ከልክ ያለፈ ውፍረት -Obesity
ከልክ ያለፈ ውፍረት – በሰውነታችን ከተገቢው በላይ ሆነው የስብ ክምችት ሲኖር የሚፈጠር ነው። ይህ ከልክ ያለፈ የስብ ክምችት የተለያዩ የጤና እክሎችን ያመጣል።
መቼ ነው ሰውነታችን ከተገቢው በላይ ውፍረት አለው የምንለው ?
በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የስብ መጠን በቀጥታ መለካት አስቸጋሪ ነው፤ ውስብስብ የሆኑ የምርመራ መንገዶችን ይጠይቃል። ስለዚህም የጤና ባለሙያዎች እና የተለያዩ በጤና ላይ የሚሠሩ ተቋማት ሌሎች መንገዶችን ይጠቀማሉ።
BMI (Body Mass Index)
የሰውነት ክብደት (ኪ.ግ)/ቁመት (ሜትር)2
ይህ ቁጥር የሰውነታችን ክብደት ከቁመታችን ጋር በማካፈል የሚገኝ ሲሆን ብዙ የህክምና ተቋማት ውፍረትን ለመለካት ይጠቀሙበታል።
ትክክለኛ የሰውነት ክብደት መጠን የምንለው የሰውነታችን BMI ከ18 እስከ 25 ባለው መጠን ሲሆን፣ ከ18 በታች ከሆነ ከመጠን ያነሰ ክብደትን ያመለክታል።
ይህ ቁጥር በ 25-30 ባለው መሀል ከሆነ Overweight/ የመጀመሪያ ደረጃ ውፍረት እንለዋለን።
ይህ ቁጥር በጣም ከፍ ብሎ 30 በላይ ከሆነ ደግሞ Obese/ እጅግ ከልክ ያለፈ ውፍረት የምንለው ደረጃ ይደርሳል።
BMI ለአብዛኛው ሰው ጥሩ የውፍረት መለኪያ ቢሆንም ሁሉም ክብደት ከስብ የመጣ ስለማይሆን አንዳንዴ ጥሩ መለኪያ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ከፍተኛ ክብደት ያላቸዉ ስፖርተኞች ሰውነታቸው የተሰራው ጤነኛ ከሆነ Muscle/ ጡንቻ ቢሆንም የBMI ቁጥራቸው ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል። ሌላው ደግሞ ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የቁመት መቀነስ ምክንያት በእድሜ የገፉ አዛውንቶችን ከተገቢ በላይ ውፍረት እንዳላቸው አርጎ ሊያሳይ ይችላል።
Waist Circumference (የወገብ ዙሪያ ስፋት)
ሌላውን የውፍረት መለኪያ መንገድ የወገብ ስፋት (waist circumference) የምንለው ነው። ይህም የሆድን ዙሪያ በሜትር በመለካት የሚገኝ ቁጥር ሲሆን በዚህ ልኬት መሰረት ወንዶች የሆድ ዙሪያ ስፋታቸው ከ40 ኢንች በላይ ከሆነ እና ለሴቶች ደግሞ ከ35 ኢንች በላይ ከሆነ ከልክ በላይ ውፍረት አለ ማለት እንችላለን።
በዚህ ዘዴ የሚለካ ውፍረት በተለይ ለጤና የበለጠ ጠንቅ የሆነውን በሆድ ዙሪያ አካባቢ የሚከማቸው ስብ ለመለካት ያገለግላል። በተለምዶ ቦርጭ የምንለው ማላት ነው።
ሁለቱንም መለኪያዎች ማለትም BMI እና የሆድ ዙሪያ ስፋት (Waist Circumference) አብሮ መጠቀም የሰውነት ውፍረትን በትክክል ለማወቅ ይረዳናል።
BMI(Body mass Index) | የውፍረት መጠንደረጃ | ለስኳር ፣ደም ግፊት እና የ ልብ ህመም የመጋለጥ ዕድል ወንዶች -የወገብ ስፋት ከ 40 ኢንች በታች ሴቶች የወገብ ስፋት ከ 35 ኢንች በታች | ለስኳር ፣ደም ግፊት እና የ ልብ ህመም የመጋለጥ ዕድል ወንዶች -የወገብ ስፋት ከ 40 ኢንች በላይ ሴቶች የወገብ ስፋት ከ 35 ኢንች በላይ | |
Underweight -ከተገቢው በታች የሆነ ውፍረት | <18.5 | – | – | |
Normal -ትክክለኛ የሰውነት ክብደት መጠን | 18.5-24.9 | – | – | |
Overweight -የወፍረት መጨመር | 25-29.9 | በመጠኑ ይጨምራል | ይጨምራል | |
ከልክ ያለፈ ውፍረት | 30-34.9 34.9-39.9 |
1 2 |
ይጨምራል በጣም ከፍ ይላል |
በጣም ከፍ ያላል በጣም ከፍ ይላል |
እጅግ ከልክ ያለፈ ውፍረት | >40 | 3 | እጅግ በጣም ከፍ ይላል | እጅግ በጣም ከፍ ይላል |
ከልክ ያለፈ ውፍረት ምን ዓይነት የጤና ችግር ያመጣል
የሰውነታችን ውፍረት በጨመረ ቁጥር ለተለያዩ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላቸን በጣም ይጨምራል።
የሰውነት ውፍረታቸው በBMI ሲለካ ከ40 በላይ የሆኑ ሰዎች ከውፍረት ጋር ተያይዘው በሚመጡ የጤና እክሎች ምክንያት ከዕድሜያቸው ከ7 እስከ 14 አስር ዓመት ድረስ ሊያጡ ይችላሉ። (የ NIH ጥናት)
ከውፍረት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና እክሎችን በጥቂቱ ዘርዝረን ብናይ
የልብና የደም ዝውውር ስርዓት ህመሞች
ከፍተኛ ውፍረት ለልብ ቧንቧዎች መጥበብ (Coronary Artery Disease)፣ የልብ ድካም (Congestive Heart Failure)፣ የኮሌስትሮል መጨመር፣ ለደም ግፊት የመጋለጥ ዕድላችንን ይጨምረዋል።
ከፍተኛ የሰውነት ውፍረት እና የስኳር ህመም
ከፍተኛ የሰውነት ውፍረት ሰውነታችን ለኢንሱሊን እንዳይታዘዝ በማድረግ ለስኳር ህመም የመጋለጥ ዕድላቸው በእጅጉ ይጨምረዋል።
ከምግብ ማብላያ ስርዓታችን ጋ የተያያዙ ችግሮች
ከፍተኛ የሰውነት ውፍረት የሀሞት ጠጠር ህመም፣ በስብ የተሞላ ጉበት ( Fatty Liver ) እና የምግብ ወደላይ የመመለስ ችግር (Gastro Esophageal Reflux Disease-GERD) የመጋለጥ ዕድላቸውን በእጅጉ ይጨምረዋል።
ከፍተኛ የሰውነት ውፍረት እና የካንሰር ህመሞች
ከፍተኛ የሰውነት ውፍረት ለተለያዩ ካንሰሮች የመጋለጥ ዕድላችንን ይጨምረዋል። በተለይ ሴቶች ላይ የሚከሰቱ የማህፀን ካንሰር እና የጡት ካንሰር ካንሰር በውፍረት ምክንያት የመከሰት እድላቸውን ይጨምራል። ይህም የሚሆነው የተከማቸ ስብ ኤስትሮጅን ወደሚባል ሆርሞን ስለሚቀየር ነው።
ከዚህም ባለፈ ከፍተኛ የሰውነት ውፍረት ለስትሮክ፣ ማይግሬን ራስ ምታት ያጋልጣል።
ከክብደት ጋር በተያያዘ ደግሞ
ለመገጣጠሚያ ህመም በተለይም የጉልበት መገጣጠሚያ ህመም Osteo Arthrithis፣ የአተነፋፈስ ችግር Obesity Hypoventilation Syndrome፣ በእንቅልፍ ጊዜ የሚያጋጥም የትንፋሽ መቆራረጥ/ Obstructive Sleep Apnea ያጋልጣል።
ስለዚህ የሰውነት ውፍረት ከተገቢ በላይ ሆነ እነዚህን መሰል ዘርፈ ብዙ ችግሮች ስለሚያመጣ የበለጠ እንዳይጨምር ከተቻለም ወደ ጤነኛ የሆነ የሰውነት ክብደት ልክ ውስጥ ለመግባት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
የልክ በላይ ውፍረት መንስኤዎች ምንድን ናቸው (የWHO ጥናት)
የሰውነት ውፍረት መጨመር በዋነኝነት ከአመጋገብና እንቅስቃሴያችን ጋር የተያያዘ ሲሆን አልፎ አልፎ ከ ሆርሞን መዛባቶች እና ከምንወስዳቸው መድኃኒቶች ጋር ተያይዞ ሊመጣ ይችላል።
በቀን ከምንመገባቸው ምግቦች እና መጠጦች የምናገኘው ኃይል/ ካሎሪ መጠን ሠውነታችን ከሚያስፈልገው በላይ ከሆነ የተረፈው ኃይል/ካሎሪ ሰውነታችን ውስጥ ወደ ስብነት በመቀየር ይከማቻል።
የምግብ አቅርቦት መስፋፋትና ዋጋ መቀነስ በአለም ላይ ሰዎች በቀን ከምግብ የሚያገኙት የኃይል መጠን/ካሎሪ እየጨመረ እንዲሄድ ሲያደርግ በተቃራኒዉ ደግሞ የቴክኖሎጂ መስፋፋት እና የትራንስፖርት አቅርቦት መጨመር ሰዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲገደብ አድርጓል።
ይህም በዓለም ላይ የከፍተኛ ዉፍረት መጠን በጣም እየጨመረ እንዲሄድ ምክንያት ሆኗል። የአለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ከ1975 ወዲህ የከፍተኛ ውፍረት መጠን በ3 እጥፍ ጨምሯል። በ 2016 የወጣ የዓለም ጤና ጥበቃ ጥናት ከ650 ሚሊየን ሰዎች በላይ አለም ላይ እጅግ ከፍተኛ የሰውነት ውፍረት/Obesity እንዳላቸው ያሳያል።
ከፍተኛ የስኳር ወይም ጣፋጭነት ያላቸው ምግቦች አቅርቦት መጨመር፣ የጣፋጭ ፈሳሾች/ለስላሳ መጠጦች፣ ጁሶች በብዛት መገኘት፣ ልጆች በተለያዩ ቪዲዮ ጌሞች እና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ማሳለፍ፣ የፈጣን ምግብ አቅራቢ ድርጅቶች መስፋፋት ከፍተኛ ውፍረት በህፃናት እና ታዳጊዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።
በ2019 የወጣ የአለም ጤና ጥበቃ መረጃ ከ38 ሚሊዮን በላይ ከአምስት አመት በታች ያሉ ህፃናት እና ወደ 340 ሚሊዮን የሚጠጉ እድሚያቸው ከአምስት እስከ 19 አመት ያሉ ህፃናት የከፍተኛ ውፍረት እንደነበረባቸው ያመላክታል።
በህፃንነት የሚከሰት ውፍረት በአዋቂነት ጊዜ ለሚመጣ ውፍረት እና የዕድሜ መቀነስ ያጋልጣል፤ ከዚህም አልፎ እነዚህ ህፃናት አስቀድሞ ለሚከሰት የደም ግፊት መጨመር እና ተያያዥ የልብ ህመሞች ያጋልጣቸዋል።
የምግብ አወሳሰድ መጠን መጨመርና የእንቅስቃሴ ማነስ በዋነኝነት የከፍተኛ ውፍረት መንስኤ ቢሆኑም አልፎ አልፎ የሆርሞን መዛባት እና መድሀኒቶች ለውፍረት መጨመር መንስኤ ሲሆኑ ይታያል።
ለምሳሌ የታይሮይድ ሆርሞን መጠን መቀነስ (Hypothyroidism) ወይም የስቴሮይድ ሆርሞኖች መጠን መጨመር (Cushing Syndrome) እንደምክንያትነት ይጠቀሳሉ። በተለይ በድንገት በተወሰነ ጊዜ የሚመጣ ውፍረት መጨመር ከሌሎች ተጓዳኝ ምልክቶች ጋር ከታየ እነዚህን ምክንያቶች እንጠረጥራለን።
በተለያዩ ምክንያቶች የምንወስዳቸው መድኃኒቶችም መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ለስኳር ህመም የሚወሰዱ አንዳንድ መድሀኒቶች፣ አንዳንድ ለአምሮ ህመም የሚወሰዱ መድሀኒቶች ወይም የስቴሮይድ ይዘት ያላቸው መድሀኒቶች ላልታሰበ ውፍረት ሊያጋልጡን ይችላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ ጫና (stress) ወይም እንቅልፍ ማጣት ራሱ በከፍተኛ ውፍረት እንደሚያጋልጥ ጥናቶች ያሳያሉ።
ከፍተኛ ውፍረትን ለመቀነስ የሚያስችል አንድ ወጥ የሆነ ቀላል መልስ የለም።
ከፍተኛ ውፍረትን ለመቀነስ የረጅም ጊዜ ዕቅድ የሚፈልግ ሲሆን ውጤቱን ለማየት እንደዛው ጊዜ ይወስዳል። የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከል፣ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግን እና የባህሪ ለውጥን ይጠይቃል።
እቅዳችንን በምንችለው እና ልናደርግ በምንችለው መወሰንና ለእቅዳችንም ተገዢ መሆን የበለጠ ውጤታማ ያደርገናል።
አመጋገብን ማስተካከል
ከሁሉም ከፍተኛ ውፍረትን ለመከላከል ከሚረዱ መንገዶች ዋንኛው እና ዉጤታማው የምንመገበውንና በቀን የምንወስደውን ካሎሪ መጠን መቀነስ ነው።
ለዚህም ቅባት ያላቸውን እና ጣፋጭ ምግቦችን መቀነስ፣
የአትክልትና ፍራፍሬ ምግቦችን በአመጋገባችን ማብዛት፣
የምንመገበው የምግብ መጠን ወይም ፖርሽን ማስተካከል ወይም መቀነስ ይረዳናል።
ከልክ ያለፈ ውፍረት የግለሰብ ጥረት ብቻ ሳይሆን የማህበራት፣ የመንግስት እና አለም አቀፍ ተቋማትን ጥረት ይጠይቃል። ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከፍተኛ የገቢ ልዩነት (Income inequality ) ባለባቸው ቦታዎች ውስጥ ከፍተኛ የሰውነት ውፍረት በብዛት ይታያል። ማኀበረሰቡ የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኝባቸውን ፖሊሲዎች መንደፍ፣ ጣፋጭ ምግቦችን እና መጠጦችን በገበያ ውስጥ እንዳይስፋፉ የማድረግ ጥረት እና የምግብ ኢንደስትሪው ጨው የበዛባቸውንና ስኳር የበዛባቸው ምግቦችን ምርት እንዲቀንስ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችን ማበረታታት ይኖርብናል።
የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ
መደበኛ የሆነ የአካል እንቅስቃሴ እንደ አለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ምክር መሰረት ቢያንስ 60 ደቂቃ ለልጆች እና 150 ደቂቃ ለአዋቂዎች በሳምንት ማድረግ ተገቢ ነው። መደበኛ የሆነ የአካል እንቅስቃሴ በአመጋገብ ያስተካከልነውን የክብደት መጠን ለመጠበቅ ይረዳል።
መደበኛ የአካል እንቅስቃሴ ከዛ ባለፈ የተስተካከለ የጡንቻ ጥንካሬ ይሰጠናል። ከልብ ህመም ጋር የሚያያዙ ህመሞችን እንዲቀንሱ ይረዳል።
አንዳንድ ጊዜ በሃኪም የሚታዘዙ ውፍረትን ለመቀነስ የሚያግዙ መድሃኒቶችን ሊኖሩ ይችላሉ። ከፍተኛ የሰውነት ውፍረት ሌሎች ተጓዳኝ የጤና እክሎችን እያመጣ ህይወታችን ወይም ጤናችንን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያውክ ከሆነ ደግሞ በቀዶ ህክምና የማስተካከል ሕክምናዎች ሊሰጡ ይችላሉ።
የጤና ወግ
በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።
………………………………………………………………………………………………………………………..
ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።
በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።
የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።
በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣ በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ