በዶ/ር ተስፋዬ ብርሃኑ(ጠቅላላ ሐኪም- ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መምህር)

Reviewed/Approved by: Alemayehu Woldeyes,MD,MSc(Consultant ophthalmologist)

   መግቢያ 
ግላኮማ ለዓለማችን ዓይነ ስውርነት ከዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀጥሎ መንስኤ ሲሆን ሊቀለበስ/ሊስተካከል ለማይችል ዓይነ ስውርነት ደግሞ ግንባር ቀደም ምክንያት ነው።
.. 2021 . በተጠኑ ጥናቶች መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 253 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የማየት እክል ያለባቸው ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ 36 ሚሊዮን ሰዎች ማየት የተሳናቸው ናቸው። በግምት 89% የሚሆኑት ማየት የተሳናቸው ሰዎች (ዝቅተኛ እይታ እና ዓይነ ስውርነት) በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉት ይገኛሉ። 
በኢትዮጵያም ወደ 5.4 ሚሊዮን የሚጠጋው ማለትም 123 ሚሊዮን ሕዝብ 1.6 በመቶው ዓይነ ስውርነት እና 3.7 በመቶው ደግሞ ዝቅተኛ የማየት ችግር አለበት። ከዚህ ውስጥ 87.4% በላይ የሚሆነውን የዓይን እክል ሳይከሰት በፊት ቀድሞ መከላከል የሚቻል ነው። የዓይን ሞራ ግርዶሽ(Cataract)  ትራኮማ (Trachoma) የብሌን ጠባሳ (Corneal opacity) በመነጽር የሚስተካከል የዕይታ ችግር (Refractive errors) እና ግላኮማ ዋነኛ የዓይነ ስውርነት መንስኤዎች መሆናቸውን ጥናቶች ይጠቁማሉ። 

 

ግላኮማ ምንድነው?

ግላኮማ በተለምዶ የዓይን ግፊት በሽታ በመባል የሚታወቅ ቢሆንም የዕይታ ነርቭንና ሬቲናን ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየጎዱ የዕይታ አድማስን ለሚቀንሱ እንዲሁም ለዓይነስውርነት ለሚዳርጉ የዓይን እክሎች የተሰጠ የወል የበሽታ ስያሜ ነው። (ነርቭ የልብ እና የአጥንት ጡንቻዎች አንዴ ከተጎዱ ወደ ቀድሞ ጤናቸው ሊመለሱ የማይችሉ ሕዋሳት መሆናቸውን ልብ ይሏል።) ግላኮማ ብዙውን ጊዜ ዓይነ ስውርነትን የሚያስከትለው  በዝግታ እና በረጅም ጊዜ በመሆኑ “ዝምተኛው የዕይታ ሌባበመባል ይታወቃል።
የተለያዩ የግላኮማ ዓይነቶች ቢኖሩም በዚህ ጽሑፍ ግን በብዛት የሚስተዋሉትን ሁለት የግላኮማ ዓይነቶችን እንቃኛለን።  እኒህም ክፍትአንግል ግላኮማ(Open angle galucoma) እና ዝግ አንግል ግላኮማ (Closed angle glaucoma) ናቸው። እነዚህ የግላኮማ ዓይነቶች የሚፈጠሩት በዓይን ውስጥ ያለው ፈሳሽ/ዓይነ ውሃ ፍሰቱ ተስተጓጉሎ ወይም ከልክ በላይ ተመንጭቶ የዓይን ውስጥ ግፊት በመጨመሩ ምክንያት በኋለኛው የዓይን ክፍል ላይ በሚገኙት የዕይታ ነርቭ እና ሬቲና ላይ ጉዳት ሲደርስ ነው።



ለግላኮማ ተጋላጭነታችንን የሚጨምሩ ነገሮች ምንድን ናቸው?
. እድሜ በተለይ 60 በላይ መሆን
. ጥቁር(አፍሪካዊ ዘር) መሆን ከነጮቹ በሦስት እጥፍ ተጋላጭነትን ይጨምራል።
. በቤተሰብ ውስጥ የግላኮማ ታሪክ ካለ በተለይ በመጀመሪያ ዘመድ(ወንድም፣ እህት፣ ወላጅ)
. ከቁጥጥር ያለፈ የዓይን ግፊት(Intra ocular pressure)
. ከቁጥጥር ያለፈ የደም ግፊት
. ያልተቆጣጠሩት የስኳር በሽታ
. ያላግባብ መድኅን ጨቋኝ(Steroids) እና ሌሎች መድኃኒቶች መጠቀም
. ዓይን ላይ የሚደርሱ አደጋዎች(Traumas)
. የዓይን መሃከለኛው ክፍል ብግነት(Uveitis )

 

የግላኮማ በሽታ ምልክቶች?
አብዛኛዎቹ ግላኮማ ያለባቸው ሰዎች የዕይታ መቀነስ እስኪኖራቸው ድረስ ምልክቶችን አያስተውሉም።
በተለይ ክፍት አንግል ግላኮማ ብዙውን ጊዜ በቶሎ ምልክቶችን አያመጣም። ሆኖም በጊዜ ሂደት የእይታ መጥፋትን በሚያስከትልበት ጊዜ፣ የጠርዝ/ጎን ዕይታን በመቀነስ ይጀምራል። ማዕከላዊ/መሃለኛው ዕይታቸው ግን ብዙውን ጊዜ አይጎዳም።  ይህም  በዋሻ ውስጥ ስንሄድ ከሚገጥመን ዕይታ ጋር ይመሳሰላል። በሽታው እየባሰ ሲሄድ ግን ማዕከላዊ እይታ ጭምር ተጎድቶ ዓይነ ስውርነት ይከሰታል።
ዝግ አንግል ግላኮማ በተለይ አጣዳፊው(Acute angle closure glaucoma) ተብሎ የሚጠራው በሽታ ሲገጥም በዓይን ውስጥ ፈጣን የግፊት መጨመር ስለሚፈጠር የሚከተሉት ምልክቶች በቶሎ ይከሰታሉ። 

  • የደበዘዘ ወይም የጠበበ የእይታ መስክ 
  • በዓይን ላይ ከባድ ህመም 
  • በመብራት ዙሪያቀስተ ደመናየሚመስል ነገር ማየት  
  • ማቅለሽለሽ/ማስመለስ
  • ራስ ምታት 
  • ምልክቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያጋጥሙ በፍጥነት የሕክምና እርዳታ ማግኘት ዓይነ ስውርነትን ለመከላከል ይረዳል።

 

የልየታ ምርመራ ለምን ያስፈልጋል?

የዓለም ግላኮማ ማኅበር(WGA) ወደ 80 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የግላኮማ ተጠቂ ቢሆኑም በሽታው እንደላባቸው የሚያውቁት ግን  50% አይበልጡም ይለናል።
ክፍት አንግል ግላኮማ ያለባቸው ሰዎች ምልክቶች እምብዛም አይኖራቸውም። ስለሆነም ባለቤቱ ባላሰበበት ሰዓት ለዝርፍያ እንደሚመጣ ሌባ ዓይናችንን ሊሰርቅ ስለሚመጣ ተዘጋጅቶ መጠበቁ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ለሌላ የጤና ምርመራ ወደ ጤና ጣቢያ ስንሄድ ደም ግፊት እንዳለብን እንደሚነገረን ሁሉ ክፍት አንግል ግላኮማም ለሌላ የዓይን ህመም ምርመራ ስናደርግ በአጋጣሚ ሊገኝ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ። ስለሆነም ከታከመ ስለማይብስ፤ ካልታከመ ግን የመታወር ስጋት ስለሚያመጣ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች የልየታ ምርመራ ቢያከናውኑ ይመረጣል። በግላኮማ የሚመጣ ዓይነ ስውርነት ሊድን አይችልምና። የዓይን ግፊት መጨመር ሊስተካከል የሚችል ለግላኮማ ከሚያጋልጡን ነገሮች አንዱ እንጂ ግላኮማ ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል። ይህም የዓይን ግፊታችን መደበኛ(8-21mmHg) ሆኖ ሳለ በግላኮማ ልንጠቃ እንችላለን ማለት ነው። ስለዚህ የዓይን ጤናችንን ለመታየት ስንሄድ ከዓይን ግፊት ምርመራ በተጨማሪ የዕይታ መስክ እና የዓይን ነርቭ ጤናማነት ምርመራ ልናደርግ ይገባል ማለት ነው። 

          የልየታ ምርመራ የሚያስፈልገው ለእነማን ነው? መቼ? በየስንት ጊዜው?
አጋላጭ ለሌለባቸው ሰዎች አጋላጭ* ነገሮች ላለባቸው ሰዎች
40 ዓመት በታች በየ 5-10 ዓመት በየ 1-2 ዓመት
40-54 በየ 2-4 ዓመት በየ 1-3 ዓመት
ከ55-64 በየ 1-3 ዓመት በየ 1-2 ዓመት
ከ64 በላይ በየ 1-2 ዓመት በየ 1-2 ዓመት

* ጥቁር/ሂስፓኒክ ዘር፣ በግላኮማ ምክንያት የመጣ የቤተሰብ የዓይነ ስውርነት ታሪክ በዋናነት ሲጠቀሱ ከላይ አጋላጭ በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር የተጠቀሱትም ያለባቸው ቢመረመሩ ይመከራል።

 

ግላኮማ ሕክምናው ምንድነው?
የዝግ እና ክፍት አንግል ግላኮማ ሕክምናዎች ሁሉም የሚሠሩት በዓይን ውስጥ ያለውን ግፊት በመቀነስ ነው። የዓይን ግፊትን ለመቀነስ 3 መንገዶች አሉ።

  • የዓይን ጠብታ መድኃኒቶች 
  • የብርሃን ጨረር  ሕክምና(Laser therapy) –ከዓይን ውስጥ ፈሳሽ የሚወጣበትን መንገድ ያሻሽላል።
  • ቀዶ ጥገናፈሳሽ በተሻለ ሁኔታ እንዲፈስ ትንሽ ቀዳዳ መክፈት ወይም በዓይን ውስጥ ትንሽ ቱቦ ማስገባትን ያካትታል።

ማወቅ ያለብዎት አንዳንድ ነገሮች፡ሐኪምዎ ያዘዘውን የዓይን ጠብታዎች ያለመሰልቸት በየቀኑ መውሰድ በጣም አስፈላጊ ነው።  እነዚህ መድኃኒቶች ዕይታዎን እንዳያጡ የሚያግዙዎት የአጠቃቀም መመሪያዎችን ከተከተሉ ብቻ መሆኑንም አይዘንጉ። ተሽሎኛል ብለው ሕክምናዎን ከመከታተል እንዳያቋርጡ።



ማጠቃለያ
በግላኮማ የሚመጣ ዓይነ ስውርነትን መከላከል ይቻላል። እንዴት ቢሉ በሽታው በልየታ ምርመራ በመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ከተገኘ ባሉት የሕክምና አማራጮች እንዳይብስ በማድረግ ዕይታን ማዳን ስለሚቻል ነው። ስለሆነም የዘገየ ምርመራ እና በቂ ያልሆነ ህክምና በግላኮማ ለሚከሰት ዓይነ ስውርነት ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸውን አውቀን ተጋላጭ የሆንን ሰዎች በጊዜ እንመርመር፤ ወላጆቻችንን በቶሎ እናስመርምር፤ ሕክምናችንን ያለመሰልቸት እንከታተል።

 

ለመጻፍ የተነበቡ ጽሑፎች
1. Uptodate 2021
2.https://www.tandfonline.com/doi/epdf/10.2147/OPTO.S295626?needAccess=true
3.https://scholar.google.com/scholar?hl=en&as_sdt=0%2C5&q=glaucoma+in+ethiopia+knowledge&oq=prevalence+of+glaucoma+in+ethiopia
4. https://www.orbis.org/en/where-we-work/africa/ethiopia
5. https://wga.one/what-is-glaucoma/#:~:text=Glaucoma%20is%20a%20chronic%2C%20progressive,produces%20characteristic%20visual%20field%20damage