በዶ/ር ስምዖን ፍትሐአምላክ- በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንየም ሜዲካል ኮሌጅ እጩ ሐኪም
አርትኦት እና እርማት- በዶ/ር ሃብታሙ ሞላ Public Health Specialist
ከመጠን ያለፈ ውፍረት ምንድን ነው?
ከመጠን በላይ ክብደት ወይም ከመጠን በላይ መወፈር ጋር ተያይዞ የሚከሰት ህመም እና ሞት በሂፖክራተስ ዘመን ከ 2500 ዓመታት በፊት ጀምሮ በህክምና ባለሙያዎች ይታወቃል:: ይህ ችግር ከመጠን በላይ የሆነ የሰውነት ስብ በማከማቸት የሚታወቅ የጤና እክል ሲሆን በጤና ላይ አሉታዊ ተጽእኖም ሊያሳድር ይችላል።
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ከመጠን ያለፈ ውፍረትን “ለጤና አደገኛ የሆነ ከመጠን ያለፈ ወይም ያልተለመደ የስብ ክምችት” ብሎ ይገለጻል። የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማእከል (ሲዲሲ) “ለአንድ ቁመት ጤናማ ነው ተብሎ ከሚታሰበው ክብደት በላይ ከመጠን በላይ ውፍረት ወይም ከመጠን በላይ መወፈር” ሲል ይገልጸዋል።
የጉዳዩ ወሰን እና አስፈላጊነት
በአለም አቀፍ ደረጃ በስፋት እየጨመረ የሄደው ይህ ሥር የሰደደ በሽታ ለአብዛኞቹ ሀገራት የጤና መጓደል ትልቅ አስተዋፅዖ አለው።
የአለም ጤና ድርጅት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ እ.ኤ.አ. በ 2016ዓ.ም. በአለም ላይ ዕድሜያቸው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ በሆናቸው አዋቂዎች ፣ 1.9 ቢሊዮን ያክሉ ከመጠን በላይ ክብደት ያላቸው ነበሩ። ከእነዚህ ውስጥ ከ650 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ውፍረት ያላቸው ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ1975 እና 2016 መካከል ያለው የአለም ውፍረት ስርጭት በሦስት እጥፍ ጭማሪ አሳይቷል። ከ1980 ጀምሮ ከመጠን በላይ ውፍረት ከ 70 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ በእጥፍ ጨምሯል። በአጠቃላይ 13% የሚሆነው የአለም አዋቂ ህዝብ (11% ወንዶች እና 15% ሴቶች) በ 2016 ከመጠን በላይ ወፍራም ነበሩ::
ወደ ኢትዮዽያ ሁኔታ ስንመጣ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ጎልማሶች የማእከላዊ ውፍረት ስርጭትን እና መንስኤዎችን በጋራ ለመወሰን የተደረገ ስልታዊ ግምገማ እና ሜታ-ትንተና እንደሚያሳየው አጠቃላይ የማዕከላዊ ውፍረት ስርጭት 37.31% ሲሆን ይህም ከፍ ያለ አኃዝ ነው።
BMI ምንድን ነው?
BMI የሰውነት ብዛት መረጃ ጠቋሚ ማለት ነው። የአንድ ግለሰብ ክብደት እና ቁመት ላይ በመመርኮዝ የሰውነት ስብን የሚያሰላ መለኪያ ነው። የአንድን ሰው ክብደት በኪሎግራም እና ቁመታቸውን ደሞ በሜትር ስኩዌር በማድረግ ከዛም በማካፈል (ኪግ/ሜ 2)ይሰላል። BMI በተለምዶ አንድ ሰው ከክብደት በታች፣ መደበኛ ክብደት፣ ከመጠን ያለፈ ክብደት ወይም ውፍረት መሆኑን ለማወቅ እንደ መመርመሪያ መሳሪያ ነው። BMI ለመለካት ቀላል፣ አስተማማኝ እና ከሰውነት ስብ እና የሰውነት ስብ ስብስብ መቶኛ ጋር የተቆራኘ ነው። BMI የአጠቃላይ የሰውነት ስብን ለመገመት ከሰውነት ክብደት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ግምት ይሰጣል።
ታዲያ ውፍረትን ለመመርመር የሚያስችሉ መስፈርቶች የትኞቹ ናቸው?
የሰውነት ብዛት መረጃ ጠቋሚ (BMI) ምደባዎች የልብና የደም ሥር በሽታ(CVD) ስጋት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በአሜሪካው ብሔራዊ የጤና ኢንስቲትዩት (NIH) እና የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ለነጭ፣ ስፓኒክ እና ጥቁር ግለሰቦች ተቀባይነት ያገኙ ለBMI የሚመከሩ ምደባዎች እኚህ ናቸው፡-
● ከክብደት በታች – <18.5 ኪ.ግ / ሜ 2
● መደበኛ ክብደት – ከ18.5 እስከ 24.9 ኪ.ግ / ሜ2
●ከመጠን በላይ ክብደት – ከ25.0 እስከ 29.9 ኪ.ግ/ሜ2
● ውፍረት – ≥30 ኪ.ግ / ሜ2
• ክፍል I – ከ 30.0 እስከ 34.9 ኪ.ግ / ሜ2
• ክፍል II – ከ 35.0 እስከ 39.9 ኪ.ግ / ሜ2
• ክፍል III – ≥40 ኪግ/ሜ2
ለውፍረት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው?
ዘር፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ለአዋቂዎች የዘር አስተዋፅኦ ከ40 እስከ 70 በመቶ ነው። አንድ ወጣት አንድ ወላጁ/ጇ ከመጠን በላይ ውፍረት ካለው፣ ከመጠን በላይ የመወፈር እድሉ/ሏ ከሌላቸው ጋር ሲነጻጸር ከሶስት እስከ አራት እጥፍ ይጨምራል። ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ሁለት ወላጆች መኖር ደሞ ከ10 እጥፍ በላይ ከመጠን በላይ የመወፈር አደጋ ጋር የተያያዘ ነው።
የማህበራዊ ሁኔታ፡ በሚገርም ሁኔታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ውፍረት ከፍተኛ ገቢ ባላቸው እና ከፍተኛ ትምህርት ባላቸው ሰዎች መካከል ዝቅተኛ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ደሞ ጤናማ ያኗኗር ሁኔታን እንደ አመጋገብ ስርአት ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድርግ(ለምሳሌ የእግረኛ መንገድ እና የመጫወቻ ሜዳ መገኘትን) ከመሳሰሉ የጤና ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።
እድሜ፡ አዋቂዎች ከ20 እስከ 65 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ቀስ በቀስ ክብደት ይጨምራሉ። ከዚያ በኋላ በአብዛኛዎቹ ሰዎች ክብደት ይቀንሳል፣ ይህ የክብደት መቀነስ ግን በከፊል የጡንቻን ብዛት በማጣት ነው።
የአኗኗር ዘይቤ፡ የአኗኗር ዘይቤዎች፣ እንደ አመጋገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (እና እንቅስቃሴ-አልባነት)፣ የእንቅልፍ ሁኔታ እና ሲጋራ ማጨስ ማቆም፣ ሁሉም ከክብደት መጨመር ጋር የተያያዙ ናቸው።
መድሐኒቶች፡ አንዳንድ የሳይኮሲስ መድኃኒቶች፣ ፀረ-ጭንቀቶች፣ ለመጣል ብሽታ የሚሰጡ መድኃኒቶች፣ ፀረ-ስኳር መድኃኒቶች እና የሆርሞን የወሊድ መከላከያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የተለመዱ መድኃኒቶች ከክብደት መጨመር ጋር ይያያዛሉ።
አንዳንድ የጤና እክሎች፡ የተወሰኑ የህክምና ሁኔታዎች እንደ ሃይፖታይሮዲዝም፣ ኩሺንግ ሲንድረም፣ ሃይፖታላሚክ ድክመቶች (ማለትም፣ ሃይፖታላሚክ ከመጠን ያለፈ ውፍረት የምንለው) እና የእድገት ሆርሞን እጥረትን ጨምሮ ከክብደት መጨመር ጋር ሊገናኙ ይችላሉ።
ከውፍረት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና አደጋዎች ምን ምን ናቸው?
1. የስኳር በሽታ
2. በደም ውስጥ ያለ የስብ መጠን መዛባት
3. ደም ግፊት
4. የልብ በሽታ
5. ስትሮክ
6. የደም መላሽ የደም ስር ውስጥ ደም መርጋት እና መሰንቀር
7. ካንሰር
8. የአጥንት እና መገጣጠሚያ ብግነት(Osteoarthritis)
9. ሪህ(Gout)
10. የሃሞት ከረጢት በሽታ እና ከአልኮል ጋር ያልተያያዘ የሰባ ጉበት በሽታ(nonalcoholic fatty liver disease)
11. የቃር በሽታ (GERD)
12. የስነ ተዋልዶ ችግሮች
13. የኩላሊት በሽታ
14. የኩላሊት ጠጠር
15. ሽንትን መቆጣጠር ያለመቻል በሽታ
16. ድባቴ
17. በእንቅልፍ ወቅት የትንፋሽ መቋረጥ(Obstructive sleep apnea)
18. አስም
19. ከቀዶ ጥገና በኋላ፣ በሆስፒታል ቆይታ፣ የመተንፈሻ አካላት፣ የቆዳ እና የጡንቻ ኢንፌክሽኖች
20. ሞት
ከመጠን ያለፈ ውፍረት በህይወት ጥራት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንድን ነው?
● በራስ መተማመን እና የሰውነት ምስል ላይ ተጽእኖዎች
● ከመጠን በላይ መወፈር ሰዎች ለራስ የሚሰጡት ግምት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል። ህብረተሰቡ ብዙውን ጊዜ ከመጠን በላይ ውፍረትን ያቃልላል፤ ይህም ወደ አሉታዊ አመለካከቶች፣ መድልዎ እና ማህበራዊ መገለል ያመጣል። እራስን ከማህበረሰቡ የውበት እና የቀጭን ልኬቶች ጋር ያለማቋረጥ በማነፃፀር የብቃት ማነስ እና ራስን መተቸትን ያስከትላል። እነዚህ ልምዶች ከመጠን በላይ ውፍረት ያለባቸው ሰዎች በክብደታቸው ምክንያት ለራስ ዝቅ ያለ ግምት፣ እፍረት እና ደካማ የሰውነት ገጽታ ስሜት እንዲሰማቸው አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
● ማህበራዊ መገለል እና መድልዎ
● ከመጠን በላይ ውፍረት ያለባቸው ሰዎች በክብደታቸው ምክንያት ብዙውን ጊዜ ለመገለል ይጋለጣሉ። ይህ መገለል በትምህርት፣ በሥራ እና በጤና አጠባበቅ እና በሌሎችም ዘርፎች ይታያል። ከመጠን በላይ ውፍረት ያለባቸው ሰዎች አካላዊ ብቃት እና ተክለ ቁመና በሚሹ ስራዎች ላይ ለመቅጠርም አድልዎና መገለል ይደርስባቸዋል።
● ከመጠን ያለፈ ውፍረት-ነክ የጤና እንክብካቤ ወጪዎች ኢኮኖሚያዊ ሸክም
● ከመጠን ያለፈ ውፍረት እና ከመጠን በላይ መወፈር-ነክ የጤና ሁኔታዎችን ማከም ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ሸክምን ይፈጥራል። ከቀጥታ የጤና እንክብካቤ ወጭዎች በተጨማሪ ሌሎች ወጪዎችም አሉ። ለምሳሌ ያክል ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ሰዎች ዝቅተኛ የስራ ምርታማነት እና ዝቅተኛ የቤተሰብ ገቢ ይኖራቸዋል። እ.ኤ.አ. በ 2017 ውፍረት ዩናይትድ ስቴትስን 1.4 ትሪሊዮን ዶላር ወጪ እንዳስወጣት ተገምቷል።
ክብደትን ለመቀነስ ምን ዓይነት የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ሊረዱኝ ይችላሉ?
● የተመጣጠነ አመጋገብ እና አመጋገብ ቁጥጥር
● መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ማካተት
● ክብደትን ለመቆጣጠር ከጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ድጋፍ መፈለግ
ክብደትን ለመቀነስ ምን ዓይነት የአመጋገብ ለውጦች ሊረዱኝ ይችላሉ?
የተመጣጠነ አመጋገብ እና አመጋገብ ቁጥጥር ከመጠን በላይ ውፍረትን ለመከላከል እና አጠቃላይ ጤናን ለመጠበቅ ወሳኝ ናቸው። እንደ ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ ፕሮቲኖች፣ እህሎች እና ጤናማ ቅባቶች ባሉ ንጥረ-ምግቦች ላይ በማተኮር፤ ሰዎች የካሎሪ መጠንን በሚቆጣጠሩበት ጊዜ ለሰውነታቸው አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ብቻ መስጠት ይችላሉ። የምግብ መጠን ቁጥጥርም ከመጠን በላይ መብላትን ለመከላከል ስለሚረዳ እና ሰዎች ለኃይል ፍላጎታቸው ተገቢውን የካሎሪ መጠን እንዲወስዱ ስለሚያደርግ እንዲሁ አስፈላጊ ነው።
ከዚህም በላይ የተመጣጠነ አመጋገብ እና አመጋገብ ቁጥጥር ከመጠን በላይ ውፍረትን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ጤና እና ደህንነት አስተዋጽኦ ያደርጋል። የተመጣጠነ የሜታቦሊዝም ተግባርን በመደገፍ፣ ረሃብን እና ጥጋብን በመቆጣጠር እና እንደ የልብና የደም ሥር (cardiovascular) በሽታ፣ ዓይነት 2 የስኳር በሽታ እና አንዳንድ የካንሰር አይነቶች ያሉ ሥር የሰደዱ በሽታዎችን የመጋለጥ እድልን በመቀነስ የተመጣጠነ አመጋገብ ለጤናማ ህይወት መሰረት ይጥላል። ጤናማ የአመጋገብ ልማዶችን እና ጥንቃቄ የተሞላበት የአመጋገብ ልምዶችን ማዳበር ግለሰቦች ጤናቸውን እንዲቆጣጠሩ፣
ጤናማ ክብደት እንዲኖራቸው እና ለሚመጡት አመታት በተመጣጠነ እና ገንቢ አመጋገብ ጥቅሞችን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
1. በቀስታ ለመብላት ይሞክሩ። ብዙ ጊዜ ትናንሽ ምግቦችን ይመገቡ። ምግቦችን አትዝለሉ።
2. በቤትዎ እና ከቤት ውጭ በሚመገቡበት ጊዜ መጠኑን ያስተውሉ። ከቤት ውጭ በሚመገቡበት ጊዜ ከሌላ ከአንድ ሰው ጋር ያዘዙትን ምግብ ይካፈሉ ወይም በኋላ ለመብላት ግማሹን ወደ ቤት ያምጡ።
3. ለምግብ መመገቢያ ትንሽ ሳህን መጠቀም። የምግብ መጠንን ለማወቅ የመለኪያ ኩባያ ይጠቀሙ።
4. ለምግብ እና ለመክሰስ አስቀድመው ያቅዱ። በምግብ መካከል በተራቡ ጊዜ ጤናማ ምግቦችን (እንደ ጥሬ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ለውዝ) ያዘጋጁ።
5. ከምግብ በፊት እና በኋላ ውሃ ይጠጡ። ይህ ተጨማሪ ካሎሪዎችን ሳይጨምሩ የሙሉነት ስሜት እንዲሰማዎት ይረዳዎታል።
6. በእያንዳንዱ ማዕድ ፕሮቲን ይመገቡ። ይህ የበለጠ የጥጋብ ስሜት እንዲሰማዎት ሊያደርግ ይችላል።
7. ክብደት ለመቀነስ በሚሰሩበት ጊዜ ጓደኛዎ ወይም የቤተሰብዎ አባል ድጋፍ እንዲሰጥዎት ያድርጉ። እንዲሁም ከጤናማ አመጋገብ እቅድዎ ዝንፍ ላለማለት ይሞክሩ።
ክብደትን ለመቀነስ በምሞክርበት ጊዜ የትኞቹን ምግቦች እና መጠጦች ማስወገድ አለብኝ?
● ኩኪሶዎችን፣ ኬኮችን፣ ከረሜላዎችን፣ ዶናትቶችን፣ ግራኖላዎችን፣ የተጋገሩ ምርቶችን፣ ሙፊኖችን፣ ቺፖሶችን፣ ክራከርን፣ የተዘጋጀ ሩዝ፣ ፓስታ እና ድብልቅ ነገሮችን ያስወግዱ።
● የታሸጉ አትክልቶችን እና የታሸጉ ፍራፍሬዎችን ያስወግዱ ።
● ሙሉ ቅባት ያላቸው የወተት ተዋጽኦዎችን፣ ቅቤን እና የአሳማ ስብን ያስወግዱ።
● ከፍተኛ ቅባት ያላቸውን ስጋዎች እንደ የበሬ ሥጋ፣ በግ፣ እንደ ቦሎኛ፣ ፔፐሮኒ ወይም ሳላሚ ያሉ ስጋዎችን ያስወግዱ።
● ሙሉ-ቅባት ማዮኒዝ እና የሰላጣ ማዘጋጃ ቅባቶችን ያስወግዱ
● እንደ ሶዳ፣ ጭማቂ እና ጣፋጭ ሻይ ያሉ ጣፋጭ መጠጦችን ያስወግዱ። ቢራ፣ ወይን እና የተቀላቀሉ መጠጦችን ጨምሮ አልኮልን ያስወግዱ ወይም ይገድቡ። ሰው ሰራሽ ጣፋጮችን ያስወግዱ። የኃይል መጠጦችን ያስወግዱ።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሳደርግ ምን ማድረግ አለብኝ?
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ስላለው ውፍረትን በመከላከል ረገድ ወሳኝ ነው። በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ ሰዎች ካሎሪዎችን ማቃጠል ብቻ ሳይሆን የሰውነት ዑደታቸውን ያሻሽላሉ ፣ ጉልበትን በብቃት መጠቀም ይችላሉ እና ክብደትን ለመቆጣጠር ይችላሉ ። ከዚህም በላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የጡንቻን ብዛት በመገንባት ለሰውነት ስብጥር መሻሻል አስተዋጽኦ ያደርጋል ይህም የሜታቦሊክ ፍጥነትን ይጨምራል እና አጠቃላይ የሰውነት ቅርፅን ያስተካክላል።
በተጨማሪም መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የምግብ ፍላጎትን በመቆጣጠር ፣የሆድ ስብን በመቀነስ እና የሜታቦሊክ ጤናን ለማሻሻል ወሳኝ ሚና ይጫወታል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የምግብ ፍላጎት ሆርሞኖችን ለመቆጣጠር፣ ምኞቶችን ለመቅረፍ እና የተሻሉ የምግብ ምርጫዎችን ለማስተዋወቅ ይረዳል። በተጨማሪም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ በተለይም የኤሮቢክ ስልጠና፣ በውስጣዊ አካላት ላይ የሚገኝ ስብ ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ይህም እንደ ዓይነት 2 የስኳር በሽታ እና የልብና የደም ሥር (cardiovascular) በሽታዎች ካሉ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ጋር የተያያዙ የጤና ሁኔታዎችን አደጋን ይቀንሳል። በአጠቃላይ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ማካተት ክብደትን ለመቆጣጠር ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ጤናን እና ደህንነትን ለማስተዋወቅ አስፈላጊ ነው።
ስለዚህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ጊዜ እነዚህን ቅደም ተከተሎች መተግበር ይችላሉ።
1. ማሟሟቅ – ሰውነትን ማሞቅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ጊዜ ጡንቻዎትን እንዳይጎዱ ይረዳዎታል። ለማሞቅ ቀላል የኤሮቢክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ (ለምሳሌ በዝግታ መራመድ) ወይም ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ድረስ ማፍታታት እንቅስቃሴ።
2. እንቅስቃሴ ያድርጉ – የኤሮቢክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን፣ የጡንቻ ማጠናከሪያን እና የማሳሳብ እንቅስቃሴዎችን በማሰባጠር የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ ይቻላል። በኤሮቢክ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወቅት በፍጥነት መራመድ፣ መዋኘት፣ መሮጥ ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማሽን መጠቀም ይቻላል። ሌሎች እንቅስቃሴዎች፣ እንደ ዳንስ ወይም ቴኒስ መጫወት፣ የኤሮቢክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዓይነቶች ናቸው። እንዲሁም አንገትዎን፣ ትከሻዎን፣ ጀርባዎን፣ ዳሌዎን እና ጉልበቶቻችሁን ጨምሮ ሁሉንም መገጣጠሚያዎችዎን ለማሳሳብ ጊዜ መስጠት አለብዎት። በሳምንት ቢያንስ 2 ጊዜ ደሞ የጡንቻ ማጠናከሪያ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይችላሉ።
3. ማቀዝቀዝ – ማቀዝቀዝ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካደረጉ በኋላ የማዞር ስሜት እንዳይሰማዎት እና የጡንቻ መኮማተርን ለመከላከል ይረዳል። ለማቀዝቀዝ, ለ 5 ደቂቃዎች ማሳሳብ ወይም ቀላል የኤሮቢክ ልምምድ ማድረግ ይችላሉ።
ክብደትን ለመቀነስ ሕክምናስ ምን ይረዳኛል?
አንዳንዴ በሐኪም የታዘዙ የክብደት መቀነሻ መድሃኒቶች የምግብ ፍላጎትን በመቀነስ ወይም የምግብ መፈጨት ዘዴን በመቀየር ይሰራሉ። እነዚህ መድኃኒቶች ሊሰጡ የሚችሉት አንድ ሰው ክብደቱን በሌሎች መንገዶች መቀነስ ካልቻለ እና ይሄው ሰው፡-
● BMI 30 ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ፣ ወይም
● BMI በ27 እና 29.9 መካከል ሆኖ እና ከክብደት ጋር የተገናኙ የህክምና ችግሮች፣እንደ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም ወይም የደም ግፊት ካሉበት ነው።
ምንም እንኳን ዶክተሮች ክብደትን ለመቀነስ የሚረዳ መድሃኒት ቢያዝዙም፤ ከመጠን በላይ ውፍረት ያለባቸው ሰዎች ሁሌም የአኗኗር ለውጦችን እንዲያደርጉ ይመክራሉ። ምክንያቱም እኚህ የአኗኗር ለውጦች አጠቃላይ ጤንነትን ለማሻሻል ስለሚረዱ ነው።
ብዙ የእፅዋት ክብደት መቀነስ መድሃኒቶች አይሰሩም ብሎም አንዳንዶቹ ደህንነታቸው ያልተጠበቀ ነው። ማንኛውንም ከዕፅዋት የተቀመሙ የክብደት መቀነስ መድኃኒቶችን ከመውሰድ በፊት ሐኪምን ወይም ፋርማሲስትን ማነጋገር ልብ ይሏል።
ለክብደት መቀነስ የቀዶ ጥገና ሂደቶችም አሉ። እነዚህም የሚሰሩት የታካሚውን ሆድ ትንሽ በማድረግ ነው። አንዳንድ የቀዶ ጥገና ዓይነቶች ምግብ በምግብ መፍጫ ሥርዓት ውስጥ የሚወስደውን መንገድ ይለውጣሉ። ስለዚህ ሰውነታችን ከምግብ ውስጥ ጥቂት ካሎሪዎችን እና ንጥረ ነገሮችን ለመውስድ ይገደዳል ማለት ነው። ነገር ግን የክብደት መቀነስ ቀዶ ጥገና ለሁሉም ሰው አማራጭ አይደለም።
ዋቢዎች
1. https://www.frontiersin.org/articles/10.3389/fendo.2022.983180/full
2. UpToDate