በዶ/ር ናታን ሙሉብርሃን  (የድንገተኛና ጽኑ ህክምና ስፔሻሊስት )

መቼም የኮሮናን ወረርሽኝ ተከትሎ ስለመተንፈሻ ማሽን አስፈላጊነትና ጥቅም ተደጋግሞ ሲነገር መስማት የተለመደ ሆኗል። ለመሆኑ የመተንፈሻ ማሽን (Mechanical Ventilator) ምንድነው? እንዴትስ ይሰራል? መቼስ ነው የምንጠቀመው? እነሆ ብያለሁ…

የሰው ልጅ ለመኖር ከሚያስፈልጉት ንጥረ ነገሮች መካከል ኦክስጅን ቀዳሚ ሊባል የሚችል ሲሆን ይህንንም ከከባቢ አየር ላይ አየር በአፍንጫና አፍ በኩል ተስቦና በአየር ቱቦ ውስጥ አልፎ በሁለቱ ሳንባዎች አማካኝነት ከደም ጋር በመቀላቀል በልብ አማካኝነት ለመላው የሰውነት ህዋሳት ይሰራጫል። ሆኖም ሳንባ በተለያየ ህመም (የሳንባ ምች፣ ኮቪድ ወዘተ…) ሲጠቃ በተፈለገው መልኩ ኦክስጅን ወደ ደም ማስገባት እንዲሁም ካርቦንዳይኦክሳይድ (የተቃጠለ አየር) ማስወጣት ይሳነዋል በሌላም በኩል የአእምሮ ንቃትን የሚቀንሱ ህመሞች እንደ ስትሮክ፣ ኃይለኛ የጭንቅላት ጉዳት፣ ማጅራት ገትር ወዘተ… ያሉ ህመሞች ሲከሰቱ የአየር ቱቦ እንደተከፈተ እንዳይቆይ ያደርጋሉ፤ በዚህም ምክንያት በቂ አየር ወደ ሳንባ አይደርስም። እንደዚህ አይነት ታካሚ ወደ ህክምና ተቋም ሲሄዱ በቂ ኦክስጅን እንዲያገኙ የመተንፈሻ ማሽን የድጋፍ ህክምና ይደረግላቸዋል። የመተፈሻ ማሽን እኤአ 1950 ዓ.ም ላይ ተቀስቅሶ የነበረውን የፖሊዮ ወረርሽኝ ተከትሎ በጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በሂደትም የተለያዩ መሻሻሎችን በማድረግ በአሁኑ ሰዓት ቀላልና ተንቀሳቃሽ የመተንፈሻ ማሽን ለመጠቀም በቅተናል።

የመተፈሻ ማሽን አንድ ታካሚ እንዲተነፍስ የሚያግዝ ማሽን ሲሆን ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች ማለትም የሳንባ መጎዳት እንዲሁም የአየር ቱቦ መዘጋት በተጨማሪም ቀዶ ጥገና (Surgery) ሲሰራ ጠቅላላ የሰመን መድሃኒት ከተሰጠ የመተንፈሻ ማሽን ያስፈልጋል። ታካሚ ከመተፈሻ ማሽን ጋር በአፍ ውስጥ በሚያልፍና ከዋናው የአየር ቱቦ (ትራኪያ) ጋር በሚያገናኝ ሰው ሰራሽ ቱቦ አማካኝነት የሚገናኝ ሲሆን ከማሽኑ ወደ ሳንባዎች በቱቦው አማካኝነት የተመጣጠነ አየር ይሰጣል እንዲሁም ከታካሚው የተቃጠለ አየር እንዲወጣ ያደርጋል። ታካሚውም ከማሽን ጋር ከተገናኝ በኃላ የቅርብ ክትትል የሚደረግለት ሲሆን የልብ ምት፣ የደም ኦክስጅን/ካርቦንዳኦክሳይድ መጠን፣ የደም ግፊት…በየሰአቱ ይታያሉ።

 

 

የመተንፈሻ ማሽን በርካታ ጥቅሞች የሚሰጥ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የተቋረጠ ወይም ሊቋረጥ ያለን አተነፋፈስ ማስቀጠል፣ ለመተንፈሻ ጡንቻዎች እረፍትን መስጠት፣ ፈሳሽ ወደ ሳንባ እንዳይገባ መከላከል፣   ሳንባው የተጎዳን ታማሚ እንዲያገግም ማሳረፍ በዋናነት ይጠቀሳሉ። የመተንፈሻ ማሽን በድንገተኛ ክፍል ውስጥ፣ በጽኑ ህክምና ክፍል ውስጥ፣ በኦፕሬሽን ክፍል፣ እንዲሁም አሁን አሁን በአንቡላንስ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የሰለጠነ ባለሞያ ብቻ ሊጠቀምበት የሚገባ መሳሪያ ነው

የመተንፈሻ ማሽን ላይ ያለ ታካሚ አክታ በራሱ መትፋት ስለማይችል በየሰአቱ በቱቦ እየተመጠጠ እንዲወጣ ይደረጋል። መመገብ ስለማይችል የምግብ ቱቦ ተቀጥሎለት የላመ ምግብ ይሰጠዋል በተጨማሪም የሰመመን መድሃኒትና ህመም ማስታገሻ ይሰጠውና እንዲተኛ ይደረጋል። የመተንፈሻ ማሽን ለመጠቀም እንደተፈለገበት ምክንያት ከሰአታት እስከ ወራት ለአንድ ታማሚ ልንጠቀም እንችላለን፤ ባለሞያዎችም በየጊዜው የታካሚውን ሁኔታ እየተከታተሉ በራሱ መተንፈስ ይችላል ብለው ሲወስኑ ከማሽን ላይ እንዲላቀቅ ያደርጋሉ።

የመተንፈሻ ማሽን የራሱ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያመጣ የሚችል ሲሆን ከነዚህም መካከል የሳንባ ኢንፌክሽን በተለይም ለረጅም ቀናት ከተጠቀምን፣ የነቃሊብ (አልቪዮሊ) መቀደድና አየር በሳንባ አቃፊ ውስጥ መጠራቀም፣ ከማሽን ላይ መላቀቅ (extubate) አለመቻል/በራስ ወደ መተንፈስ መመለስ አለመቻል፣ የማይድሞች ከሆኑ ደግሞ ስቃይን ማራዘም ይጠቀሳሉ።