በዶ/ር ሄኖክ ደሴ ውብነህ (የስነ-አእምሮ ሪዚደንት ሐኪም)

 

መግቢያ

ጭንቀት በዋነኛነት የወደፊቱን ነገር ካለማወቃችን ጋር ተያይዞ ምን ይፈጠር ይሆን? ብለን የምናስበው  እና የተበታተኑ ሀሳቦች የሚመላለሱበት ግልጽ ያልሆኑ ስሜቶች የሚስተናገዱበት የታፈነ ስሜት ነው::

የጭንቀት ህመም ዓይነቶች ወይም መገለጫዎች

የጭንቀት ህመም የብዙ ህመም ስብጥር ነው። ምንም  እንኳን ቀጥተኛ እና አቻ ትርጉሞች ባይሆኑም ከብዙ በጥቂቱ ለመግለጽ ያክል፦

የጥቅል (አጠቃላይ) ጭንቀት (Generalized anxiety disorder) ቢያንስ ለ 6 ወራት ያህል  በሁሉም ጉዳይ በሚባል ደረጃ ጭንቀትን መቋቋም አለመቻል በአብዛኛዎቹ ቀናት የሚያሳይ ከሆነ እና ምልክቶቹ በዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ከሆነ እና ምልክቶቹ ሌላ መንስኤ እንደሌላቸው በምርመራ ከተረጋገጠ  የጥቅል (የአጠቃላይ) ጭንቀት ሊሆን ይችላል።

በተጨማሪም

ድንገተኛ መሸበር (Panic disorder)፦ ይህ የአእምሮ የጤና እክል ከነበርንበት የስሜት ደረጃ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የሚፈጠር ድንገቴ እና ቅጽበታዊ የሆነ ከፍ ያለ ፍራቻ ነው። ከፍርሃቱ በተጓዳኝ አብረው ሊኖሩ የሚችሉትን ምልክቶች የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል የልብ በከፍተኛ ሁኔታ በፍጥነት መምታት፣ ላብ በላብ መሆን፣ ትንፋሽ ማጠር፣ ራስን ለመሳት መሞከር ወይም እስታለሁ በማለት በፍርሃት ውስጥ መዋጥ ናቸው።

ልዩ ፍራቻ (Specific phobia) በሕይወት አጋጣሚ በቂ ምክንያት ሳይኖረን አንዳንድ

ነገሮችን እንፈራለን። ፎብያ ማለት ግን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እስኪታወክ ድረስ እና የዕለት ከዕለት ስራችን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በሚያደርስ መልኩ መፍራት ይታይባቸውል። ልዩ ፍራቻዎቹ እንደየሰው የሚለያዩ ሲሆን ከእነዚያ ውስጥ የሚከተሉትን ያካትታል።

ለምሳሌ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።

  • ከፍ ያለ ቦታ
  • የተዘጋ/የተጣበበ ቦታ
  • የተለያዩ እንስሳትን መፍራት እና ሌሎችም ናቸው። እነዚህ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በጭንቀት ና በፍርሃት ውስጥ ይገባሉ በተጨማሪም የሚያስፈራቸው ሁኔታ ላይ ለመውጣት ማናቸውንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም።
  • የማህበራዊ ፍራቻ እና ጭንቀት (Social Anxiety Disorder) ፦ ይህ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ግምገማ ያለባቸውን ማኅበራዊ መድረኮች በመፍራት ከማኅበራዊ እንቅስቃሴ መታቀብ፣ ለመሳተፍ መቸገር ይስተዋልባቸዋል። ለምሳሌ በአደባባይ ንግግር ማድረግ መፍራት፣ በቃል የሚቀርቡ ገለጻዎችን መሸሽ፣ አዲስ ሰው ለማውራት መቸገር፣ እንዲሁም ከሌላ ሰው ጋር ለመመገብ እስከ መፍራት የደረሰ ትልቅ የእፍረት ስሜት ሊኖራቸው ይችላል።
  • በስተመጨረሻም የጭንቀት ህመም ሌሎች አይነቶች እንዳሉትም መዘንጋት አይገባም

ስርጭቱስ ምን ያክል ነው?

በአለም ላይ ካሉ 4 ሰዎች ከጭንቀት ህመም አንዱ በህይወት ዘመናቸው የሚያጋጥማቸው ሲሆን እንደ አጠቃላይ አሜሪካን ሀገር በተሰራ ጥናት 17.7% አመታዊ ስርጭት አለው። የጭንቀት ህመም አብዛኛውን ጊዜ መካከለኛ ዕድሜ ላይ ያሉትን ሰዎች የሚያጠቃ ሲሆን፤ በፆታ ካየነው ደግሞ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ላይ በሁለት እጥፍ የመከስት እድል አለው።

መንስኤው ምንድን ነው?

ትክክለኛ መንሥኤው ባይታወቅም የሚከተሉት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡

  • የዘረ መል መዋቅር እና የአንጎል ኬሚካላዊ አሰራር (አእምሮችን መልእክት የሚቀበልበት እና የሚልክባቸው ንጥረ-ነገሮች)
  • አካባቢያዊ ተፅዕኖዎች (ጦርነት፣ መፈናቀል እና ሌሎችም)
  • እንደ ሰው ያለን ሥነ-ልቦናዊ ውቅር

ለዚህ ህመም መከሠት የራሳቸውን አስተዋፅዖ ያደርጋሉ ተብሎ ይታመናል።

  • በተጨማሪም የውስጥ ደዌ ህመም እንደ መንስኤ ሊጠቀስ ወይም በተጓዳኝ የመከሰት ዕድል እና በፊት ህመሙ ከነበረባቸው ሊያባብሰው ይችላል ።

ምልክቶቹ ምን ምን ናቸው?

እንደየ የጭንቀት ህመም አይነቶቹ ምልክቶቹ ይለያያሉ።

ከዚህ የአእምሮ ህመም ጋር ተያይዞ አብረው የሚመጡትን አካላዊ ምልክቶች ጠቅለል አድርገን ብንመለከት፦

¤ ከመጠን ያለፈ እና የማያቋርጥ ባልተጨበጠ ነገር ላይ ከልክ በላይ ጭንቀት ወይም ውጥረት

¤ በጣም መድከምና እረፍት ማጣት፣ መቁነጥነጥ

¤ ከሀሳብ ብዛት የተነሳ እንቅልፍ ማጣት፣ መነጫነጭ (ከበፊቱ ባልተለመደ ሁኔታ ብስጩ መሆን)

¤ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ዋነኞቹ ምልክቶች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ የጭንቀት ህመም

  • የልብ ምት መፍጠን እና የትንፋሽ መፍጠን
  • መንቀጥቀጥ
  • ራስ ምታት እና ላብ
  • ራስን ሊስቱ እንደሆነ ማሰብና እንዳንዴም ራስን መሳት ይስተዋላሉ።

የበሽታው ምልክቶች የመምጣትና የመሔድ ባሕርይ አላቸው። በተጨማሪም እንደ ድባቴ ካለ የአእምሮ ሕመም ጋር አብሮ የመከሠት ዕድሉ የሰፋ ነው። የሁለቱ ህመሞች ጥምረት ደግሞ ብዙ ጊዜ ታማሚዎችን እራሳቸውን ወደ ማጥፋት ሊያመራቸው ይችላል። እንዲሁም  ለአደንዛዥ ዕፅ ወይም ለአልኮሆል መጠጥ ችግሮች የተጋለጡ ሊሆኑ ይችላሉ።

 

እንዴት ይታከማል?                                                                                                                                                                      

ይህንን ህመም በሁለት አይነት መልኩ ማከም የሚቻል ሲሆን

  1. የመጀመሪያው በግርድፍ አማርኛ ስንተረጉመው  የንግግር  ሕክምና (Psychotherapy) በመጠቀም ሊታከም  ይችላል። በጣም ብዙ አይነት የንግግር ህክምና አማራጮች ሲኖሩ እንደ ህመሙ አይነት አማራጮችን ልንጠቀም እንችላለን። የንግግር ህክምናው   በግል ወይም በቡድን ሊሰጥ ይችላል።
  2. ሁለተኛው ደግሞ በሚዋጡ መድሃኒቶች የሚደረግ ህክምና ነው። ሀገራችን ውስጥ ብዙ አይነት የመድሃኒት ህክምና አማራጮች ሲኖሩ፣ የታካሚውን ሁኔታ ማለትም  እድሜ ፣ተጓዳኝ ህመም  እና ሌሎች ነገሮች ታሳቢ  አድርገን እንመርጣለን። የመድሃኒት ህክምናው እንደ አጠቃላይ ውጤታማ የህክምና አማራጭ ነው።

¤  አንድ ሰው ለጭንቀት ህክምና ሁለቱንም የህክምና አማራጮች በአንድ ላይ ቢወስድ  ማለትም  በመድሃኒት ወይም በንግግር ብቻ ከመታከም የተሻለ እንደሆነ ይታመናል።

በመጨረሻም ከላይ የተዘረዘሩ ምልክቶች ከታዩ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ እና በማማከር የጭንቀት ህመም ምርመራ እና ሌሎች ተያያዥ ህመሞችን ለመለየት በባለሞያዎች ተጨማሪ ምርመራዎችን በማድረግ  የሚለይ እና የሚታከም መሆኑን ሊያውቁ ይገባል።

 

 

ቁልፍ ቃላት፤ ጭንቀት  የአእምሮ ጤና

 

ዋቢዎች

  1. Kaplan & Sadock’s Synopsis of Psychiatry, 12th Edition
  2. Diagnostic and Statistical Manual of Mental Disorders,5th Edition:DSM-5
  3. Kessler, R. C., Chiu, W. T., Demler, O., & Walters, E. E. (2005). Prevalence, Severity, and Comorbidity of 12-Month DSM-IV Disorders in the National Comorbidity Survey Replication. Archives of General Psychiatry, 62(6), 617-627.