦች በተጨማሪ ወላጆች ስለ ስነ-ፆታ ጤንነት ከልጆች ጋር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ነው።
አካላዊ ለውጦች
የልጆች አካላዊ ለውጦች የጉርምስና ጅማሮ ምልክት ናቸው። እነዚህም ለውጦች የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ :-
– ፈጣን የቁመት መጨመር
– የብብት እና የብልት ፀጉር እድገት
– የቆዳ ለውጦች (ለምሳሌ, ብጉር)
ወንዶች ላይ የሚታዩ አካላዊ ለውጦች የድምፅ መጎርነን ፣ የፊት ፀጉር (ፂም) ማብቀል እንዲሁም የትከሻ መስፋት ይጨምራል። ሴቶች የጡት ማጎጥጎጥ ፣ የወር አበባ ማየት የዳሌ መስፋት እና የመሳሰሉ አካላዊ ለውጦችን ማየት ይጀምራሉ።
የአእምሮ ደህንነት
የጉርምስና ወቅት ለአእምሮ ደህንነት አስፈላጊ የሆኑ ማህበራዊ እና ስሜታዊ ልማዶችን ለማዳበር ወሳኝ ወቅት ነው።
በሆርሞን (Hormone) የሚመሩ አካላዊ ለውጦች እና ቀጣይነት ያለው የአዕምሮ እድገት የሚከሰቱት ከልጅነት ወደ አዋቂነት የሚደረገውን ሽግግር የሚያበረታቱ ማህበራዊ መዋቅሮች ሲፈጠሩ ነው።
በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ለተለያዩ አደጋዎች በተጋለጡ ቁጥር በአእምሮ ጤንነታቸው ላይ የሚኖረው ተፅእኖ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።
በጉርምስና ወቅት ለአእምሮ የጤና መቃወስ ከሚዳርጉ በርካታ ሁኔታዎች መካከል አሉታዊ የአቻ ግፊቶች ፣ የቤተሰብ ግጭት ፣ ጾታዊ ጥቃት እና የማንነት ጥያቄ ዋነኞቹ ናቸው።
በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤት እንዲሁም በሰፊው ማህበረሰብ ውስጥ የልጆች ጥቃት ተከላካይ እና አእምሮ ጤና ደህንነት ደጋፊ አካል ሊኖር ይገባል።