የኮቪድ 19  አዲሱ ገፅታ

በዶ/ ነህሚያ አንዳርጋቸው (በሚሌኒየም የኮቪድ ህክምና ማዕከል ጠቅላላ ሀኪም)

 

ኮቪድ 19 ወይም በህክምና መጠሪያው SARS-COV 2 በዋነኝነት የመተንፈሻ አካላት ላይ እክል የሚያመጣ፣ በቀሪዎቹ የአካላዊ ስርዓቶቻችንም ላይ ችግር ሊያስከትል የሚችል ደቂቅ ህዋስ ሲሆን የሚመደበውም ቫይረስ ከሚባሉት የደቂቅ ተዋህሲያን ፈርጅ ነው።

እነዚህ በጥቅሉ ቫይረስ ተብለው ከሚጠሩት ተዋህሲያን ባህሪ ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው ከአካባቢያቸው ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር ሂደት ፈጣን የገጽታ ለውጥ ማስተናገዳቸው ነው። የኮቪድ 19’ም ቫይረስ በዚህ የተፈጥሮ ህግ መሰረት ቫይረሱ ከተለየበት ዲሴምበር 2019 ጀምሮ በርካታ ለውጦችን አስተናግዷል። ባለሙያዎችም በዘረ መል ጥናት እነዚህን ለውጦች በመከታተል ተመሳሳይ ለውጥ ያላቸውን ቫይረሶች ወደ አንድ ግንድ እያመጡ ስም እየሰጡ ይገኛሉ። ይህንንም ጥናት እያካሄዱ ያሉ የተወሰኑ ተቋሞች ያሉ ሲሆን በስፋት የሚታወቀው ግን በዓለም ጤና ድርጅት የተዋቀረው ቡድን እና ቡድኑ የቫይረሱን ግንዶች የሚጠራባቸው ስያሜዎች ናቸው። እነዚህም አልፋ፣ ቤታ፣ ጋማ እንዲሁም ዴልታ የተባሉት የኮቪድ 19 ዝርያዎች ናቸው። 

ታዲያ በዚህ አመት ብቻ ቫይረሱ ብዙ ዝርያዎችን ከፈጠረ፤ ለምን እነዚህ አራቶቹ ተለይተው ወጡ?

የሚከሰቱት ዝርያዎች በባህሪያቸው ከሰው ሰው የመተላለፍ አቅማቸው ከፍተኛ የሆነ፣ የሚያስከትሉት የህመም ሁኔታ ከበድ ያለ ወይም ለየት ያለ ሆኖ ከተገኘ ‘አሳሳቢ ዝርያ’ / Variant of Concern ተብለው ይመደባሉ። ከላይ የተጠቀሱትም አይነቶች በእነዚህ መስፈርቶች ላይ ተንተርሶ አሳሳቢ የህመም እና ስርጭት ሁኔታ ላይ በመድረሳቸው ከፍተኛውን የአለም የጤና ድርጅት የአመዳደብ ደረጃ ይዘዋል። ከዚህ ዝቅ ስንል ‘ክትትል የሚያስፈልጋቸው ዝርዮች’ / Variant of Interest ተብሎ የሚጠራው መደብ ሲገኝ እነዚህንም በባህሪያቸው የመተላለፍ አቅማቸው መጠነኛ መጨመር ካሳየ ነገር ግን የሚያመጡት ህመም ላይ መጨመርም ወይም መለየት ከሌለ ከዚህ ደርጃ ላይ እናስቀምጣቸውለን።

አልፋ/ Alpha – B.1.1.7

መጀመሪያ የተለየው: ዩናይትድ ኪንግደም

ስርጭት: ከሌሎች አይነቶች አንጻር በጣም ከፍተኛ በሆነ መጠን እና ፍጥነት ይሰራጫል

ከባድ ህመም እና ህልፈት: በአንጻራዊነት የበለጠ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ላይ ህመም እንዲሁም ህልፈት ያስከትላል

ክትባት: በአሁኑ ሰአት እየተሰጡ ያሉ ክትባቶች ይሄንን አይነት በሚገባ ይከላከላሉ፤ ከከባድ ህመም እና ህልፈትም ይጠብቃሉ።

ቤታ/ Beta – B.1.351

መጀመሪያ የተለየው: ደቡብ አፍሪካ

ስርጭት: በመጠኑ ከፍ ያለ አንጻራዊ የስርጭት መጠን ይኖረዋል

ከባድ ህመም እና ህልፈት:  እስካሁን ባለው መረጃ በግልጽ የተለየ የጨመረ ከባድ ህመም እና ህልፈት አያስከትልም

ክትባት: በአሁኑ ሰአት እየተሰጡ ያሉ ክትባቶች ይሄንን አይነት በሚገባ ይከላከላሉ፤ ከከባድ ህመም እና ህልፈትም ይጠብቃሉ።

 ጋማ/Gamma – P.1

መጀመሪያ የተለየው: ጃፓን/ ብራዚል

ስርጭትበመጠኑ ከፍ ያለ አንጻራዊ የስርጭት መጠን ይኖረዋል

ከባድ ህመም እና ህልፈት:  እስካሁን ባለው መረጃ በግልጽ የተለየ የጨመረ ከባድ ህመም እና ህልፈት አያስከትልም

ክትባት: በአሁኑ ሰአት እየተሰጡ ያሉ ክትባቶች ይሄንን አይነት በሚገባ ይከላከላሉ፤ ከከባድ ህመም እና ህልፈትም ይጠብቃሉ።

ዴልታ/ Delta – B.1.617.2

መጀመሪያ የተለየው: ህንድ

ስርጭት: ከሌሎች አይነቶች አንጻር በጣም ከፍተኛ በሆነ መጠን እና ፍጥነት ይሰራጫል

ከባድ ህመም እና ህልፈት: በአንጻራዊነት የበለጠ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ላይ ህመም እንዲሁም ህልፈት ያስከትላል

ክትባት ከዴልታ አይነት አዲስ ከመሆን ጋር ተያይዞ በኮቪድ ክትባት እና በዚህ አይነት መካከል ያለው ቁርኝነት ሙሉ ለሙሉ ግልጽ አይደለም። ይህም ሆኖ እስካሁን እየወጡ ያሉ ጥናቶች የሚያመላክቱት የኮቪድ 19 ክትባት አሁንም ቢሆን ጠቃሚ እንደሆነ ነው:: ዴልታ አይነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አገራት በስፋት እና በፍጥነት እየተሰራጨ የሚገኝ ዝርያ ነው። ይህ አይነት ከአሳሳቢነቱ እና ከአዲስነቱ አንጻር በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሳል።ከእነዚህ ጥያቂዎች መካከልም የተወሰኑትን የሚከተሉት ናቸው።

ክትባቱን የወሰደ ግለሰብ የዴልታ ዝርያን የመከላከል አቅሙ ምን ይመስላል?

እስካሁን ባሉን መረጃዎች ክትባቱን ያልወሰደ ሰው ክትባቱን ከወሰደ ሰው ጋር ሲነጻጸር በዴልታ አይነት የመጠቃት እድሉ በስምንት እጥፍ የጨመረ ሆኖ ተገኝቷል። በተመሳሳይ ክትባቱን ያልወሰደ ሰው ክትባቱን ከወሰደ ሰው ጋር ሲነጻጸር በዴልታ አይነት ታሞ ሀኪም ቤት የመግባት እና የመሞት  እድሉ በሃያ አምስት እጥፍ የጨመረ ሆኖ ተገኝቷል።

በኮቪድ 19 ተጠቅቶ ያገገመ ሰው (ነገር ግን ያልተከተበ) ግለሰብ የዴልታ ዝርያን የመከላከል አቅሙ ምን ይመስላል?

ባለፉት 12 ወራቶች ውስጥ በኮቪድ 19 ተይዞ ያገገመ ሰው ሌሎቹን የኮቪድ አይነቶች የመከላከል አቅሙ ከሞላ ጎደል ከተከተበ ሰው ጋር ተመሳሳይ እንደነበር ሲነገር ቆይቷል። ነገር ግን ይህ ሁኔታ ዴልታ አይነትን እንደማያካትት ጥናቶች እያመላከቱ ነው።

ተጨማሪ የኮቪድ 19 ዝርዮች ይፈጠ ይሆን?

አዎ! አሁንም ቢሆን የአለም የጤና ድርጅት ‘ሚው’ እና ‘ላምዳ’ የተባሉ አይነቶችን እየተከታተለ ይገኛል። ‘ላምዳ’ በጁን ወር 2021 እንዲሁም ‘ሚው’ በኦገስት ወር መጨረሻ ‘ክትትል የሚያስፈልጋቸው አይነቶች‘ የሚለውን የአለም ጤና ድርጅት ደረጃን ተቀላቅለዋል።