በናሆም ጌታቸው (በጎንደር //// የህክምና ተማሪ-C2)

ስኪፍሬንያ ምንድን ነው?

ስኪዞፍሬንያ የአንድን ሰው በትክክል የማሰብ አቅም የሚያውክ በሽታ ነው። ይህ በሽታ አንድን ሰው የሌለን ነገር እንዲያዩ፣ የሌለን ድምጽ እንዲሰሙ እንዲሁም በእውነታ ላይ ያልተመሰረቱ ነገሮችን እንዲያምኑ ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ የአንድን ሰው ስሜት አገላለጽ፣ ድርጊት አፈጻጸም እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለው ግንኙነት ላይ አሉታዊ ትጽእኖ ያሳድራል።

ስኪፍሬንያ ምልክቶች

ሀ) ‘ፖዘቲቭ’ ምልክቶች‘ፖዝቲቭ’ ስንል አዎንታዊ ወይም በጎ ለማለት ሳይሆን በስኪዞፍሬንያ ምክንያት የመጡ አዲስ፣ ያልተለመዱና ከጤናማ አኗኗር የወጡ ባህሪያት ናቸው።

 

‘ሀሉኔሽን’ – ማለት የሌለን ነገር መስማት፣ ማየት፣ ማሽተት ወይም መቅመስ ማለት ነው። ለምሳሌ፡ በአካል ማንም ሳያዋራቸው ግን በአእምሮቸው ውስጥ ይህን ወይም ያንን አድርግ የሚሉ ድምጾችን መስማት።

 

                     

‘ድሉዥን’ – ‘ድሉዥን’ ማለት የተሳሳቱ፣ በእውነት ላይ ያልተመሰረቱ አመኔታዎችን መያዝ ነው። ለምሳሌ፡- ካለምንም ምክንያት ወይም ማስረጃ ሰዎች ሊገድሏቸው እያሴሩባቸው እንደሆነ ማመንና መጨነቅ።

ያልተቀናጀ ንግግር – ሌላው የስኪዞፍሬንያ ምልክት በተቀናጀና ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ማሰብ እንዲሁም መናገር አለመቻል ነው። ይህ ህመም ያለባቸው ሰዎች ማንሳት የፈለጉት አንኳር ሀሳብ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ረዥምና ዙሪያ ጥምም ንግግር ያደርጋሉ፥ በአንድ ሀሳብ ላይ የጀመሩትን ንግግር ሳይቋጩ ምንም የይዘት ግንኙንት ወደሌለው ሌላ ሀሳብ ይሄዳሉ፥ አንዳንዴም ደግሞ ቃላት ይፈጥራሉ ወይም ምንም ትርጉም የሌላቸው ነገሮችን ይናገራሉ።

ለምሳሌ፡                  ጥያቄ፡ “ሰዎች ጸጉራቸውን ለምን ይበጠራሉ?

መልስ፡ “ምክንያቱም ህይወት ላይ አዙሪት ያመጣል፥ ቁምሳጥኔ ተሰብሯል   አግዘኝ ዝሆን። ሰላጣ ግን ጀግና አይደል?!”

                               

ለ) ኔጌቲቭ’ ምልክቶች‘ኔጌቲቭ’ ስንል በበሽታው ምክንያት በጤናማ ጊዜ የነበሩ ነገር ግን አሁን የሌሉ ወይም የተዳከሙ ባህሪያት ናቸው።

ለምሳሌ

. ከተለምዶ የተለየ ዝምተኛነት

. ለግል ንጽህና ትኩረት አለመስጠት

. በተለምዶ የሚያዝናኑና የሚያስደስቱ ነገሮችን ለማከናወን ፍላጎት ማጣት

. ከተለምዶ የተለየ ስሜት አልባነት። በፊት ላይ ምንም አይነት ስሜት ያለመነበብ።

                

 

ሐ) የመገንዘብ አቅም መቀነስ ምልክቶችይህ የአንድ ሰው በትክክል የማሰብ አቅም ሲታወክ የሚመጡ ምልክቶች ናቸው። የሚረበሹ የስራ ክፍሎች

. የመማር አና የማስታወስ

. የሰውን ንግግር የመረዳት

. ችግሮችን የመፍታት ችሎታ

 

የስኪፍሬንያ መንስኤ ?

የስኪዞፍሬንያ በሽታ መንስኤው እስካሁን አይታወቅም፥ ሆኖም ግን ተመራማሪዎች የዘረ-መል (‘Genetics’)፣ የአንጎል ኬሚስትሪና የአካባቢ ተፅእኖ ድምር ውጤት ነው ብለው ያምናሉ።

በተፈጥሮ የሚገኙ ‘ዶፓሚን’ና ‘ግሉታሜት’ የተባሉ የአንጎል ኬሚካሎች ባሉባቸው የአንጎል ክፍሎች ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮች ለበሽታው አስተዋጸኦ አላቸው ተብሎ ይታሰባል። የአንጎል ምስል ጥናቶች እንደሚያሳዩት ስኪዞፍሬንያ በታመሙ ሰዎች የአንጎል መዋቅር ውስጥ አንዳንድ ክፍሎች ላይ የተወሰኑ ለውጦች ይገኛሉ። የእነዚህ ለውጦች ምክንያት በደንብ ግልጽ ባይሆንም ስኪዞፍሬንያ ትክክለኛ አንጎል ላይ ከሚከሰት ችግር የሚመጣ በሽታ መሆኑን  ያስረዳሉ።

ለስኪፍሬንያ የሚያጋልጡ ነገሮች ምንድን ናቸው?

    . በስጋ-ዘመድ ውስጥ በበሽታው የተጠቃ ሰው መኖር

    . በእርግዝናና በወሊድ ወቅት በሚያጋጥሙ ችግሮች። ለምሳሌ፦ በእርግዝና ወቅት የተመጣጠነ ምግብ ያለመውሰድ፣ ለመርዛማ ንጥረ-ነገሮች እንዲሁም ለ‘ኢንፌክሽኖች’ መጋለጥ።

    . በወጣትነት ጊዜ አእምሮ ላይ ተጽእኖ ያላቸውን የተለያዩ አድንዛዥ እጾች መጠቀም።

አንድ ሰው ስኪዞፍሬንያ አለበት ሚባለው ነው?

ይህ በሽታ እንደሌሎች በሽታዎች በላቦራቶሪ ወይም በአካል ምስል ምርመራ ተለይቶ የሚታወቅ በሽታ አይደለም፥ ይልቁንስ አንድ ሰው ስኪዞፍሬንያ አለበት የሚባለው ልምድ ባለው የአእምሮ ሀኪም ከተመረመረ በኋላ ነው። ሀኪሙ የበሽታውን ምልክቶች ከሚያሳየው ሰው ጋር የቃለ-መጠይቅና የሰውነት ምርመራ ይደርጋል። በመቀጠልም ከስኪዞፍሬንያ ውጭ ያሉ ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች ሊያመጡ የሚችሉ ሌሎች በሽታዎች አለመኖራቸውን በደም ምርመራና እንዲሁም በአንጎል ምስል ምርመራዎች ይረጋገጣል (ለምሳሌ-አንጎል ላይ ካንሰር፣ የመጠጥ ወይም የተለያዩ እጾች ተጸእኖ) ። የሌላ በሽታዎች ውጤት እንዳልሆነ ከተረጋገጠና ምልክቶቹ ቢያንስ ለስድስት ወር ከቆዩ ይህ ግለሰብ ስኪዞፍሬንያ አለበት ተብሎ ህክምና ይጀምራል።

ስኪዞፍሬንያ ለታመመ ሰው ምን አይነት ህክምና ይሰጣል?

ስኪዞፍሬንያ ‘አንቲሳይኮቲክ’ በሚባሉ መድሀኒቶች ይታከማል። እነዚህ መድሀኒቶች ምልክቶችን በማቅለልና ከጠፉ በኋላም ተመልሰው እንዳይመጡ በማድረግ ይረዳሉ፥ ነገር ግን መድሀኒቶቹ የበሽታውን ምልክቶች መቆጣጠር እንጂ ታማሚውን ከበሽታው አይፈውሱትም። በዚህም ምክንያት መድሀኒቶቹ ለእድሜ ልክ የሚወሰዱ ናቸው።

ከመድሀኒት በተጨማሪ የተለያዩ የምክር አገልግሎቶችን በመስጠት የታማሚዎችን ማህበራዊ፣ ስነ-ልቦናዊና የስራ ቦታ ህይወት በጤናማ ሁኔታ እንዲመሩ እገዛ ይደረግላቸዋል።

 

 

 

ዋቢ መጻህፍት

    . Crowley, K. (2018, April 03). Patient education: Schizophrenia (The Basics). UpToDate.

https://www.uptodate.com/contents/schizophrenia-the-basics?source=related_link

    . American Psychological Association. (2015, February 15). Recognizing the signs of schizophrenia. http://www.apa.org/topics/schizophrenia/recognizing

    . Bhandari, S. (2020, January 21). Schizophrenia: An overview. WebMD.

https://www.webmd.com/schizophrenia/mental-health-schizophrenia

 

ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ሄርሞን አማረ (የስነ አዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።