Written by: ሀና ወንዳለ (Medical Intern ጎንደር ዩኒቨሲቲ)
Reviewed by: Dr. Lidya Million( Pediatrics Specialist)
አብዛኛዎቻችን በምንኖርበት አካባቢ የወለደች እናት ለመጠየቅ ስንሄድ “ህፃኑ ቢጫ ሆኖ ማሞቂያ ገባ” ሲባል ሰምተን ይሆናል። ለመሆኑ ይህ ነገር ምንድነው? እንዴትስ ይከሰታል?
ከስሙ እንደምንረዳዉ በጨቅላ ህፃናት ላይ የሚከሰት ቢጫ መሆን የአይናቸዉ ነጩ ክፍል ላይ ገፉም ሲል ደግሞ የ ሰውነታቸውቆዳ ቀለም መቀየር ሲሆን ፤ በተለምዶ ቢጫ መሆን ቢባልም ቀለሙ ከቢጫ እስከ ብርቱካናማ እና ወደ አረንጓዴ የተጠጋ ሊሆን ይችላል። ይህ ክስተት ልጆች በተወለዱ በአንድ ሳምንት ዉስጥ 80% የሚሆኑ ያለቀናቸዉ የተወለዱ ልጆች ላይ የሚታይ ሲሆን ፤ በቀናቸዉ ከተወለዱት ውስጥ 60% የሚሆኑት ላይ የመከሰት እድል አለዉ።
ለዚህ የሰዉነት ቢጫ መሆን መንስዔዉ በሰዉነታችን ዉስጥ የሚገኝ “ቢሊሩቢን” የተባለ ንጥረነገር በብዛት መከማቸት ነዉ። “ቢሊሩቢን” ጤነኛ ሰዉ ላይ ቀይ የደም ህዋሳት ሲሰባበሩ የሚፈጠር ሲሆን ፤ በጉበት እና ኩላሊት በመታገዝ ከሰዉነታችን በሰገራ እና በሽንት ዉስጥ ይወገዳል።
ጨቅላ ህፃናት እንደተወለዱ ሰዉነታቸው ወደተለመደዉ ስርዓት እስኪላመድ ባለዉ የመጀመሪያዎቹ 2 – 3 ቀናት ዉስጥ የሚከሰት ቢጫ መሆን በማንኛውም ልጅ ላይ ሊከሰት የሚችል ሲሆን ለዚህም መንስዔዉ ፦
- በሰዉነታቸዉ ዉስጥ ያሉ ቀይ የደም ህዋሳት ብዙ መሆን እና ለማርጀትና ለመሰባበር የሚፈጅባቸዉ ጊዜ አጭር መሆን
- “ቢሊሩቢን” ከሰዉነታችን እንዲወገድ የሚያደርጉ ኬሚካሎች አለመመረት ይጠቀሳሉ።
ከዚህ ባሻገር ግን የተለያዩ ህመሞችም በጨቅላ ህፃናት ላይ ቢጫ መሆንን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ከነዚህም ዉስጥ ፦
- በእናትና ልጅ የደም አይነት አለመስማማት የሚከሰት የቀይ የደም ህዋስ መሰባበር
- እንደተወለዱ የሚከሰቱ የተለያዩ ኢንፌክሽኖች
- ያለቀናቸዉ መወለድ
- ከሚጠበቀዉ በታች የሆነ ክብደት
- በዘር የሚተላለፉ በጉበት ዉስጥ ያሉ “ቢሉሪቢንን” ለማስወገድ የሚረዱ ኬሚካሎች እጥረት
- በባህላዊ መንገድ በሚደረጉ እንጥል ማስቆረጥ እና ማስገረዝ ምክንያት የሚከሰት ከመጠን በላይ የደም መፍሰስ
- ከተለመደዉ በታች የሆነ የሰዉነት ሙቀት(መቀዝቀዝ) እንደ አጋላጭ ሁነቶች ይጠቀሳሉ።
ምልክቶች
ዋናዉ የዚህ ህመም መገለጫ ምልክት የጨቅላ ህፃናቱ ሰዉነት ቢጫ መሆን ቢሆንም በተለምዶ አራስ እናቶች ደብዘዝ ያለ ብርሀን ያለበት ቤት ዉስጥ ስለሚቀመጡ ፥ ህፃናቱም አብዛኛዉን ሰዓት በእንቅልፍ ስለሚያሳልፉ የሰዉነታቸዉንም ሆነ የአይናቸዉን ቀለም መቀየር እናቶች በቶሎ ላያስተዉሉ ይችላሉ።
ከዚህ በተጨማሪ የሚከሰቱ ምልክቶች ፦
- ማስመለስ
- ጡት ወይም ወተት በደንብ አለመዉሰድ
- የንቃት መቀነስ
- የሰዉነት ክብደት መቀነስ
- የሽንት ቀለም መጥቆር
- የሰገራ ቀለም መንጣት ይጠቀሳለ።
የህመሙ መጠን ሲጠነክር እና “ቢሉሪቢን” ወደ አዕምሮ በመሄድ መጠራቀም ሲጀምር እንደ ሰዉነትን ማንቀጥቀጥ ፣ መዝለፍለፍ ፣ የንቃት መቀነስ እስከ እራስን መሳት ሊያደርስ ይችላል።
ህመሙን ለመለየት የሚደረጉ ምርመራዎች
በደም ምርመራ ፦
- ሰዉነት ዉስጥ ያለን የ”ቢሊሩቢን” መጠን
- የእናት እና የልጅ የደም አይነት
- የቀይ ደም ህዋሳትን መጠን
- በሰዉነት ዉስጥ ኢንፌክሽን መኖር ማወቅ ይቻላል
ከዚህም በተጨማሪ በአልትራሳዉንድ እና ኤም.አር.አይ በመሰሉ ምርመራዎች በጉበት እና የሀሞት ከረጢት ላይ ያሉ አጋላጭ ችግሮችን መለየት ይቻላል።
ተያያዥ መዘዞች
ከዚህ ህመም ጋር ተያይዞ የሚመጣ እና አሳሳቢ የሆነዉ መዘዝ የ”ቢሊሩቢን” በጭንቅላት ዉስጥ መጠራቀም እና የሚያመጣቸው ጉዳቶች ናቸዉ። ይህም ህመሙ በተከሰተ በሳምንት ዉስጥ መጥባት መቀነስ ፣ ሰዉነት ማንቀጥቀጥ ፣ ንቃት መቀነስ እና የሰዉነት መዛል በመሳሰሉ ምልክቶች ይገለፃል።
በረጅም ጊዜ (አንድ አመት እና ከዛ በላይ) የሚከሰተው መዘዝ ደግሞ መራመድ አለመቻል እና የአዕምሮ እድገት ውስንነት እስከ የመስማት ችሎታን ማጣት ሊያደርስ ይችላል።
ህክምናዉ
በህክምና ወቅት ዋነኛዉ ግብ በልጆቹ ሰዉነት ዉስጥ ያለዉ የ”ቢሊሩቢን” መጠን መቀነስ ሲሆን ይህንንም በዋናነት በሦስት መንገዶች ማሳካት ይቻላል።
- የጨረር ህክምና : ይህ ህፃናትን የተለያየ ቀለም እና ሀይል ባለቸዉየብርሀን ጨረር ላይ በማድረግ በሰዉነታቸዉ ዉስጥ የተከማቸዉን “ቢሊሩቢን” በቀላሉ መወገድ ወደሚችል አይነት መቀየር ነዉ።
- ደም መቀየር : ይህ በህፃኑ ዉስጥ ያለዉን ደም በማስወጣት እና በሌላ ደም በመቀየር ፥ በደም ዉስጥ ያለዉን “ቢሊሩቢን” በዛዉ በማስወጣት መጠኑን ለመቀነስ የሚደረግ ነዉ።
- መድሀኒቶች : ይህም በጉበት ዉስጥ ያሉ “ቢሊሩቢንን” ለማስወገድ የሚረዱ ኬሚካሎችን እንዲመረት የሚረዱ ፣ የቀይ ደም ህዋሳትን እንዳይሰባበሩ የሚረዱ መድሀኒቶችን ያጠቃልላል።
ከዚህ በተጨማሪ ከህመሙ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የደም እና “ኦክስጂን” ማነስ እንደ አስፈላጊነቱ ደም በመስጠት እና ህፃናቱን ኦክስጅን ላይ ማድረግ ሊኖርብን ይችላል።
ሌላዉ ይህን ህመም ያመጣዉን ዋናውን መንስዔ ማከም ዘላቂ መፍትሄ ሲሆን ጎንለጎን ህፃናቱ በቂ የሆነ ፈሳሽ እና የጡት ወተት ማግኘታቸዉ መዘንጋት የለበትም።
መከላከያ መንገዶች
- ጨቅላ ህፃናት እንደተወለዱ በቂ የሆነ ወተት እንዲያገኙ ማድረግ የ”ቢሊሩቢንን” ከሰዉነት መወገድ ማፉጠን ይቻላል።
- ከላይ ከተጠቀሱት አጋላጭ ነገሮች ካሉ ህመሙን በቶሎ መለየት እና ማከም ይቻል ዘንድ ክትትል ማድረግ
- በእናትና ልጅ ደም መሀል አለመስማማት ካለ ተገቢዉን የህክምና ክትትል ማድረግ
ከላይ ከተዘረዘሩት መከላከያ መንገዶች በተጨማሪ እናቶች ከወለዱ እለት ጀምሮ በቂ ብርሃን ባለበት ቦታ ላይ የልጆቻቸውን አይን እና ሰውነት ቆዳ ቀለም በማስተዋል የዚህን ህመም መከሰት ቀድሞ ማስተዋል ይቻላል።
Reference :
- Nelson text book of pediatic 22nd edition
- Standard treatment guideline by Ministry of Health Ethiopia