በዶ/ር ተስፋዬ ብርሃኑ(ጠቅላላ ሐኪም- ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መምህር)

Reviewed by- Dr. Lemma Zewde, Internal Medicine

 

መግቢያ

ጉበት ትልቁ የሰውነት ክፍል ሲሆን ከ1-1.5 ኪግ ይመዝናል። ጉበት በጅማቶችና አያያዥ ሕዋሳት አማካይነት በጨጓራ፣ አንጀት፣ ድልሺ፣ እና ትላልቅ ደም ሥሮች ተከቦ በቀኝ የላይኛው ሆድ ክፍል ውስጥ ከታችኞቹ የጎድን አጥንቶቻችን ሥር ይገኛል።

1/4ኛው ከልብ የሚረጨው ደም ለጉበት ይላካል። ጉበት በሰውነታችን ውስጥ የሚከናወኑ አጸግብሮቶችን ሚዛን(Homeostasis) በመጠበቅ ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው። ይህም እጅግ አስፈላጊ ፕሮቲኖች(አልቡሚን፣ ሆርሞንና ኢንዛይም ተሸካሚ ንጥረነገሮች፣ ለደም እርጋታ ለእድገት እና ለዑደተሕይወት የሚጠቅሙ)፣ ሃሞት ያመርታል፣ የሰውነት የሥኳር እና የስብ መጠን ይቆጣጠራል።

 

የጉበት በሽታ ሥርጭት

የጉበት በሽታ በ2020 በዓለም ዙሪያ ወደ 1.5 ቢሊዮን የሚጠጉ ግለሰቦችን የጎዳ ዓለም አቀፍ የህዝብ ጤና ችግር ነው። CLD የተለያዩ መንስኤዎች ሲኖሩት ሥር የሰደደ  አልኮል ተጠቃሚነት፣ የቫይረስ ሄፓታይተስ ቢ፣ ሲ እና ዲ ኢንፌክሽኖች፣ አልኮሆል ያልሆነ የስብ ጉበት በሽታ (NAFLD)፣ ግለመድኅን የጉበት ብግነት እና ድኅረ መድኃኒት የጉበት ጉዳት ዋነኛ መንስኤዎች ሲሆኑ በሃገራችን ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ዋና ዋና መንስኤዎች መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ።

በዚህ ጽሑፍ ያለ መጠን በተወሰደ መድኃኒት ምክንያት ስለሚከሰት የጉበት መጎዳት ዳሰሳ እናደርጋለን።

 

ድኅረ-መድኃኒት ጉበት ጉዳት/ ዲሊ(DILI) ምንድነው?

ለተለያዩ በሽታዎች በሐኪም ማዘዣ ሊሆን ይችላል ያለ ማዘዣ የወሰድናቸው መድኃኒቶች እንዲሁም ከእጽዋት የተቀመሙ የባህል መድኃኒቶች ጉበት ላይ ጉዳት ሲያስከትሉ የሚገጥመን የጤና ዕክል ነው። ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶችን እንደ መድኃኒትነት መጠቀሙ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት የመጣ ሲሆን ከብዙ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በታሪክ ማስረጃዎች ተመዝግቧል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምዕራባውያን ማህበረሰቦች ውስጥ ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶች  አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል። በተለይም ለሰውነት ግንባታ ፣ ክብደት ለመቀነስ እና “ጥሩ ጤና”ን ለመጠበቅ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው። ይህም በሕዝቡ ውስጥ በሰረጸው ምርቶቹ ተፈጥሯዊ ስለሆኑ ምንም ጉዳት የላቸውም በሚል  የተሳሳተ  እምነት ስለተደገፈ ነው። በተቃራኒው ግን ከዕፅዋት የተቀመሙ ምርቶች ከፍተኛ የጎንዮሽ ጉዳቶችን እንደፈጠሩ ጥናቶች ያሳያሉ።  ከእነዚህም መካከል ንቅለተከላ የሚያስፈልገው ወይም ለሞት የሚዳርግ አጣዳፊ የጉበት ጉዳት በዋናነት ተደጋግሞ ተገልጿል::

 

የዲሊ መንስኤዎች

ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶች ጋር የተዛመደ የጉበት ብግነት በምዕራባውያን አገሮች ውስጥ ሁለተኛው በጣም የተለመደው ድኅረ-መድኃኒት የጉበት ጉዳት (DILI) ሲያስከትሉ በምስራቁ  ክፍል ውስጥ ደግሞ ዋነኛ የዲሊ መንስኤ ናቸው። ለቲቢ፣ እችአይቪ/ኤድስ፣ ካንሰር፣ ለአእምሮ  እና ለሌሎችም ሕመሞች የሚታዘዙ መድኃኒቶች በዋናነት ሲጠቀሱ ያለማዘዣ የሚወሰዱ የሕመም ማስታገሻዎችም ፓራስታሞልን ጨምሮ ተጠቃሽ ናቸው።

 

የዲሊ ምልክቶችና ምርመራው

የዓይን ቢጫ መሆን/መደፍረስ፣ ትንሽ እንደተንቀሳቀሱ የድካም ስሜትና መዛል፣ ማሳከክ፣ የቀኝ ላዕላይ ሆድ ክፍል ህመም፣ ደም ማስመለስ፣ ከሆድ የሚጀምር የሰውነት ዕብጠት፣ የሰገራ እና የሽንት ቀለም መቀየር፣

ሐኪሞች ያልታወቀ የጉበት ጉዳት ያለበትን ሕሙም ሲገመግሙ  ሁል ጊዜ ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶችን መጠራጠር አለባቸው።

የደም ምርመራ እና አልትራሳውንድ ምርመራ እንዳስፈላጊነቱ ይታዘዛል።

 

ዲሊ ሊያስከትል የሚችለው ውስብስብ የጤና እክል ምንድነው

  • ድንገተኛና አደገኛ የጉበት መድከም(Fulminant hepatic failure)
  • ሥር የሰደደ የጉበት በሽታ(Chronic liver disease)
  • የመጨረሻ ደረጃ የጉበት መኮማተር(Cirrhosis) 

 

ሕክምናው

ሕመምተኛው የወሰደውን መድኃኒት ወይም የተጠቀመውን ዕጽ የመርዛማነት ክብደት ቀድሞ ማወቅ ሊያስከትል የሚችለውን የጤና ዕክል ደረጃ ለመተንበይ እና አጣዳፊ የጉበት ድካምን ለመከታተል ይረዳል። በመድኃኒት/በዕጽ ምክንያት ለሚመጣው የጉበት ጉዳት ዋናው የሕክምና ዘዴ መድኃኒቱን/ዕጹን ከመጠቀም ማቋረጥ ነው።

አስከፊ ጉዳት ካስከተለ ግን  ድጋፍ ሰጪ ሕክምና ያስፈልጋል። ከዛም ከባሰ የጉበት ንቅለተከላ ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል።

 

መከላከያ መንገዱ

ጉበትን ሊጎዱ የሚችሉ አልኮል እና ሌሎች መድሃኒቶችን ያስወግዱ –

የመጨረሻ ደረጃ የጉበት መኮማተር(Cirrhosis) በሽታ ያለባቸው ሰዎች ጉበትን እንደሚጎዱ ከሚታወቁ ነገሮች ሁሉ መራቅ አለባቸው።

ማለትም

  • ከአልኮል
  • ስቴሮይድ ካልሆኑ ፀረ-ብግነት መድኃኒቶች(NSAIDs) ለምሳሌ ጎፈን(ibuprofen, naproxen)
  • እንደ ካቫ ያሉ አንዳንድ ማሟያዎች እና ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶች
  • ትኩሳት ፣ ህመም እና ሌሎች የተለመዱ በሽታዎችን ለማከም ብዙ የሚገዙ እና በሐኪም የታዘዙ መድሃኒቶች አሲታሚኖፌን ይይዛሉ። ስለሆነም ፓራሴታሞል/ፓናዶል (acetaminophen)  በቀን ከ2 ግራም በላይ መውሰድ የለባቸውም።

ጉበትን ለመከላከል የሚወሰዱ ክትባቶች—— የሄፐታይተስ ኤ እና ቢ መከላከያ የሆኑ ክትባቶች በጉበት ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ይረዳሉ። ኢንፌክሽኖች በተለይ በሲሮሲስ በተያዙ ሰዎች ላይ ከባድ ሊሆኑ ስለሚችሉ፣ ከጉንፋን የሚከላከሉ ክትባቶችን (በዓመት አንድ ጊዜ)፣ የሳንባ ምች (ቢያንስ አንድ ጊዜ)፣ ዲፍቴሪያ እና ቴታነስ (በ10 ዓመት አንዴ) እና ሌሎች ክትባቶችን መውሰድ አስፈላጊ ነው።

 

ማጠቃለያ

ከዕፅዋት የተቀመሙ መድኃኒቶች በምስራቃውያን ዘንድ  የተለመዱ የሕክምና አማራጮች ናቸው።  በምዕራባውያን አገሮችም ተወዳጅነትን እያገኙ ነው። በኢትዮጵያም በጥናት የሰፈረ ነገር ባላገኝም ተጠቃሚው ማኅበረሰብ ብዙ እንደሚሆን እሙን ነው። ይህም  ከጎንዮሽ-ጉዳት ነፃ እንደሆኑ ስለሚቆጠር ነው። በተቃራኒው ግን አደገኛ የጉበት ብግነትን ጨምሮ ከባድ መርዛማነት ከአጠቃቀማቸው ጋር ተያይዞ ሪፖርት ተደርጓል። ለቲቢ፣ ኤችአይቪ፣ ካንሰር፣ እና ሌሎችም በሽታዎች መድኃኒት ሲጠቀሙ ክትትል ማድረግ፣ ከሐኪም ትዕዛዝ ውጭ መድኃኒቶችን አለመጠቀም፣ የቤት ውስጥ የጤና መፍትሄዎችን በመጠኑ መጠቀም፣ ለጤና ዕክልዎ ከባሕል ሕክምና በፊት ወደ ጤና ተቋም ጎራ ማለት ባህልዎ ይሁን የጽሑፉ መልእክት ነው።

 

ዋቢዎች

  1. Uptodate 2023
  2. Harrison principles of internal medicine, 21st edition
  3. https://doi.org/10.1155/2021/8740157
  4. https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC4561772/#:~:text=Herbal%20medicine%2Drelated%20hepatotoxicity%20represents,to%20dietary%20supplements%5B11%5D