
ቋቁቻ (pityriasis versicolor)
Apr 11, 2023
By Jochebed Kinfemichael Suga, 4th year medical student at Myungsung Medical College
ጆኬቤድ ክንፈሚካኤል ሱጋ (ሚዩንግሱንግ ህክምና ኮሌጅ የ፬ አመት ተማሪ)
Reviewed/Approved by: Dr. Messay Tesfaye(Dermatovenereologist, Pediatric dermatology subspecialist)
ቋቁቻ(pityriasis versicolor) ምንድነው?
በቆዳችን ላይ ከሚፈጠሩ የቆዳ ኢንፌክሽን አይነቶች በተለይም በሞቃታማ ስፍራዎች ውስጥ በብዛት ከሚስተዋሉት አንዱ እና ዋነኛዉ የቆዳ በሽታ ቋቁቻ ነው፡፡
በተለምዶ በቆዳችን ላይ በቋሚነት የሚኖሩ በአይኖቻችን ልናያቸዉ የማንችላቸዉ ጥቃቅን ተዋስያን ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ጥቃቅን ተዋስያን ውስጥ ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶች እና ፈንገሶች ይካተቱበታል፡፡ በቆዳችን ላይ ከሚኖሩ ፈንገሶች ውስጥ በስፋት በቆዳችን ላይ የሚኖረው የፈንገስ አይነት ማላሴዚያ (malassezia) የተባለው የፈንገስ ዝርያ ነው፡፡ ይህ ተህዋስ በቆዳችን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አይኖርም፡፡ ሆኖም ግን ይህ የፈንገስ አይነት ከመጠን በላይ መብዛት ሲጀምር ወይም የሰውነታችን በሽታን የመከላከል አቅም ሲቀንስ በቆዳችን ላይ ችግር መፍጠር ይጀምራል፡፡ በዚህ የፈንገስ አይነት በቆዳችን ላይ ከሚፈጠሩ ችግሮች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛዉ የቆዳ ቀለም መቀየር ነው፡፡ ይህ የቆዳ ቀለም መቀየር በብዛት የሚከሰተው በደረት እና በጀርባ ላይ ሲሆን ታዳጊዎች እና ወጣቶች ላይ በተደጋጋሚ ሲፈጠር እንመለከታለን፡፡
ይህ የቋቁቻ በሽታ ህመም የሌለዉ እና ከሰው ወደ ሰው የማይተላለፍ የቆዳ ችግር ነዉ፡፡
ለቋቁቻ በሽታ መፈጠር ምክንያቶች ምንድን ናቸዉ?
ለቋቁቻ በሽታ መፈጠር ዋነኛ የሚባል ምክንያት ወይም ደግሞ አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ለቋቁቻ ተጠቂ እንደሆኑ ሳይንስ ያስቀመጠው ትንታኔ ባይኖርም ለቋቁቻ መከሰት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ አስተዋፅኦዎች እንዳሉ ተቀምጧል፡፡ ከነዚህም ዉስጥ
ሞቃት እና እርጥበታማ አየር
ለላብ የተጋለጠ ቆዳ
ቅባታማ ቆዳ
ደካማ በሽታን የመከላከል አቅም
የሆርሞኖች መለዋወጥ
በተፈጥሮ ለበሽታው የተጋለጡ ሆኖ መገኘት
የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለበት ሰው (malnourishment)
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች በተለምዶ በሰውነታችን ላይ የሚገኘውን የፈንገስ አይነት በብዛት እንዲራባ እና ቆዳ ላይ ችግር እንዲፈጥር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡
የቋቁቻ በሽታ ምልክቶች ምን ምን ናቸዉ?
አብዛኛውን ጊዜ የቋቁቻ በሽታ ብዙ ምልክቶችን ይዞ የሚመጣ አይደለም። ዋነኛ የሚባልው ምልክት ከአካባቢው ነጣ ብሎ ወይም ይበልጥ ጠቁሮ የሚገኝ የቆዳ ቀለም ለውጦች መኖር ሲሆን የተለያዩ ቅርፆች እና የተለያየ መጠን ሊኖራችዉ ይችላል። እነዚህ የቆዳ ቀለም ለውጦች በብዛት በደረት፣በጀርባ፣ በሆድ እና በአንገት ላይ ይገኛሉ። ከቆዳ ቀለም ለውጥ በተጨማሪ ያልተጋነነ ማሳከክ ሊኖራቸው ይችላል። የፀሀይ ጨረር ያለውን የቆዳ ቀለም ለውጥ ጉልህ ሆኖ እንዲወጣ ያደርገዋል።
ለቋቁቻ በሽታ ምን አይነት ምርመራዎችን እናደርጋለን?
የቋቁቻ በሽታ በአይን በማየት ብቻ የጤና ባለሙያዎች መለየት ይችላሉ። ሆኖም የማረጋገጫ ምርመራ ለማድረግ የቆዳ ቀለም ከቀየረበት ቦታ በመፋቅ ወይም በመቅረፍ ናሙና ከተወሰደ በኋላ አጉልቶ ሊያሳየን በሚችል መሳሪያ (microscope) በቆዳ ህዋሳት የፈንገስ እድገት መኖር እና አለመኖሩን ማየት እንችላለን።
የጨረር ምርመራ (Wood lamp): ይህ የመመርመሪያ አይነት በአይነቱ ለየት ያለ የጨረር አይነትን በመጠቀም የሚሰራ ሲሆን የቆዳ ቀለም ለውጥ ወዳለበት ቦታ አቅርበን በመያዝ የፈንገስ እድገት አለ ወይም የለም የሚለውን በቀላሉ በአይን እንድንለይ ይረዳናል። ይህ የብርሃን ጨረር ቆዳ ላይ ሲያርፍ የፈንገስ እድገት ካለ ቢጫማ ወይም አረንጓዴ ቀለምን ይሰጠናል። ይህ የመመርመሪያ መንገድ በሀገራችን ውስጥ በብዛት ያልተለመደ ስለሆነ በስፋት አገልግሎት ላይ ሲውል አንመለከትም።
ለቋቁቻ የሚደረጉ ህክምናዎች ምንድን ናቸው?
የቋቁቻ በሽታ በራሱ የሚጠፋ ስላልሆነ ህክምና ማግኘት ይገባዋል። ከህክምና በኋላ የተቀየረው የቆዳ ቀለም በምን ያህል ፍጥነት ይመለሳል እና ሙሉ በሙሉ የመጥፋቱ እና ያለመጥፋቱ ጉዳይ ከሰው ሰው የሚለያይ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ እስከ ሁለት ወራቶችን ሊወስድ ይችላል።
የቆዳ ቀለም ለውጥ ለአዕምሮ የሚፈጥረው መረበሽ ካልሆነ በስተቀር ህክምናው ውስብስብ አይደለም። በቆዳ ላይ በሚቀባ የፀረ፡ፈንገስ (antifungal) ክሬሞች የሚታከም ሲሆን ትልቅ የቆዳ ስፋት ያለው እና የቆዳ ቀለም ለውጡ እየሰፋ የሚሄድ ከሆነ በአፍ በሚወሰዱ መድሃኒቶች ይታከማል። መድሃኒትን በአግባቡ አለመውሰድ በሽታው እንዲመላለስ ተፅዕኖ ያደርጋል።
የቋቁቻ በሽታን እንዴት መከላከል ይቻላል?
ከመጠን በላይ የሆነ ሙቀትን መከላከል
ከመጠን በላይ ከሆነ የፀሀይ ብርሀን ራስን መጠበቅ
ከመጠን በላይ የሆነ ላብን መከላከል
ከነዚህም በተጨማሪ ከዚህ በፊት በቋቁቻ ተይዞ የነበረ ሰው በድጋሚ የመያዙ እድል ከፍተኛ ስልሆነ ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ በፀረ፡ፈንገስ መታጠቢያዎች (antifungal shampoo) እንዲታጠብ ይመከራል።
የጤና ወግ
ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።
የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።
https://linktr.ee/Yetena_Weg
