ትክክለኛ መርጃዎችን ብቻ እናጋራ! የተሳሳቱ መረጃዎችን ባለማካፈል ኃላፊነታችንን አንወጣ ።

እንደ ኮሮና ቫይረስ ያሉ ቶሎ ተዛማች በሽታዎች ሲፈጠሩ  በህብረተሰቡ ውስጥ መደናግጥን ይፈጥራሉ። የተዛቡ መረጃዎች ይበዛሉ። በተለይ በዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን በአንድ ቦታ የተነሳ የተሳሳተ መረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ቦታ ይዳረሳል ። አሁንም አያየነው ያለነው ነገር ይሄ ነው ።

በተለይ የህክምና ባለሙያዎች ፣ ታዋቂ ሰዎች ፣የሚዲያ ሰዎች፣  የመንግስት ባለስልጣናት ፣ በህዝቡ ዘንድ ተደማጭነት ስላላችሁ የምታጋሩት መረጃ ትክክለኛ መሆኑን ሁሌም አጣሩ። 

የጤና ወግ የሁልጊዜም አላማ በጥናት አና በ መረጃ የተደገፈ የህክምና ትምህርት ለህብርተሰቡ ማዳረስ አና የበኩላችንን አስተዋፆ ማድረግ ነው ። ስለዚህ ዛሬ  እስካሁን በብዛት በማህበራዊ ሚዲያ በስህተት አና ባለማወቅ በ ኮሮና ቫይረስ ዙሪያ አየተሰራጩ ያሉ የተዛቡ መረጃዎችን ለማስተካከል አንሞክራለን ። 

1) ነጭ ሽንኩርት መብላት የኮሮና ቫይረስ ኢንፌክሽንን  ለመከላከል ይረዳል የሚባለው አውነት ነው?

ነጭ ሽንኩርት አንዳንድ ፀረ-ተሕዋስያን ባህሪ ሊኖረው የሚችል ጤናማ ምግብ ነው ፡፡ ሆኖም ነጭ ሽንኩርት መብላት ሰዎችን ከኮሮና ቫይረስ  አይከላከልም ። ይሄን የሚደግፍ ምንም የህክማ ጥናት አስካሁን የለም ።  

2) በሞቃት እና እርጥበት አዘል የአየር ጠባይ ባለባቸው (Tropical Weather ) አካባቢዎች የ ኮሮና ቫይረስ ላይተላለፍ ይችላል የሚባለው አውነት ነው?

እስካሁን ካለው ማስረጃ ድረስ የ ኮሮና ቫይረስ በሙቅ እና እርጥበት አዘል የአየር ሁኔታ ያላቸውን አካባቢዎች ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች ሊተላለፍ ይችላል ፡፡ በ ቅርቡም በዜና አንዳየነው ኢትዮጵያን ጨምሮ በሞቃታማ የአየር ፀባይ ውስጥ ባሉ ሌሎችም የአፍሪካ አገራት በሽታው ተከስቷል ።  ከኮሮና ቫይረስ እራስዎን ለመከላከል በጣም ጥሩው መንገድ እጅዎን ደጋግሞ ማፅዳት ነው ፡፡ ይህንን በማድረግ በእጅዎ ላይ ሊኖሩ የሚችሉትን ቫይረሶች ያስወግዳሉ

3) የኮሮና ቫይረስ ኢንፌክሽን የዘር ልዩነቶች አሉ? የጥቁር ህዝቦችን አይዝም የሚለው አውነት ነው?

የጥቁር ህዝቦች  ልክ እንደ ሌሎች ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ይያዛሉ፡፡ በ ቅርቡም በዜና አንዳየነው ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎችም የአፍሪካ አገራት በሽታው ተከስቷል ። 

4)  አዲሱ የኮሮና ቫይረስ በዕድሜ የገፉ ሰዎችን  ብቻ ነው የሚያጠቃው የሚባለው አውነት ነው ወይስ ወጣቶችንም  ይይዛል ?

በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች በአዲሱ ኮሮና ቫይረስ (2019-nCoV) ሊጠቁ ይችላሉ። አዛውንቶችና ቀደም ሲል የጤና ችግሮች (እንደ አስም ፣ ስኳር ፣ የልብ ህመም) ያለባቸው ሰዎች የበለጠ ለበሽታው ተጋላጭ ሆነው ቢታዩም በሁሉም የአድሜ ክልል መከሰቱ አልቀረም። ወጣቶች አና ጥሩ ጤና ላይ ያሉ ሰዎች ብዙ የበሺታው ምልክት ሳይታይባቸው በሽታውን ሊያሰራጩ ስለሚችሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ።

5)  የኮሮና ቫይረስ  ኢንፌክሽንን ብዙ የሞቀ ውሃ በመጠጣት እና ኮምጣጤ በመጠጣት መከላከል ይቻላል ወይ ? 

አይቻልም። ቫይረሱን በሞቀ ውሀ ፣ በኮምጣጤ ወይም በጨው ማስወገድ አይቻልም ። ለጊዜው ያለው መፍትሄ ላለመያዝ ጥንቃቄ ማድረግ ብቻ ነው ።

✔ከታመም እና ምልክት ካለው ሰው ቢያንስ በ ሁለት ሜትር ርቀት ላይ መሆን

✔እጃችንን በደንብ መታጠብ

✔ሰው የተሰበሰበበት ቦታ ላይ አለመሆን

6) የኮሮና ቫይረስ ምንጩ እንስሳት ናቸው ይባላል ፣ የከብት ጥሬ ስጋ በመብላት ይተላለፋል?

የኮሮና ቫይረስ በእንስሳት ውስጥ የተለመዱ የቫይረስ ቤተሰቦች ናቸው ፡፡ 

አልፎ አልፎ ወደ ሰዎች ሲተላለፋ ከፍ ያለ ስርጭት እና በሽታ ያ ስከትላሉ። 

ለምሳሌ SARS -CoV ( ሳርስ) የ ሲቬት ድመት ዝርያዎች ውስጥ መነሻውን ሲያደርግ MERS – CoV ደግሞ በግመሎች ይተላለፍ እንደነበር ይታወቃል። 

ለአዲሱ COVID-19 አስተላላፊ ሊሆኑ የሚችሉ የእንስሳት ምንጮች ገና አልተረጋገጡም ፡፡ አንዳንድ ቅድመ ጥናቶች ፓንጎሊዮን እና የሌሊት ወፎች መነሻ ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ይጠቁማሉ። 

የአለም ጤና ጥበቃ ድርጅት እንደ አጠቃላይ ጥንቃቄ በማለት

የእንስሳት ገበያዎች በሚጎበኙበት ጊዜ እራስዎን እንዲጠብቁ ይመክራል። 

✔ከእንስሳት ጋር በሚገናኙበት ጊዜ ቀጥተኛ ንክኪ ያስወግዱ ፡፡ 

✔በማንኛውም ጊዜ ጥሩ የምግብ ደህንነት ልምዶችን ያረጋግጡ ፡፡ 

✔ጥሬ ስጋ ወይም ያለበሰሉ የእንስሳት ምግቦችን አይመገቡ። 

✔ ያልታሸጉ ምግቦችን , ጥሬ ወይም ያልበሰሉ እንስሳትን ምርቶች እንደ የጥሬ ሥጋ ፣ ወተት ወይም የእንስሳት አካሎችን በጥንቃቄ ይያዙ ፡፡

ስለዚህ አዎ ጥሬ ስጋ አይብሉ። 

  7) ቫይረሱ ከሰውነት ውጭ ምን ያህል ይቆያል ? የ በር እጀታ የመሳሰሉት ግእዝ ነገሮች ላይ ሊቆይ ይችላል?  

ቫይረሱ እንደ ፕላስቲክ ፣ የመታጠቢያ ገንዳ ላይ ፣ ግራናይት ላይ፣ ብረት ወይም መዳብ ባሉ ነገሮች ላይ ምን ያህል ረጅም ጊዜ መቆየት እንደሚቻል ገና ብዙ አይታወቅም ፡፡

 መጀመሪያ ላይ የወጡ ጥናቶች ለጥቂት ሰአታት ብቻ እንደሚቆይ ቢያሳዩም ከ ሁለት እስከ ሶስት ቀን ድረስ ሊቆይ እንደሚችል አዳዲስ ጥናቶች አሳይተዋል።

ስለዚህ በየቀኑ በተለያዩ ሰዎች ሲነካ የሚውልን ነገር ቶሎ ቶሎ እንዲያጸዱ ሲዲሲ (CDC) ይመክራል።

እነዚህም የበር እጀታዎች መጸዳጃ ቤቶች ፣ ስልኮች ፣ የታክሲ በር መክፋቻዎችን ይጨምራል።    

  8) ህፃናት በ አዲሱ ኮሮና ቫይረስ ይይዛሉ ወይ? ለሌሎችስ ሊያስተላልፉ ይችላሉ?

ህፃናት አንደ ከአዋቂዎች በ COVID-19 የመያዝ እድል አላቸው፡፡   እስካሁን ከታመሙት ውስጥ 2.4% ያህሉ ከ 18 አመት በታች ያሉ ሕፃናትሲሆኑ በፀና ከታመሙት ውስጥ 0.2% ህፃናት ናቸው። ከተያዙ በኋላ ግን የሚታይባቸውበሽታ ምልክቶች ቀለል ያሉ የጉንፋን ምልክቶች ብቻ የመሆን እድላቸው ከአዋቂዎች በላይ ነው፡፡ በCOVID-19 የመሞት እድላቸውም ከአዋቂዎች ያንሳል፡፡ ነገር ግን ቫይረሱን ተቀብለው ለሌሎች የቤተሰብ አባላት ያስተላልፋሉ፡፡ የተላለፈባቸው የቤተሰብ አባላት ደግሞ እድሜያቸው ከ60 አመት በላይ ከሆኑ ደግሞ በበሽታው የመጎዳት ወይም የመሞት እድላቸው በየትኛውም እድሜ ክልል ከሚገኙ ሰዎች ይጨምራል፡፡ ስለዚህም ህፃናትን COVID-19 እናዳይዛቸው ስንከላከል ቤተሰባችንንም እየጠበቅን መሆኑን በመረዳት “አይዛቸውም” ብለን አንዘናጋ፡፡      

9) የኮሮኔቫቫይረስ በሽታ የተያዙ ሰዎችን ለመመርመር በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ያሉ የሙቀት መመርመሪያዎች (thermal scanners)  ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?

በ ኮሮና ቫይረስ ኢንፌክሽን  ምክንያት ትኩሳትን ያዳበሩ ሰዎችን  ለመለየት የሙቀት ምርመራዎች ውጤታማ ናቸው ፡፡ ሆኖም በበሽታው ተይዘው አንደ ትኩሳት ያሉ ምልክቶችን ያላሳዩ ሰዎችን ኣይለይም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በበሽታው የተያዙ ሰዎች እስኪታመሙና ትኩሳት አስኪያሳዩ ድረስ ከ 2 እስከ 14 ቀናት ድረስ ስለሚወስድ ነው።             

10) ኮሮናቫይረስ ከማንኛውም በሽታ አምጪ በሽታ የበለጠ ገዳይ ነው?

የኮሮና ቫይረስ የሚያመጣው ከፍተኛ ህመም የሞት መጠን 2-3 በመቶ ነው ። በተለምዶ ፍሉ ወይም እንፍሉየንዛ ከምንለው ሌሎች በቫይረስ ከሚመጡ የመተንፈሻ አካላት ህመም አንፃር በጣም ከፍተኛ ነው። በ እንፍሉየንዛ ከታመሙ ሰዎች ውስጥ 0.1% ብቻ ለሞት ይዳረጋሉ።አንደ ኢቦላ ካሉ ለሎች በሽታ ኣምጪ ተዋስያን ኣንጻር ግን በጣም ኣነስተኛ ነው። ለምሳሌ ኢቦላ አስከ 90 በመቶ የተያዙ ስዎችን ሊገል ይችላል።       

  11 ) ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ፌጦ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብል፣ የጤና አዳም ፍሬ እና ሎሚ አንድ ላይ ወቅጣችሁ፣ በማር ብትጠቀሙ ትድናላቹ የሚባለው አውነት ነው ወይ ?

አንዚህ ከላይ የተዘረዘሩት በተለምዶ በ ቤት ውስጥ ለተለያዩ ህመሞች የምንጠቀማቸው ቅምሞች አና የ ቅጠል አይነቶች ለኮሮና ቫይርስ መድኃኒትነት አንደሚውሉ የሚያሳይ ምንም የህክምና ማስረጃ የለም። ለጊዜው ያለው መፍትሄ ላለመያዝ ጥንቃቄ ማድረግ ብቻ ነው ።

✔ከታመም እና ምልክት ካለው ሰው ቢያንስ በ ሁለት ሜትር ርቀት ላይ መሆን

✔እጃችንን በደንብ መታጠብ

✔ሰው የተሰበሰበበት ቦታ ላይ አለመሆን

በቀጣይነት ሌሎች መረጃ ሲያጋጥማቹ ሁልጊዜም ትክክለኛ መሆኑን ለማጣራት ሞክሩ ።

የጤና ወግ የሚከተሉትን መረጃ የማረጋግጥ ምክሮች ትጠቁማለች

  1. መረጃዎን ከ ታመነ መንጭ ብቻ ይከታተሉ።  በዚህ በኮሮና ቫይርስ ዙሪያ ሁሉም ሰው የራሱን ሃሳብ ሊፅፍ ይችላል አርስዎ ግን ከጤና ጥበቃ አና ከተመረጡ ትክክለኛ ምንጮች ብቻ ዜናዎን ያግኙ
  2. ለሌሎች የሚያጋሩትን መረጃ ከመላክዎ በፊት አውነታኛነቱን ያረጋግጡ ።
  3. ከብዙ ያልተረጋገጠ ዜና  ይልቅ የሚያምኑት ጥቂት ተዓማኒ የመረጃ ምንጭ ይበቃዎታል ።
  4. ሰበር ዜና ማካፈልን ልምድ ላለችው ጋዜጠኞች ይተዉ ።

ሁሌም ጥያቄ ካላቹ አድርሱን። ምንም ነገር ያለ ጥናት አና ማስረጃ አናጋራችሁም ። አላማችን በህክምና ትምህርት ውስጥ መረጃ የመጠቀም ባህልን ማዳበር ነው ።