ዶክተር ኪሩቤል ምስጋናው(ጠቅላላ ሀኪም)

Dr. Kirubel Misganaw(General practitioner)

Reviewed/Approved by: Dr. Yared Zenebe (Neurologist)

 

የፓርኪንሰንስ ህመም ከእድሜ መግፋት ጋር የሚያያዝ እና በጊዜ ሂደት ውስጥ እየባሰ የሚሄድ የነርቭ ህመም ነው። ህዋሶችን በተለይም ዶፓሚን የተባለውን ንጥረ ቅመም የሚያመነጩትን ነርቮች በመግደልና ቁጥራቸውን በማመናመን የነርቭ ህመምን ያመጣል።

 

ዋና ዋና የህመሙ መገለጫዎች፡- 

ሰውነታችን ባረፈበት ጊዜ የጣት፣ የእጅ ወይም የአገጭ መንቀጥቀጥ

ሰውነትን ለማንቀሳቀስ መቸገርና መግረር

የሰውነት እንቅስቃሴ አዝጋሚና የተንቀራፈፈ መሆን

የሰውነትን ሚዛን ለመጠበቅ መቸገር

የአረማመድ መዛነፍ እና ደጋግሞ መውደር

ከእነዚህም በተጨማሪ ጮክ ብሎ ንግግር ለማድረግ መቸገር ፣ ለመዋጥ መቸገርና የለሃጭ መዝረብረብ እንዲሁም በእርምጃ ጊዜ በድንገት ድርቅ ማለት ወይም መራመድ ፈልጎ እግርን ለማንሳት መቸገር የፓርኪንሰንስ ህመም ምልክቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰውነትን ከማንቀሳቀስ ጋር የተገናኙ ምልክቶች (በእንግሊዘኛውም Motor Symptoms) በመባል ሲታወቁ በተቃራኒው ሰውነትን ከማንቀሳቀስ ጋር ግንኙነት የሌላቸው (በእንግሊዘኛውም Non-Motor Symptoms) የምንላቸው የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

ከተቀመጥንበት ወይም ከተኛንበት ቦታ ላይ ቶሎ ብለን በምንነሳበት ጊዜ የሚከሰት ቅፅበታዊ የደም ግፊት መቀነስና ተያይዞም የማዞርና የመውደቅ ስሜት

የጨጓራ እና አንጀት እንቅስቃሴ መቀነስና የምግብ በቶሎ አለመፈጨት

የሆድ ድርቀት

ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት ፣ ለመውጣት መቸገርና ማምለጥ

በወሲብ ወቅት የወንድ ብልት ለመቆም መቸገር

የእንቅልፍ ችግር (መቃዥት ፣ ቀን ቀን አብዝቶ ማንቀላፋት ፣ ማታ ቶሎ ለመተኛት መቸገርና ቶሎ ቶሎ መንቃት)

የማሰብ ፣ ማሰላሰልና ማስታወስ ችግሮች

የስሜት (ሙድ) መለዋወጥና መረበሽ

የትኩረት ማጣት እና አንድን ተግባር ጀምሮ ለመፈፀም መቸገር

ሰውነት ላይ ያለ ህመም (እንደ የጀርባና የእግር ህመሞች)

የእግር ማበጥ የመሳሰሉ ችግሮች ተጠቃሾች ናቸው።

 

በአለም አቀፋ ደረጃ ከዚህ በሽታ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እስከ 5 ሚሊዮን ገደማ እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ በኢትዮጽያ ውስጥም ጥናታዊ ግምቶች እንደሚያሳዩት ከፓርኪንሰን ህመም ጋር የሚኖሩ ሰዎች ብዛት ከ100,000 እንደሚበልጥ ይገመታል። ነገር ግን ህመሙ ታውቆላቸው ህክምና የሚያገኙ ሰዎች ቁጥር እጅግ በጣም አናሳ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

 

የፓርኪንሰንስ ህመም በምን ምክንያት ይከሰታል? ተጋላጭ የሆኑትስ እነማን ናቸው?

የፓርኪንሰንስ ህመም የሚከሰትበት እርግጠኛ ምክንያት ተለይቶ ባይታወቅም በዘረመል (gene) እና አካባቢያዊ መንስኤዎች መካከል ያለ ቁርኝት ለበሽታው መከሰት ምልክት እንደሆነ በጥናት ተረጋግጧል። ይህ መስተጋብርም የህመሙ መሰረት የሆነውን አልፋ ሲኒኩሊን (a synichulin) የተባለ በአድ ፕሮቲን ዶፓሚን (Dopamine) የተባለውን ንጥረ ነገር በሚያመርቱ የነርቭ ህዋሳት ውስጥ ሲከማችና ሲገድላቸው የሚከሰት ህመም ነው።

ስለ ዶፓሚን በአጭሩ ለማብራራት ያህል ፤ ዶፓሚን ማለት በአንጎላችን ውስጥ ባሉ ነርቮች የሚመነጭ ኬሚካል ሲሆን በቀዳሚነት የሚጠቀስበት ተግባር ደስታን ከማግኘት እና ስሜታችንን(ሙድ) መቆጣጠሩ ላይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዶፓሚን ከሰውነት እንቅስቃሴ፣ ከትኩረት፣ ከግንዛቤ፣ ከትዝታ፣ ከባህሪ፣ ከመማር ችሎታ እንዲሁም ከእንቅልፍ እና ንቃት ጋር በተያያዘ ትልቅ ሚና የሚጫወት የነርቭ ህዋሶችን ከራሱ ከአምሮአችን እና ከተቀረው የሰውነት ክፍላችን ጋር የሚያስተሳስር ወሳኝ መልዕክተኛ ኬሚካል ነው፡፡ ለዚህም ነው የፓርኪንሰንስ ህመም ተጠቂዎች ላይ በብዛት የሚታዩት የአካልና (motor) እና አካላዊ ያልሆኑ (Non-motor) ምልክቶች ይህንን የሚያመላክቱት፡፡

ለዚህ በሽታ በብዛት ተጋላጭ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ60 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች ሲሆኑ በ20ዎቹ እንዲሁም ከዚህም ባነሰ እድሜ ላይ ባሉ ግለሰቦችም ላይ ህመሙ የመከሰት እድል አለው፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ የሚፈጠረው ህመሙ በቤተሰብ ውስጥ ካለና ከዘረማል (ጂን) ጋር የተያያዘ ሲሆን ነው፡፡ ፓርኪንሰንስ በጥቂቱም ቢሆን በወንዶች ላይ ጎላ ብሎ የመከሰት እድል አለው፡፡ አካባቢያዊ መንስኤዎች ስንል ደግሞ የተለያዩ አይነት ፀረ-አረም እና ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች መጋለጥ ፤ የጭንቅላት ጉዳት ወይም ለአየር ብክለት ተጋላጭ መሆን ናቸው፡፡

 

ፓርኪንሰንስ በቤተሰባዊ የጅን ውርርስ ወይም በዘር የሚወረስ በሽታ ነውን? 

እስከ 10% የሚሆነው የፓርኪንሰንስ ህመም የሚከሰተው በዘረመል አማካኝነት ከቤተሰብ በሚወረስ ችግር ሲሆን ከ90% በላይ የሚሆነው ግን በዘፈቀደ ወይም ግልጽ ባልሆነ ምክንያት የሚከሰት እና ይህ ነው የሚባል ከቤተሰብ የዘር ሀረግ ጋር ቁርኝት የሌለው በሽታ ነው፡፡

 

የፓርኪንሰንስን ህመም ህክምና (Diagnosis) ምን ይመስላል?

የፓርኪንሰንስ ህመምን ለመለየት የሚረዱ ቀጥተኛ የምርመራ መንገዶች በሙከራ ላይ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ አንድ ሰው የፓርኪንሰንስ ህመም ተጠቂ መሆኑን በህክምና ለማወቅ ሀኪሙ ከታማሚው ዝርዝር የህመሙን ታሪክ በመጠየቅና በአካሉ ላይ የሚታዩ የህመም ምልክቶችን በመለየት ህመሙ መኖሩን መለየት ይችላል፡፡

ስለዚህ አንድ ግለሰብ ይህ ህመም እንዳለበት ከተጠረጠረም ሆነ ከተወሰነ በዚህ ህመም ላይ የበለጠ እውቀት ወዳላቸው ስፔሻሊስት የነርቭ ሀኪሞች (Movement disorder Neurologist) መላክ አስፈላጊ ነው፡፡

ከፓርኪሰንስ ህመም ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ የጤና ችግሮች (complications)፡-

የአነጋገር ችግር

የማኘክ እና የመዋጥ ችግር

ድባቴ እና ጭንቀት

የመርሳት ችግር

የሆድ ድርቀት

ከሽንት ቧንቧ ጋር የተያያዙ ችግሮች

ወሲብ ከመፈፀም ጋር የተያያዙ ችግሮች በዋነኝነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

 

የፓርኪንሰንስን ህመምን ማከም ወይም መቆጣጠር ይቻላል? 

ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ የፓርኪንሰን ህመም ፈውስ ያልተገኘለት በሽታ ቢሆንም የህመሙ ምልክቶችን ለመቆጣጠር የተለያዩ የህክምና አማራጮች አሉን። እነዚህም በሶስት ዋና ዋና ክፍል ይካተታሉ

  • ከመድሀኒት ውጭ የሆነ ህክምና
  • የመድሃኒት ህክምና እና
  • የቀዶ ጥገና ህክምና

ከመድሀኒት ውጭ የሆነ ህክምና፡ በዚህ ውስጥ የሚካተቱት የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በዘላቂነት መስራት ፣ የሰውነትን ሚዛን የሚያሻሽሉ ስፓርቶች ላይ መሳተፍ ፣ አእምሮን የሚያነቃቁ ጨዋታዎችን መጫወት

የመድሃኒት ህክምና፡ የህክምናው ምሰሶ የሆነው ሌቮ ዶፓ (levodopa) የሚባለው መድሃኒት ሲሆን የሚወሰደውም በሀኪም ትዕዛዝና ክትትል መሰረት በዘላቂነት የሚወሰድና የህመሙን ምልክት ለመቆጣጠር በዋናነት ይጠቅማል፡፡

ከሌቮ ዶፓ (levodopa) በተጨማሪ ሌሎች የመድሃኒት አማራጭ ህክምናዎች ይታዘዛሉ።

የህመሙን ምልክቶች ከመድሃኒት ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሲሆን እንደ አማራጭ የቀዶ ጥገና ህክምና ይሰጣል።

የቀዶ ጥገና ህክምና፡ የሰውነት መንቀጥቀጥ ፣ አካልን ለማዘዝ አለመቻልና ከመድሀኒት ጋር የተያያዘ አላስፈላጊ የሰውነት መንቀሳቀስ ችግሮችን በመድሀኒት ለማከም በማይችልበት ጊዜ እንደ አማራጭ በጭንቅላት ውስጥ የሚቀበር የኤሌክትሪክ መሳርያ (Deep Brain Stimulation/DBS) በማስገባት ማከም ይቻላል።

በአንጀት በኩል የሚቀበር ዱኦ ዶፓ

(DuoDopa) የሚባሉት የመድሀኒት መስጫ አማራጮች አሉ፡፡

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg