Written by በእምነት የሻው ሳልህ (በቅ/ጳ/ሚ/ሜ/ኮ የ5ኛ አመት ተማሪ)
የጡት ማጥባት ጥቅሞች
የመጀመሪያ ሳምንት ላይ…
እንኳን ደስ አለሽ! አሁን ልጅሽን ፈጣሪ ረድቶሽ በሰላም ተገላግለሻል፡፡ ከዚህ በኋላ ለሚኖረው የጡት ማጥባት ቆይታሽም እጅግ ጠቃሚዎቹ ጊዜያት እነዚህ የመጀመሪያ ቀናቶች ናቸው፡፡ በጥሩ ሁኔታ ማጥባት ከጀመርሽ በጥሩ ሁኔታ የመቀጠል እድልሽ ሰፊ ይሆናልና፤ እንዲሁም መጀመሪያ በደንብ ካጠባሽ ወደፊት ጡትሽ በቂ ወተት ይኖረዋል የሚል ተፈጥሯዊ ሕግ ስላለ ምንም እንኳን እነዚህ ቀናት በሕይወትሽ ትልቅ ለውጥ የምታስተናግጂባቸው እና ከባድ ቢሆኑም ልጅሽን በማጥባት የሚቀጥሉትን ጊዜያቶች የተስተካከሉ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ይህንን የመጽሐፉን ክፍል ስታነቢ ልጅሽ ከሁለት ሳምንት አልፏት ቢሆን እንኳን ይህ ክፍል አይመለከተኝም ብለሽ እንዳትዘዪው፤ ምናልባት አስተያየትሽን ሰፋ ሊያደርግልሽ ስለሚችል ማለት ነው፡፡
በመጀመሪያዎቹ ቀናት ጤነኛ የአመጋገብ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ልክ ሕጻኗ ልጅሽ እንደተወለደች ካንቺ ጋር ለተወሰነ ጊዜ በመነካካት መቆየት ስላለባት ሆድሽ ላይ እንድትተኛ ይደረጋል፡፡ ከተወለደች በኋላ ባለው የአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥም ጡት ማጥባት አስጀምሪያት፡፡ ልጅሽ በዚህ ጊዜ እንገር ታገኛለች። ይህ የመጀመሪያው ከጡትሽ የሚወጣው ቢጫ ቀለም ያለው ወፈር ያለ ወተት ነው ፤ ሕጻኗ ልጅሽን ከተለያዩ በሽታዎች ይጠብቃታል፡፡
በመጀመያው ሳምንት የሚኖረው የማጥባት ሁኔታ በሁለተኛው ሳምንት እና ከዚያ በኋላ ከሚኖረው ጋር ሰፋ ያለ ልዩነት ሊኖረው ይችላል፡፡ እስካሁን የሰማሽውና ያነበብሽው ነገር አብዛኛው ከሁለተኛው ሳምንት ጀምሮ ያለውን የሚመለከት ነው፡፡
ገና የተወለደችው ጨቅላ ሕጻን ልጅሽ ከወሊድ በፊት ተርባ አታውቅም ነበር፤ የምግብ(ንጥረነገር) ፍላጎቷ በቋሚነት በእትብት በኩል ይሟላላት ነበር፡፡ ከወሊድ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ረሃብ ምን ማለት እንደሆነ ታያለች፡፡ የሥርዓተ ልመትን (digestive system) መጠቀም እና በጊዜ የተገደበ መብልም ለሷ አዲስ ነው፡፡
ታዲያ ልጅሽ የምታሰተናግደውን ተፈጥሯዊ ለውጥ ቀለል ለማድረግ ቀስ በቀስ፣ በትንሽ በትንሹ ማጥባት ትጀምሪያለሽ፤ የልጅሽ ጨጓራ በእያንዳንዱ የመጥቢያ ጊዜ ከ5 እስከ 10 ሚሊ ሊትር ብቻ ነው መያዝ የሚችለው፣ የሚደንቀው ነገር በዚህ ጊዜ በጡትሽ ውስጥ ተዘጋጅቶ ያለው እንገርም መጠኑ ይህን ያህል ነው፡፡ ከሚበቃት በላይ ወተት ብታጠጫት፣ ጨጓራዋ የመለጠጥ አቅምም ስለሌለው መልሶ ወደ ውጪ መውጣቱ ነው፡፡
መች መች ላጥባት?
ገና የተወለደችው ልጅሽ በጣም እንቅልፋም በመሆኗ መመገብ በሚያስፈልጋት ጊዜ ሁሉ የመፈለግ ምልክቶችን ላታሳይሽ ትችላለች፡፡ ስለዚህ ፍላጎት ባሳየች ጊዜ ሁሉ አጥቢያት፤ ነገርግን በ24 ሰዓት ውስጥ ቢያንስ 8 ጊዜ ትጥባ፡፡ በተደጋጋሚ ማጥባት ጡትሽንም የበለጠ ወተት እንዲያመርት እንደሚያደርገው አትርሺ፡፡
ከላይ እንደጠቀስነው ልጅሽ ሲርባት/ ምግብ ስትፈልግ ምልክቶችን ታሳይሻለች (ምንም እንኳን በመጀመሪያው ሳምንት በተገቢው ጊዜ ሁሉ ባታሳይም)፡፡ ሕጻናት እንደራባቸው ለማወቅ የግድ እስከሚያለቅሱ መጠበቅ የለበትም፡፡ ማልቀስ የልጅሽን ረሃብ የሚያመለክት ዘግይቶ የሚመጣ ምልክት ስለሆነ ሕጻኗ እዚህ ደረጃ ሳትደርስ እንድትመግቢያት ይመከራል፡፡ ታዲያ ከማልቀስ ቀደም ብለው የሚመጡ ምልክቶች፡
- አፏን በደንብ በመክፈት ራሷን ከአንድ ጎን ወደ ሌላ ማመላለስ (ጡት እየፈለገች መሆኑ ነው)
- እጇን ወደ አፏ መክተት
- መንጠራራት እና እንቅስቃሴ ማብዛት
- የመጨናነቅ/ የመረበሽ ስሜት ማሳየት ናቸው፡፡
ሕጻናት ገና እንደተወለዱ አካባቢ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሊጠቡ ይችላሉ፡፡ ለአንድ ወይም ሁለት ቀን በጣም በተደጋጋሚ ሊጠቡ፣ በሌሎች ቀናት ደግሞ በቀን ትንሽ ጊዜ ብቻ ሊጠቡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ረገድ አንድ ሕጻን ከሌላ ሕጻን ቢለያይም አብዛኞቹ ግን ከአንድ እና ከሁለት ሳምንት በኋላ ቋሚ የመጥቢያ ሰዓቶችን / ድግግሞሽን እየያዙ ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ አካባቢ በ24 ሰዓት የምትመገብበትን ድግግሞሽ መቁጠርና መቆጣጠርሽ እንደተጠበቀ ሆኖ በመጥቢያ ሰዓቷ መካከል የሚኖረውን ክፍተት ግን ብዙ አትጨነቂበት፡፡ ሕጻኗ ትንሽ አደግ እስከምትል ቋሚ የመመገቢያ ጊዜ እንዲኖራት አትጠብቂ፡፡ (ልጅሽ በየግማሽ ሰዓቷም የምትጠባበት ጊዜ ይኖር ይሆናል!!)
የሽንት ጨርቅ
የሽንት ጨርቅን በተመለከተ በደንብ እየጠባች ያለች ሕጻን በቀን ቢያንስ 6 ዳይፐሮችን/ የሽንት ጨርቆችን እያራሰች ታስቀይርሻለች፡፡ ይህ ግን ከትንሽ ጊዜ በኋላ ነው እውነት የሚሆነው፤ ለጊዜው ግን ትንሽ ለየት ያለ ነገር ይኖራል። በመጀመሪያዎቹ ቀናት ሕጻኗ የምትወስደው ወተት ትንሽ በመሆኑ፣ የምታስቀይርሽ ዳይፐርም እንዲሁ አነስ ያለ ይሆናል፡፡ ይህ እስከ 3ኛ እና 4ኛ ቀን ድረስ ይቀጥላል፡፡ በአንደኛው ሳምንት መጨረሻ ላይ ልጅሽ የምትጸዳዳበት መጠን ስትወለድ ከነበራት በዐሥር እጥፍ ሊጨምር ይችላል፡፡
ከልጄ ጋር በአንድ አልጋ እንተኛ?
ከጤነኛ ወሊድ በኋላ እናትና ልጅ ተለያይተው እንዲተኙ ባለሙያዎች አይመክሩም፡፡ ባስፈለገ ጊዜ ሁሉ ልጅሽን ለመመገብ፣ እቅፍ ለማድረግ እና ለማጽዳት ከልጅሽ ጋር በአንድ አልጋ፣ ካልሆነም በአንድ ክፍል መተኛት ይኖርብሻል፡፡ ስለዚህ ልጅሽን ካንቺ ጋር በአንድ አልጋ አስተኚያት፣ አሊያም ደግሞ በሕጻን አልጋ አድርገሽ ካንቺ አጠገብ አስተኚያት፡፡
በተለይ በሀገራችን አብዛኞቹ ጡት የሚያጠቡ እናቶች ከልጆቻቸው ጋር እጅግ የተቆራኘ የዕለት ዕለት ኑሮ ስላላቸው ይህንን ጉዳይ ማንሳት ምናልባት ለቀባሪ እንደ ማርዳት ሊሆንብን ይችላል፡፡ ለአንድ ሕጻን ከእናቱ ጋር በአንድ አልጋ መተኛት ለደኅንነቱ አስጊ እንደሆነ የሚነገርበትም ጊዜ አለ፡፡ በእርግጥም ይህንን የሚጠቁሙ አንዳንድ ጥናቶችም አሉ፤ ሌሎች በቅርብ ጊዜ የወጡ ጥናቶች ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው በአንድ አልጋ መተኛት ችግር እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ምንም እንኳን በባለሙያዎቹ ዘንድ አወዛጋቢ ቢሆንም ግን እጅግ ለረዥም ጊዜ በእናቶች ሲተገበር የነበረ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ከሕጻኗ ልጅሽ ጋር በአንድ አልጋ የምትተኚ ከሆነ ግን የሚከተሉትን ነገሮች ተጠንቀቂ፡
- መጠጥ ጠጥተሽ ከሆነ ከልጅሽ ጋር አብረሽ እንዳትተኚ
- ሲጋራ የምታጨሺ ከሆነ አቁሚ
- አልጋ ላይ እንጂ ሶፋ ላይ ልጅሽን ይዘሽ እንዳትተኚ
የጡት ማጥባት ጥቅም ምንድነው?
አንድ የማይቀለበስ እውነት የጡት ወተት ለጨቅላ ሕጻንሽ እጅግ ተመራጭ የሆነው ምግቧ መሆኑ ነው፡፡ የጡት ወተት ለልጅሽ እድገት እጅግ የተስማማ ነው፡፡አንቺ በተገቢው መንገድ የምትመገቢ ከሆነ፣ የጡትሽ ወተት በኃይል ሰጪ ካሎሪዎች እና በሌሎች የተመጣጠኑ ንጥረነገሮች የተዋቀረ ይሆናልና እስከ ስድስት ወር የሚያስፈልጋትን ነገር ሁሉ ያሟላላታል፡፡
የጡት ወተት በውስጡ የእናቲቱን የዓመታት ትዝታ እና እውቀትን ይይዛል! ይህም ማለት አንቺ በሽታን የተዋጋሽባቸውን ጥበቦች የያዙት ወታደሮች በጡት ማጥባት ጊዜ ወደ ልጅሽ ያልፋሉ፡፡ እነዚህ ወታደሮች አንቲቦዲስ ይባላሉ፡ በአጭሩ በደም ውስጥ የሚገኙ በሽታ አምጪ ተህዋስያንን የሚዋጉልን ፕሮቲኖች ናቸው፡፡ የፎርሙላ ወተት የሚጠቀሙ ሕጻናት የጡት ወተት ከሚወስዱት ይልቅ በተደጋጋሚ ይታመማሉ ማለት ነው፡፡
የጡት ወተት ከዚህም ሌላ ብዙ ጥቅሞች አሉት፤ ከነዚህም ውስጥ የልጅሽን አንጀት የማነቃቃት ብቃቱ ይጠቀሳል፡፡ የጡት ወተት የሕጻኗን ሰገራ ስለሚያለሰልስላት በቀላሉ እንድትጸዳዳ ይረዳታል፡፡ ሕጻናት የፎርሙላ ወተትን ለማብላላት ከጡት ወተቱ ይልቅ ሁለት እጥፍ ጊዜ ይፈጅባቸዋል፤ ስለዚህ ፎርሙላን ሲወስዱ የሚመገቡበት ድግግሞሽም ይቀንሳል፤ ሰገራቸውም የጠጠረና ሽታ ያለው ሊሆን ይችላል፡፡
ጡት ማጥባት የልጅሽን ጤና ከመጠበቅ ባለፈ ንቁ እና ብልህ እንድትሆንም ያስችላታል፡፡ ብዙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ጡት የሚጠቡ ሕጻናት በፎርሙላ ወተት እና በሌላ መንገድ ምግባቸውን ካገኙት ሕጻናት የበለጠ የሰላ ጭንቅላት ይኖራቸዋል፡፡ የዚህም ምክንያቱ ጡት ማጥባት ለሕጻናት የአዕምሮ እድገት የሚያስፈልገውን ንጥረነገር በመያዙ ነው፡፡
ጡት ማጥባትን የፎርሙላ ወተት ከመጠቀም የተሻለ የሚያደርገው ሌላው ነገር ሁሌም ዝግጁ፣ ተስማሚ እና በምቹ የሙቀት መጠን የሚገኝ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ጡጦ ማጠብ፣ መቀቀል፣ መበጥበጥ፣ ወተቱን ማሞቅ ወዘተ የሚባል ነገር ባለመኖሩ ሰዓትሽንም ገንዘብሽንም ይቆጥብልሻል፡፡
ጡት ማጥባት ላንቺም ብዙ ጥቅም አለው፤ ከወሊድ በኋላ ሕጻኗ ያንቺን ጡት ስትጠባ ከማህጸንሽ የሚፈሰው ደም እንዲቀንስ ያደርግልሻል፡፡ ማህጸንሽም በፍጥነት ከእርግዝና በፊት ወደ ነበረው መጠን እንዲመለስ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ጡት የምታጠቢ ከሆነ ለጡት እና ሌሎች አንዳንድ ካንሰሮች ያለሽ ተጋላጭነት ይቀንሳል፡፡ ጡት ማጥባት ተፈጥሯዊ የእርግዝና መከላከያሽም እንደሆነ መዘንጋት የለብሽም፡፡
ጡት በማጥባት ወቅት ልጄን እንዴት ልያዛት?
የተሳሳተ የሕጻን አያያዝና አስተቃቀፍ ጡት ማጥባትን እንዳይሳካ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ የተሳሳተ አያያዝ እና የጡት አጎራረስ የእናቲቱን የጡት ጫፍ እና ጡቱን ራሱንም ሊጎዳ ይችላል፡፡
ለሁሉም እናቶች የሚመች አንድ ዓይነት አቀማመጥ እና የአያያዝ ስልት ማግኘት ከባድ ነው፤ ምክንያቱም ያንቺ የክንድ ርዝመት፣ እንዲሁም የጡትሽ ግዝፈት ከሌሎች እናቶች ጋር ስለሚለያይ ነው፡፡ ለጓደኛሽ ወይም ለጎረቤትሽ በጥሩ ሁኔታ የሰራው ላንቺ ላይሰራ ይችላልና ላንቺና ለልጅሽ የሚመቸውን አያያዝና አቀማመጥ በሙከራ ድረሺበት፡፡
የትኛውንም ዓይነት አያያዝና አቀማመጥ ብትመርጪም ዋናው ነገር ክንድሽ እና ትከሻሽ ዘና ማለቱ እና ምቾት ማግኘትሽ፣ እንዲሁም ሕጻኗን ወደ ራስሽ አስጠግተሸ እና ሙሉ በሙሉ ወደ ጡትሽ አዙረሽ መያዝ እንድትችዪ ማድረጉ ነው፡፡ በምታጠቢበት ጊዜ፣
- የሕጻኗ አንገት ሙሉ በሙሉ ክንድሽ ላይ ይሁን (እስከ ትከሻዋ ድረስ) እጅሽ እስከ ሕጻኗ መቀመጫ መድረስ አለበት፡፡
- የሕጻኗ ሰውነት ወዳንቺ ሰውነት ይጠጋ
- የሕጻኗ አፍ በደንብ ይከፈት፤ ጡቱን ስታጎርሻት በመጀመሪያ ሕጻኗ አፏን በደንብ እንድትከፍት አድርገሻት በሙሉ አፏ እስከምትይዘው ድረስ በደንብ ማስገባት አለብሽ፡፡
- አገጯ ጡትሽን መንካት አለበት፡፡
ልጄ በደንብ እየጠባች እንደሆነ እንዴት አውቃለሁ?
በአግባቡ እየጠባች ያለች ሕጻን ስትውጥ ትሰሚያታለሽ፤ ስትጠባም ጉንጯ ሞላ ያለ እንጂ ወደ ውስጥ የተጣበቀ አይሆንም፡፡ ስትጠባ ረጋ እና ዘና ትላለች፤ ስትጨርስም ራሷ ጡትሽን ትለቀዋለች፡፡ በዚህ ጊዜ አፏ እንደራሰ ማየት ትችያለሽ፡፡ የጡትሽ ጫፍም ስለአጠባብሽ ይናገራል፡ ልክ ልጅሽ ጠብታ ስትነሳ የጡትሽ ጫፍ መጠፍጠፍ ወይም የተቆነጠጠ አይነት መምሰል የለበትም፤ ሕጻኗ በትክክል ጎርሳ ከነበረ የጡትሽን ጫፍ ሳይሆን በደንብ ገባ አድርጋ ጡቱን ስለምትጎርስ የጫፉ ቅርጽ ያን ያህል አይለወጥም፡፡ ካጠባሽ በኋላ ጡትሽም ወተቱ ስለሚወጣ ለስለስ ይላል፡፡
ሕጻኗ ልጅሽን ስታጠቢ ታዲያ አንዱን ጡት ጨርሳ ሳትጠባ ወደሌላኛው ማዞር የለብሽም፡፡ወደ ሌላኛው ጡትሽ ከማዞርሽ በፊት አንዱ ጡትሽ ላይ እስከምትጨርስ ድረስ ፣ቢያንስ ከ5 እስከ 10 ደቂቃ አጥቢያት፡፡ (ገና አዲስ የተወለዱ ሕጻናት በአንድ ጡት ላይ እስከ 20 ደቂቃ ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ፤ እያደጉ እና እየተለማመዱ ሲሄዱ ነው ከ5-10 ደቂቃ በአንድ ጡት ላይ የሚወስዱት፡፡) ይህን ስታደርጊ ሕጻኗ ልጅሽ በደንብ ንጥረነገር ያለውን ቆየት ብሎ የሚወጣውን ወተት እንድታገኝ ታደርጊያታለሽ፡፡
ሕጻናት አንድ ጊዜ ሲጠቡ ሁለት ዓይነት ወተትን ያገኛሉ፤ ልጅሽ ገና መጥባት እንደጀመረች የሚወጣው ወተት የስብ መጠኑ አነስተኛ የሆነ፣ የውሃ መጠኑ ደግሞ በዛ ያለ ስለሆነ የሕጻኗን ጥም ይቆርጥላታል፡፡ ትንሽ ቆይቶ የሚወጣው ወተት ግን የካሎሪ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ፣ ረሃቧን ሊቆርጥ የሚችል አይነት ነው፤ ስለዚህም ነው ‘የተመጣጠነ ወተት’ እንድታገኝ ልጅሽን አንዱ ጡት ላይ እስከምትጨርስ ድረስ ሳታጠቢ ወደሌላኛው ማለፍ የሌለብሽ፡፡
የጤና ወግ
ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።
የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።