Written by :Anan Asefa (jimma university,C2)

Reviewed by: Dr. Binyam Yohannes Colorectal Surgery Fellow at Saint Paul’s Hospital Millennium Medical Collgee

 

 

ትርፍ አንጀት ምንድን ነው?

ትርፍ አንጀት (appendix) በታችኛው የሆድ ክፍል በቀኝ በኩል የሚገኝ ቀጠን ያለ ቱቦ መሰል አካል ሲሆን በትልቁ አንጀት የመጀመሪያ ክፍል ላይ ይገኛል ።

በርግጥ ትርፍ አንጀት የሚለው ስያሜ የተሳሳተ ትርጉምን የሚሰጥ ነው። ምክንያቱም “ትርፍ” ይባል እንጂ ለሰውነታችን በሽታ ተከላካይ ህዋሳት እንደ መኖሪያ ያገለግላቸዋል። በመሆኑም ጠቃሚ የሰውነት ክፍል ነው። ይህ የአንጀት ክፍል በተለያዩ ተህዋስያን ሲጠቃና ተፈጥሮአዊ ክፍተቱ ሲደፈን ህመም ይፈጥራል። ይህም የትርፍ አንጀት ህመም ይባላል።

የትርፍ አንጀት ህመም እንዴት ይከሰታል?

  • በባዶ ሆድ ሰውነት መታጠብ ለትርፍ አንጀት ህመም ይዳርጋል የሚለው እሳቤ በተለምዶ የሚነገር አገላለፅ እንጂ በሳይንሳዊ ትንታኔ የተረጋገጠ አይደለም።
  • የትርፍ አንጀት ህመም በዋናነት የሚከሰተው ትርፍ አንጀት (appendix) በልዩ ልዩ ተህዋሲያን ሲጠቃና በውስጡ ያለው ተፈጥሮአዊ ክፍተት ሲደፈን ነው። ትርፍ አንጀት ከሌሎች የአንጀት ክፍሎች አንፃር ጠባብ ክፍተት ስላለው በቀላሉ እንዲደፈን ያደርገዋል ።
  •  ክፍተቱ እንዲደፈን የሚያደርጉ ምክንያቶች መሀል በትልቁ አንጀት ውስጥ ያለው ደረቅ አይነምድር (fecolith) ወይም የአንጀት ውስጥ እጢዎች (lymph nodes) ማበጥ ሊሆን ይችላል ።
  • ትርፍ አንጀት ሲደፈን በውስጡ ለጥገኛ ተህዋስያን ምቹ መኖሪያን ይፈጥራል። በተፈጥሮ በአንጀት ውስጥ የሚገኝ ባክቴሪያን ጨምሮ ሌሎች በሽታ አምጪ ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶች እና ሌሎች ጥገኛ ትላትሎች  በውስጡ መራባት ይጀምራሉ። በተለይ ጋዝ አመንጪ ባክቴሪያዎች የሚለቁት ጋዝ እና በተፈጥሮ አንጀት የሚያመነጨው ወፍራም ፈሳሽ ትርፍ አንጀት ውስጥ ግፊት በመፍጠር የትርፍ አንጀት ግድግዳ እንዲለጠጥ ያደርጋል ።
  • አብዛኛውን ግዜ የሆድ  ህመም በዚህ ወቅት ይጀምራል። ግፊቱ በዚሁ ከቀጠለም የትርፍ አንጀት ግድግዳ የደም ስሮችን በመዝጋት የትርፍ አንጀት ህዋሳት የኦክስጅንና የንጥረ ነገር እጥረት እንዲገጥማቸው ይደረጋል ። ባስ ሲልም ህዋሳቱ እንዲሞቱና አንጀት ውስጥ ያለው ይዘት በሆድ ውስጥ እንዲቀላቀልና ከፍተኛ የተህዋስያን ስርጭት በሰውነት ውስጥ እንዲከሰት ያደርጋል። ይህ የሚሆነው ህመሙ በጀመረ ከ 48-72 ሰአታት ብለው ግዜ ውስጥ ነው ።
  • ትርፍ አንጀት እንድትፈርጥ የሚያደርጉት ምክንያቶች ደግሞ አፋጣኝ ህክምና አለማግኘት ፣ የታማሚው ሰው የጤና ሁኔታ (እንደ ስኳር ህመም ) ፣ እድሜ (ህፃናት እና አዛውንት ) ናቸው።

ምን ያህል ስዎችን ያጠቃል ?

ይህ ህመም በአለም ላይ ዋነኛ የማህበረሰብ ጤና  ጠንቅ እየሆነ መጥቷል። እኤአ በ 2019 ዓ .ም የተደረገ ጥናት ከ100,000 ሰዎች መሀል 8.7 % ሰዎች በዚህ ህመም እንደሚያዙ ያመለክታል። በዚህም  የህመሙ ስርጭት ከ1990-2019 እ.ኤ.እ ብለው ግዜ የ 20.8% ጭማሪ አሳይቷል ።

ለትርፍ አንጀት ህመም ምን ያጋልጣል?

ለትርፍ አንጀት ህመም ተጋላጭ የሆኑት አብዛኛውን ግዜ በ20ዎቹ እድሜ የሚገኙ ወጣቶች እና ታዳጊ ልጆች ቢሆኑም በማንኛውም የእድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን ሊይዝ ይችላል ። አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ በትርፍ አንጀት ህመም የመያዝ  እድሉ ወደ 8% አካባቢ ነው( ወንዶች በተወሰነ ደረጃ የመጠቃት እድላቸው ከፍ ይላል)

ምልክቶች

የትርፍ አንጀት ህመም ድንገተኛ የሆድ ህመምን  ከሚያስክትሉ ህመሞች መሀል አንዱ ነው። ይህ ህመም በቀኝ ሆድ አካባቢ ላይ ወይም ከእንብርት ጀምሮ ወደ ቀኝ የሆድ ክፍል የሚዛመት ሊሆን ይችላል ። ህመሙ እየበረታ የሚሄድ ሲሆን መንቀሳቀስ፣ ማሳል፣  ማስነጠስ፣ ሆድን መንካት ፣ ባስ ሲልም መተንፈስ ሳይቀር ህመሙ እንዲባባስ ያደረጋሉ።

ከሆድ ህመም ውጪ የዚህ ህመም ምልክቶች ማስቀመጥ፣ ማስመለስ፣ ትኩሳት፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ የሆድ ድርቀት ውይም የሆድ መነፋትን ሊያሳይ ይችላል ።

ምርመራ

የዚህ ህመም ምርመራ የሚካሄደው የህመሙን ሁኔታ፣መቼ እንደጀመረ ፣ የቀድሞ አጠቃላይ የጤና ሁኔታን በመጠየቅ እና አካላዊ ምርመራ በማድረግ ነው። በተጨማሪ ደግሞ የደምና የሽንት ምርመራ ፣ አልትራሳውንድ ፣ ሲቲ ስካን ውይም ኤም አር አይ ሊታዘዝ ይችላል ።

እንዴት ይታከማል?

  • ህክምናው በአብዛኛው ቀዶ ጥገና የሚጠይቅ የሆድ ህመም አይነት ነው ። ምክንያቱም ህመሙ በድንገት የሚከሰት እና አጣዳፊ በመሆኑ እና በቶሎ ካልታከመ  ለውስብስብ የጤና መታወክ ስለሚዳርግ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቀዶ ጥገናው የሚከናወነው በላፓራስኮፒ እየሆነ መቷል ። ይህም በፍጥነት ለማገገም ይረዳል።
  • ቶሎ ከህመሙ ለማገገም የሚረዳው ወሳኙ ነገር  አፋጣኝ ህክምና ማግኘት ነው ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ትርፍ አንጀት ከፈረጠች  ረጅም የማገገሚያ ግዜን ይወስዳል። የሆድ ተህዋሲያን ስርጭት እና እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳት ሊያስከትልም ይችላል ።

ትርፍ አንጀት  በቀዶ ጥገና ከወጣ በኋላ ያለ ችግር መኖር ይቻላል ።

የትርፍ አንጀት ህመም ቶሎ ከታከመ የሚድን በመሆኑ ከላይ የተዘረዘሩ ምልክቶችን ካስተዋሉ በፍጥነት በአቅራቢያዎ ውደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ህክምና ማግኘት ያስፈልጋል ።

ያስተውሉ ፡- ሀኪም ጋር ከመቅረቦ በፊት  ህመሙን ለማስታገስ ምንም አይነት መድሃኒት ባይወስዱ ይመከራል። ይህም ሀኪሙ ትክክለኛ የህመሙን ልክ በመመልከት የትርፍ አንጀት ህመሙ ቶሎ ተደርሶበት እንዲታከም ስለሚረዳ ነው ።

 

 

 

Reference

Sabiston textbook of surgery 20th edition

 

“The global, regional, and national burden of appendicitis in 204 countries and territories, 1990–2019: a systematic analysis from the Global Burden of Disease Study 2019 – PMC” https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC9945388/

 

“Appendicitis | Johns Hopkins Medicine” https://www.hopkinsmedicine.org/health/conditions-and-diseases/appendicitis