By: Dr.  Nahom Megerssa (GP at Armed Forces Comprehensive Specialized Hospital)

ዶክተር ናሆም መገርሳ ( አጠቃላይ ሀኪም)

Reviewed/Approved  by: Dr.Lemma Zewde (Editor at Yetena Weg/ Internist)

 

የቶንሲል ህመምና የልብ በሽታ

የጉሮሮ ህመምን ከሚያስከትሉ ምክንያቶች መካከል በተለያዩ ተዋህስያን ኢንፌክሽን ምክንያት የሚመጡ እንደ ቶንሲል ህመም ያሉ በሽታዎች ዋነኞቹ ሲሆኑ አለርጂ፣ የጉሮሮ መድረቅ፣ በጣም ሙቅ የሆኑ ምግቦች ወይም መጠጦችን መውሰድ እና ድምፅን አብዝቶ መጠቀም የመሳሰሉ ምክንያቶች ደግሞ አነስተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።

የቶንሲል ህመም

ቶንሲሎች በአፋችን የላ ክፍል ከእንጥል በግራና በቀኝ በኩል የሚገኙ እጢዎች ሲሆኑ ጥቅማቸውም ከምንመገባቸው ምግቦችና ከምንተነፍሰው አየር ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ ጎጂ ተዋሲሀንን እንደመጀመሪያ መከላከያ መንገድ ሆኖ ማገልገል ነው፡፡ የእነኚህ ቶንሲሎች በኢነፌክሽን መጠቃት በተለምዶ “ቶንሲል” የምንለውን ህመም ያስከትላል፡፡ የቶንሲል በሽታ ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃ ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ በትምህርት መግቢያ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ህፃናትን ያጠቃል፡፡

 

የቶንሲል በሽታ መንስኤው ምንድን ነው?

ቶንሲል በተለያዩ ምክንያቶች ሊቆጣ ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ ግን በቫይረስ ወይም ባክቴሪያ ምክንያት በሚመጣ ኢንፌክሽን ይታመማል፡፡ አብዛኛው (25-45%) የሚሆነው የቶንሲል በሽታ በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ሲሆን ባክቴሪያ በተለይም ግሩፕ ኤ ስትሬፕቶኮከስ (Group A streptococcus) የተባለው ባክቴሪያ ቀጣዩን ደረጃ ይይዛል፡፡ የቶንሲል በሽታ መተላለፊያ መንገዶች ከጉንፋን እና መሰል የመተንፈሻ አካላት በሽታ መተላለፊያ መንገዶች ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ እነዚህም በሽታው ያለበት ሰው በሚያስልበት ወይም በሚያስነጥስበት ጊዜ በቅርበት መሆን፣ በቀጥታ ንክኪ ማለትም ንፁህ ባለሆኑ እጆች መጨባበጥ ወይም በተዋህስያኑ ከተበከሉ ግዑዝ ነገሮች ንክኪ ናቸው፡፡

የቶንሲል በሽታ ምልክቶች

የቶንሲል በሽታ ምልክቶች እንደ አምጪው ተዋህስ አይነት ይወሰናል፡፡ በምልክቶች ብቻ በእርግጠኝነት በባክቴሪያ ወይም በቫይረስ ነው የመጣው ብለን መደምደም ባንችልም በአብዛኛው

ከቫይረስ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ቶንሲል በሽታ

  • ቀስ በቀስ የመጀምር
  • አብሮ ተያይዞ ሳል ወይም ጉንፋን መሰል ምልክቶች የማሳየት 
  • የቶንሲል መቅላት እና ማበጥ
  • ቀለል ያለ ትኩሳት፣ ራስ ምታትና ብርድብርድ የማለት ምልክቶችን ያሳያል

በሌላ በኩል በባክቴሪያ ምክንያት የሚመጣ የቶንሲል ህመም

  • በአጭር ጊዜ ውስጥ(በፍጥነት) የመጀመር
  • በከፍተኛ ሁኔታ ለመዋጥ የመቸገር
  • የቶንሲል መቅላት፣ ማበጥና አልፎም መግል የመያዝ
  • አንገት ላይ ያሉ እጢዎች (Lymph nodes) የማበጥ
  • ከፍተኛ የሆነ ራስ ምታት፣ ትኩሳትና ብርድ ብርድ የማለት ምልክቶችን ያሳያል፡፡

ከቶንሲል ህመም ጋር ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉ መዘዞች

አብዛኛው የቶንሲል ህመም ያለ ተያያዥ ቸግሮች ቢድንም በአግባቡ ካለታከመ አንዳንድ ጊዜ የተለያዩ መዘዞችን ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ በባክቴሪያ የሚመጣ የቶንሲል ህመም በቫይረስ ከሚመጣው ይልቅ ከእነኚ መዘዞች ጋር የመያያዝ እድል አለው፡፡ እነኚ ተያያዥ ችግሮች በቀጥታ ከበሽታው ጋር የሚገናኙ ወይም ሰውነታችን በሽታውን ለመከላከል ከሚሰጠው ምላሽ ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በቀጥታ ከበሽታው ጋር የሚገናኙ የምንላቸው መዘዞች

  • ቶንሲል ላይ ያለ መግል በመስፋፋት የአየር መተንፈሻ ቱቦን መዝጋት (ህፃናት ላይ ይበልጥ ይታያል)
  • የሳይነስ ኢንፌክሽን
  • የጆሮ ኢንፌክሽን
  • ማጅራት ገትር
  • አንገት አካባቢ ያሉ ደም ስሮች ኢንፌክሽን

ሰውነታችን በሽታውን ለመከላከል ከሚሰጠው ምላሽ ጋር የተያያዙ ችግሮች ወድያውኑ ወይም ከበሽታው ቆየት ብለው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ይህም የሚከሰተው ሰውነታችን ራሱን ከበሽታው ለመከላከል የሚያመርታቸው ኬሚካሎች (antibodies) ባለማወቅ ቁልፍ የሆኑ የሰውነት ክፍሎቻችንን ሲያጠቁት ነው፡፡ አኪዩት ሪዩማቲክ ፊቨር (Acute rheumatic fever) ደግሞ በዚ መልኩ ከሚመጡት መዘዞች ዋነኛው ነው፡፡ 

አኪዩት ሪዩማቲክ ፊቨር (Acute rheumatic fever)

 ይህ ችግር የሚታየው የቶንሲል ህመም ከዳነ ከ2-3 ሳምንት በላ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ከ5-15 ዓመት ያሉ ታዳጊዎችን ያጠቃል፡፡ ቶንሲል ህመም ታመው ከነበሩ ታማሚዎች 0.5-3% የሚሆኑት ይህ ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡ የችግሩ ምክንያትም የቶንሲል ህመምን የሚያመጣው ባክቴሪያ (Group A streptococcus) ሽፋን ላይ ያለው ኬሚካል (antigen) የተለያዩ የሰውነት አካላችን ላይ ከሚገኘው ኬሚካል (antigen) ጋር ሲመሳሰልና ለባክቴሪያው ታልሞ የተሰራው የመከላክያ ኬሚካል (antibodies) በስህተት የገዛ አካላችንን ሲያጠቃ ነው፡፡ በዚህም ችግር ሊጠቁ የሚችሉት አካላት ልብ፣ አንጎል፣ ቆዳና መገጣጠሚያዎች ናቸው፡፡

 

ምልክቶቹም የሚከተሉት ናቸው 

  • የተለያዩ መገጣጠሚያዎች ህመምና እብጠት 
  • በቆዳ ላይ የሚወጡ ዕብጠቶችና ቀላ ያሉ ሽፍታዎች
  • ታማሚው ሊቆጣጠራቸው የማይችል የፊት፣ የእጅና የእግር  ዳንስ መሰል እንቅስቃሴዎች(ከአንጎል ጉዳት ጋር ተያይዞ የሚመጣ)
  • ትኩሳትና አጠቃላይ የህመም ስሜት

 

እነኚህ ጊዜያዊ ምልክቶች ጥሩ መሻሻል ቢያሳዩም ሁኔታው በተደጋጋሚ የመምጣትና በልብ ውስጥ ያሉት ቫልቮች ላይ ጉዳት በማምጣት ቀስ በቀስ ዘላቂ ለሆነ የልብ ቫልቮች ጉዳትና ልብ ድካም የመዳረግ ዕድል አላቸው፡፡

መፍትሄው

የቶንሲል ህመም በሚያጋጥም ጊዜ አቅራቢያ ወዳለ ጤና ተም መሄድ ያስፈልጋል፡፡ የሚሰጠውም ህክምና ዓላማው

  • አኪዩት ሪዩማቲክ ፊቨር (Acute rheumatic fever) ሳይከሰት በፊት በሽታው ያመጣውን ተዋህስ ማጥፋት- ይህም ፀረ-ተዋህስ መድሃኒቶችን በመስጠት ይታከማል (primary prevention)
  • አኪዩት ሪዩማቲክ ፊቨር (Acute rheumatic fever) ከተከሰተ ከእሱ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ምልክቶችን በማስታገሻና ሌሎች መድሃኒቶች ማከም
  • አኪዩት ሪዩማቲክ ፊቨር (Acute rheumatic fever) ተመልሶ እንዳይመጣና በልብ ቫልቮች ላይ የሚያመጣውን ጉዳት ለመቀነስ የሚደረግ መከላከያ (secondary prevention)- ይህ  በሽታው በልብ ላይ ያለው ጉዳት ታይቶ ከ5 አመት እስከ እድሜ ልክ ድረስ በየወሩ በመርፌ መልክ በሚሰጥ መድሃኒት ይታከማል።

 

በመጨረሻም ቶንሲል በቀዶ ጥገና ስለማስወጣት

 

በቶንሲል ህመም በተደጋጋሚ ከሚጠቁ ታካሚዎች ወይም ከታካሚ ወላጆች የሚደርሰኝ ጥያቄ “ቶንሲሉ በቀዶ ጥገና ቢወጣስ? የሚል ነው፡፡ መልሱ እንደሚከተለው ነው።

 

ቶንሲል በቀዶ ጥገና መወገድ የሚኖርበት ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው።

 

  • ቶንሲል አብጦ ለመተንፈስ፣ ለመመገብ ወይም የእንቅልፍ መተኛት ችግር ካመጣ
  • በመድሃኒት መዳን ያልቻለ መግል ቶንሲል ላይ ካለ
  • ሚነት በቶንሲል ምክንያት የመጣ መጥፎ የአፍ ጠረን
  • የካንሰርነት ጥርጣሬ ሲኖር
  • በተደጋጋሚ ማለትም በ1 ዓመት ውስጥ 7 እና ከዛ በላይ፣ ለ2 ተከታታይ አመታት በዓመት ወስጥ 5 እና ከዛ በላይ፣ ለ3 ተከታታይ አመታት በዓመት ወስጥ 3 እና ከዛ በላይ ኢንፌክሽኖች ካሉ

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg