በዶክተር ሜሮን ሀሰን

የህፃናት ህክምና እስፔሻሊስት

By Dr. Meiron Hassen, MD

Pediatrics and child health specialist

 

 

ጉድ በል ሃበሻ የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው !

የአስራ ሶስት ወር ፀሀይ ያላት ሃገራችን ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ልጆቻችን በአግባቡ ፀሀይ እንደማይሞቁ ጥናቶች አመላክተዋል። በአዲስ አበባ ጭራሽ 67 በመቶ ይደርሳሉ።

 

ምክንያቱ በዋናነት በቂ እውቀት ማጣት ሲሆን ጎጂ እምነቶች እንዲሁም የአኗኗር ሁኔታ አለመመቸት ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸው ተደርሶበታል። በዚህም ምክንያት ህፃናት 80 በመቶ የሚሆነውን ቫይታሚን ዲ የሚያገኙበትን ምንጭ ያሳጣቸዋል።

 

ቫይታሚን ዲ በሰውነታችን ውስጥ ካልሽየም እንዲሁም ፎስፌት ከተባሉ ንጥረ ነገሮች አጥንት እንዲሰራ ፣ እንዲያድግ እንዲሁም እንዲጠነክር የሚረዳ አስፈላጊ ደቃቅ ንጥረነገር ነው። በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ህፃናት ይህንን ንጥረነገር በበቂ ሁኔታ ካላገኙ ለአጥንት መሳሳትና ከሱ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ መዘዞች ይዳረጋሉ።

 

ምልክቶቹም የእድገት ማዝገም፣ የግንባር መፍጠጥ፣ የጀርባ እንዲሁም የጎን አጥንቶች መጣመም፣ የአጥንት አንጓዎች መስፋት፣ የእግር አጥንት መጣመም፣ የበሽታ መከላከል እቅም ማነስ፣ የካልሽም ማነስና ተያይዞ የሚመጣ መንቀጥቀጥ እስከ ትንፋሽ ቧንቧ መታፈን እና ሞት ሊያደርስ ይችላል።

 

 

መፍትሄው

ፀሀይ በአግባቡ ማሞቅ!

ከ15ኛ ቀን እድሜ ጀምሮ ልጆች ተንቀሳቅሰው ፀሀይ እስከሚያገኙበት ጊዜ ድረስ በቀን ለ 15 – 30 ደቂቃ ያህል ቀጥተኛ የጠዋት ፀሀይ እንዲያገኙ ማድረግ።

ይሄንንም ልጆች ተንቀሳቅሰው የፀሃይ ብርሃን እስኪያገኙ መቀጠል።

ቤተሰብን ይሄን እንዲያደርግ መምከርና ማገዝ።

የበሽታው ምልክቶች ካሉ ህክምና በአፋጣኝ እንዲያገኙ ማድረግ ።

 

ስህተቶች ፡

ፀሃይዋን በቀጥታ ቆዳ እንዳያገኘው ማድረግ (መጋረድ)

ቅባት አንዳንዴም ቅቤ ወይም ቫዝሊን ቀብቶ ወይንም እየቀቡ ማሞቅ

በመስኮት መስታወት የሚገባ ፀሀይ ማሞቅ።

ልብስ አልብሶ ማሞቅ (ከአይንና ፀጉር ውጭ መሸፈን)

ለረጅም ጊዜ ፀሀይ በማይወጣበት ወራት ቫይታሚን ዲ አለመውሰድ ወዘተ

የአጥንት መሳሳት (rickets) ምልክቶች ያሉበት ህፃን የራጅ እና ደም ምርመራ አድርጎ ከተረጋገጠ በኃላ በመርፌ የሚሰጥ ቫይታሚን ዲ እንዲሁም የሚጠጣ ካልሲዬም ይሰጠዋል። ክትትልም ይደረግለታል። ይህም በአለም አቀፍ ጥናቶች እንደታየው ለ25% አለም አቀፍ የህክምና ወጪ ምክንያት እንደሆነ ተመዝግቧል።

እና ይሄ የአባይን መገደብ ከጨረስን ፀሀያችንን ደግሞ እንገድብ አያሰኝም?

 

አንድን ህፃን ማሳደግ መንደር ሙሉ ሰው ርብርብ ያስፈልጋል። ስለ ህፃናት የአጥንት ጤንነት ይህን ካወቁ ያሳውቁ ፣ የማህበረሰባዊ ግዴታዎን ይወጡ!

 

የጤና ወግ

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ

ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg