በዶ/ር አጋዠ መላኩ (በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ሬዚደንት ሃኪም)

Reviewed by ዶ/ር  ሙሉጌታ ካሳሁን (Surgeon)\

 

የጭንቅላት እጢ ምንድን ነው?

የጭንቅላት እጢ የአንጎል ህዋሳት ወይም ከሱ ጋር የተያያዙ ህዋሳት ጤናማ ባልሆነ መንገድ ሲባዙ የመከሰት ሲሆን ብዙ አይነት የጭንቅላት እጢዎች አሉ። አንዳንዶቹ በአጭር ጊዜ የሚራቡ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ቀስ በቀስ ይባዛሉ። በጊዜ ሂደትም ወደጤናማው የአንጎል ክፍል በመዛመት በሽታውን ከባድ ሊያደርጉት ይችላሉ። እነዚህ በፍጥነት የሚባዙ ጤናማ ያልሆኑ የአንጎል ህዋሳት በፍጥነት በሚባዙበት ጊዜ በአጥንት ውስጥ የተሸፈነውንና መለጠጥ የማይችለውን አንጎላችንን እንዲያብጥ በማድረግ የተለያዩ የበሽታውን ምልክቶች እንዲኖሩ ያደርጋል። የጭንቅላት እጢ የሚከሰትበት የአንጎል ክፍል የተለያየ ሲሆን በህጻናት ልይ ብዙውን ጊዜ በታችኛው የአንጎል ክፍል የሚከሰት ሲሆን በአዋቂዎች ደግሞ ብዙውን ጊዜ በላይኛው የአንጎል ክፍል ላይ ይከሰታል። የጭንቅላት እጢ ከደም ካንሰር ቀጥሎ ህጻናትን የሚያጠቃ የእጢ አይነት ነው።የጭንቅላት ዕጢዎች ከነርቭ ፣ ከደም ስር ፣ ከጭንቅላት ሽፋን ፣ ወይም አጥንት ሊነሳ የሚችል  ሲሆን  ከሌላ የሰዉነት  ክፍልም, ለምሳሌ ከጡት ካንሰር ሊዛመት ይችላል ::

የጭንቅላት እጢ ምልክቶች ምን ምን ናቸው?

የጭንቅላት እጢ ምልክቶች እጢው እንዳለበት ቦታ የተለያየ ሲሆን ዋና ዋና ምልክቶችም ከፍተኛ የሆነ የእራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽና ማስታዎክ፣ የሰውነት ሚዛንን መጠበቅ ያለመቻል፣ የአይን ብዥ ማለት እንደሁም ማንቀጥቀጥ(seizure) እና የተወሰነ የአካል ክፍል መስነፍን ሊአመጣ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ምንም ምልክት ላያሳይ ይችላል።

 

መቼ ወደ ህክምና ቦታ መሄድ ያስፈልጋል?

የጭንቅላት እጢ ምልክቶች ከሌሎች የበሽታ አይነቶች ምልክቶች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላል፡ ስለሆነም ህመምተኞች ከዚህ በታች የተዘረዘሩት  ምልክቶች ሲኖሩ በቶሎ በአቅራቢ ወደሚገኝ የጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል፡ሳይዘገዩ ወደ ህክምና ተቆም ሂዶ መመርመር አና መከታተል የመዳን ተስፋን ይጭምራል  ::

  • በራስ ህመም ማስታገሻ የማይቆም ከፍተኛ የሆነ ራስ ህመም
  • ተከታታይ የሆነ ማዞርና ማስታዎክ፣ በተለይም ጠዋት ጠዋት የሚከሰት ውይም ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስ ከሆነ
  • የተዎሰነ የአካል ክፍል መስነፍ(paresis) የሚኖር ከሆነ
  • ማንቀጥቀጥ እና እራስን አለማዎቅ ወይም እራስን መሳት ካለ(seizure and confusion)
  • ከራስ ህመም ጋር የተያያዘ የእይታ ብዥ ማለት(blurring of vision ) ካለ

የጭንቅላት እጢ እንዴት መመርመር ይቻላል?

የጭንቅላት እጢ ምልክቶች በሚኖርበት ጊዜ የህክምና ባለሙያዎች ትክክለኛ ምክንያቱን ለማረጋገጥ ምርመራዎችን ያዝዛሉ። በአሁኑ ጊዜ CT SCAN እና MRI የተባሉ የጭንቅላት እጢ መመርመርያ መሳሪያዎች በስፋት አገልግሎት ላይ ይውላሉ። በእነዚህ ምርመራዎች የጭኝቅላት እጢን የሚያመላክቱ ግኝቶች ሲኖሩ የእጢውን አይነት ለመለየት ከእጢው ላይ የሚዎሰድ ናሙና(biopsy) ሊያስፈልግ ይችላል።

 

የጭንቅላት እጢ እንዴት ይታከማል?

የጭንቅላት እጢ የተለያዩ የህክምና አይነቶች ሲኖሩት ይህም በታካሚውና የህክምና ባለሙያዎች የጋር ምክክርና የእጢውን አይነት፣ የህመም ደረጃና የህክምና አማራጮችን የካተተ ይሆናል። የህክምና አማራጮችም የቀዶ ህክምና(surgery)፣ የጨረራ ህክምና(radiation therapy) እና ኪሞቴራፒ(chemotherapy) ሊሆኑ ይችላሉ። እንደ እጢው ደረጃ አንደኛውን ውይም ሁሉንም አማራጮች ያካተተ ህክምና ሊሰጥ ይችላል።