በአቤኔዘር ቦጋለ በMyungsung Medical College የህክምና ተማሪ-C1)

የኮቪድ 19  ወረርሽኝ የጥፋት በትሩን አለም ላይ ማሳረፍ ከጀመረ እነሆ ሁለት አመታት ተቆጠሩ።በነዚህም ሁለት አመታት ከበሽታው ጋር የተያያዙ በርካታ አስከፊ ዜናዎች ቢሰሙም የክትባቱ መገኘት ግን አብዛኛዉን የአለም ህዝብ ያስደሰተና ተስፋ የሰጠ ነበር።ለመሆኑ ይህ ክትባት እንዴት በሽታዉን መከላከል ያስችላል?እንዴትስ ፈጥኖ  ሊደርስ ቻለ? ክትባቱስ ኮቪድ 19 ሊያሲዘን ይችላል? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ቀጥሎ ባለዉ ፅሑፍ ለመመለስ እሞክራለዉ።መልካም ንባብ።

ሀ፡ለመሆኑ ይህ ክትባቶች እንዴት በሽታዉን መከላከል ያስችላሉ?

ከተለያዩ የሰውነታችን ተግባራት መካከል አንዱ እራሱን ከበሽታ መከላከል ነው።ሰውነታችን ሊያጠቃው የመጣ በዐድ አካል(ባክቴሪያ ቫይረስ ፈንገስ ወ.ዘ.ተ) ካለ ለማወቅ  ከዚያም አልፎ ለመግደል ወይም ባለበት ለማቆም የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማል።ከእነዚህ መካከል ዋናው መንገድ ያንን በዐድ አካል የሚያጠቃ “ወታደር” ወይም በሕክምና ቋንቋ Antibodies በመስራት ነዉ።ታዲያ እነዚህን Antibodies ለመስራት በመጀመሪያ ስለ በዐድ አካሉ ማንነት እና እንዴት ሰውነታችንን እንደሚያጠቃ መረጃ ያስፈልገዋል።ስለዚህ ይህ በዐድ አካል ቀደም ሲል ሰውነታችንን ካጠቃ ሰውነታችን የቀድሞ መረጃ ስላለው ፀረ እንግዳ አካላትን(Antibodies)በፍጥነት ማዘጋጀት ይችላል።ነገር ግን ይህ ለሰውነታችን አዲስ ከሆነ ሰውነታችን ፀረ እንግዳ አካላትን ለማዘጋጀት ጊዜ ይወስድበታል።በዚህ የጊዜ ክፍተት ውስጥ ታዲያ ይህ በዐድ አካል ሰውነታችንን በከፍተኛ መጠን ያጠቃል። ስለዚህ ክትባቶች የሚሰጡት ይህንን “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” አይነት ሁኔታ ለመከላከል እና ቀድሞ “በርበሬዉን ለመቀንጠስ” ነዉ።የኮቪድ 19 ክትባትም ዋና ጠቀሜታ ይኸዉ ነዉ።

የኮቪድ ክትባት ወደ ሰውነታችን ሲገባ ከላይ የጠቀስነውን አይነት መረጃ የኮቪድ 19 ስለሚያስከትለው ቫይረስ(ኮሮና ቫይረስ)ለሰውነታችን በበሽታዉ ከመያዛችን በፊት ይደርሠዋል።ስለሆነም በቂ እና ብቁ የሆኑ “ወታደሮችን” ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ ያገኛል።ነገር ግን መሳሳት የሌለብን ነገር ክትባቱ የኮሮና ቫይረስን ሙሉ ክፍል አልያዘም፤ይልቁንም ከቫይረሱ ዉስጥ Spike Protein በመባል የሚታወቀዉን እሾህ መሰል ቅንጣት እንጂ።ይህ እሾህ መሰል ቅንጣት የተመረጠበትም ምክንያት ቫይረሱ ከሳንባችን ጋር ለመጣበቅ የሚጠቀምበት በመሆኑ ነው። ታዲያ ይህ ማለት ኮሮና ቫይረስን እንደ አንድ ሰው ብንወስደው ክትባት ውስጥ የተካተተው “እጁ” ብቻ ነው እንደማለት ነዉ።

ምስል 1-የኮሮና ቫይረስ  መዋቅር(structure) ማሳያ

ከላይ የተሰጠዉ ቀላል እና አጭር ማብራሪያ ሁሉም የኮቪድ ክትባቶች በመሠረታዊነት የሚከተሉት ቢሆንም ለመከማቸት የሚፈልጉት መጠነ ሙቀት፣ Spike Proteinን ወደ ሰውነታችን ለማስገባት የሚጠቀሙት መንገድ እና ሌሎችም ምክንያቶች በመካከላቸው የተወሰነ ልዩነት ፈጥሯል።

ለ-በኮቪድ-19 ክትባት ዙሪያ ከሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች መካከል ጥቂቶቹ እና ምላሾቻቸዉ
ከላይ የተሰጠዉ ቀላል እና አጭር ማብራሪያ ሁሉም የኮቪድ ክትባቶች በመሠረታዊነት የሚከተሉት ቢሆንም ለመከማቸት የሚፈልጉት መጠነ ሙቀት፣ Spike Proteinን ወደ ሰውነታችን ለማስገባት የሚጠቀሙት መንገድ እና ሌሎችም ምክንያቶች በመካከላቸው የተወሰነ ልዩነት ፈጥሯል።

ሐሰተኛ መረጃ 1-የኮቪድ ክትባቶችን ለመፍጠር ጥቅም ላይ የዋለው ቴክኖሎጂ ደህንነቱ ያልተጠበቀና በጣም አዲስ ነው።

እዉነኛዉ መረጃ-ይህ ክትባት ለመፍጠር ጥቅም ላይ የዋለው ቴክኖሎጂ ምርምር የተጀመረው በ1990ዎቹ ሲሆን ከኮቪድ ጋር የሚቀራረቡት እና ቀደም ብለው የተከሰቱት ሁለት የመተንፈሻ አካላት  በሽታዎች (SARS (ከባድ አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት ሲንድሮም) እና MERS (የመካከለኛው ምስራቅ የመተንፈሻ ሲንድሮም) ላይ የተደረጉት ምርምሮች  ለዛሬው  የቴክኖሎጂው እድገት አግዘዋል።

ሐሰተኛ መረጃ 2-የኮቪድ ክትባትን መውሰድ ኮቪድን ሊያስዝ ይችላል።

እዉነኛዉ መረጃ-ከላይ ለማስረዳት እንደሞከርኩት ይህ በሕክምና እውቀት መሰረት የሚቻል አይደለም። ክትባቱ ቫይረሱን በውስጡ አልያዘም።

በመጨረሻም ምንም እንኳን ክትባት መውሰድ በበሽታው የመያዝ እና ለሞት የመጋለጥ እድልን በከፍተኛ መጠን ቢቀንስም በሀገራችን ክትባቱን የወሰደዉ ሰዉ ቁጥር ከሀገሪቱ ህዝብ ቁጥር አንፃር አነስተኛ በመሆኑና በኮሮና ቫይረስ የመለዋወጥ ፀባይ ምክንያት አሁንም ጥንቃቄ አይለየን።

ዋቢ

1-Centers for Disease Control and Prevention,.2021. Understanding How COVID-19 Vaccines Work https://www.cdc.gov/coronavirus/2019-ncov/vaccines/different-vaccines/how-they-work.html

2- Centers for Disease Control and Prevention. 2021. Myths and Facts about COVID-19 Vaccines https://www.cdc.gov/coronavirus/2019-ncov/vaccines/facts.html

3-Krishna Mohan Agarwala Swati Moha patrab Prairit Sharmaa Shreya Sharmac Dinesh Bhatiad Animesh Mishrae.(2020). Study and overview of the novel corona virus disease (COVID-19).Science Direct. https://doi.org/10.1016/j.sintl.2020.100037

 

ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ (የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት/የተላላፊ በሽታዎች ሰብ ስፔሻሊስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።