በዶ/ር ኤደን በላይ (በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቆዶ ህክምና ሬዝደንት)
የሃሞት ጠጠር ምንድነው?
የሃሞት ከረጢት በቀኝ በኩል በላይኛው የሆዳችን ክፍል ከጉበት ስር ተለጥፋ የምትገኝ አነስተኛ ኮሮጆ መሰል አካል ስትሆን አገልግሎቷም በጉበት ውስጥ የሚመረተውንና ለቅባታማ ምግቦች ሥርዓተ ልመት አስፈላጊ የሆነውን ሀሞት የተሰኘ ውህድ ማጠራቀም ብሎም በውስጡ ያለውን የውሃ መጠን በመቀነስ የጨዋማ ንጥረ ነገሮችን (Bile salts) ይዘት ከፍ ማድረግ ነው ::የሃሞት ከረጢትን ከሚያጠቁ የተለያዩ የጤና እክሎች መካከል በጣም በስፋት የሚስተዋለው የሃሞት ጠጠር
ነው:: የሃሞት ጠጠር በባህር ዳርቻ እንደሚገኙ ትናንሽ ጠጠሮች ያለ ሲሆን በይዘቱና በአፈጣጠሩ የተለያየ ነው።
እንዴት ይፈጠራል?
ሃሞትበይዘቱከውሃ፣ጨዋማ ንጥረነገሮች (bilesalts)፣ኮሌስትሮል እና ቢሊሩቢን ውህድ ሲሆን የነዚህ ኬሚካሎች መጠን መዛባት ወይም ከሚፈለገው መጠን በላይ በሃሞት ከረጢት ውስጥ መገኘት
አጋላጭ መንስኤዎች
በሃሞት ጠጠር ህመም የመጠቃት እድል ከተለያዩ አጋላጭ ሁኔታዎች ጋር ይዛመዳል።ተጋላጭ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት የሚከተሉት ናቸው።
. እድሜ
. ፆታ፦ሴቶች በሶስት እጥፍ ከወንዶች ይልቅ በህመሙ የመያዝ አዝማሚያ ያሳያሉ (በተለይም በአርባዎቹ የእድሜ ክልል የሆኑና ብዙ ልጆች የወለዱ እናቶች)
. የስኳር ህመም
. ከመጠን ያለፈ ውፍረት
. የአመጋገብ ሥርዓት፦ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን ያላቸው ምግቦች በብዛት መመገብ እና ለረዥም ጊዜ መጾም
. እርግዝና እንዲሁም የሆርሞን ይዘትያላቸው የእርግዝና መከላከያዎች
. ቀይ የደም ህዋሳትን የሚያጠቁ በሽታዎች
የበሽታው ምልክቶች ምንድናቸው?
በአብዛኛው ማለትም ሰማኒያ በመቶ አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች ምንም ዓይነት ምልክት ሳይኖራቸው ለረዥም ጊዜ ሊቆዩ ወይም ፈፅሞ ላይኖራቸው ይችላል። እነዚህም የሃሞት ጠጠር እንዳለባቸው የሚታወቀው በሌላ ህመም ምክንያት አሊያም ለህክምና ክትትል በሚሰራ የሲኖግራፊ ምርመራ ነው።
ምልክት በሚኖራቸው ህሙማን ዘንድ በብዛት የሚስተዋሉት፤በቀኝ ጎን ውጋት፣አልፎ አልፎ ከ ህመሙ ጋር የተያያዘ መጠነኛ ትኩሳት፣ማቅለሽለሽና ማስመለስ፣የዓይን ቢጫ መሆን ናቸው። ሌላው ታካሚዎች ልብ ሊሉት የሚገባው የሃሞት ጠጠር ህመም የምግብ አለመፈጨት ስሜት በተለይም የቅባትነት ይዘት ያላቸው ምግቦች አለመስማማትን በማስከተል ከጨጓራ ህመም ጋር ተመሳሳይነት ስለሚኖረው በብዛት እንደ ጨጓራ ተደርጎ መድሃኒት በሃኪሞች ሊታዘዝ ይችላል።ስለሆነም ታካሚው
በምልክቶቹ ላይ መሻሻል ካላሳየ ተመልሶ ሃኪምን ማማከር ያስፈልጋል።
ህመሙ እንዳለብን እንዴት ይረጋገጣል?
የህመሙ ምልክቶች ያለው ሰው በዋናነት በሚደረግለት የሲኖግራፊ(abdominal ultrasound) ምርመራ በሃሞት ከረጢት ውስጥ ጠጠሮቹን ለማየት ብሎም ተያያዥ ችግሮችን (complications) መለየት የሚቻል ሲሆን እንዳስፈላጊነቱ ተጨማሪ የምስል እና የላብራቶሪ ምርመራዎች በ ሃኪምዎ ሊታዘዙ ይችላሉ::
የ ሃሞት ጠጠር የሚያስከትላቸው ጉዳቶች
በተደጋጋሚ የሆድ ህመም ሳቢያ በእለት-ተለት እንቅስቃሴ ላይ ከሚፈጥረው እክል ባሻገር በርካታ የጤና መታወክ ሊያስከትል ይችላል። ከነዚህም የተወሰኑቱ፦
. የሃሞት ከረጢት ብግነት እና ኢንፌክሽን (inflammation and infection)
. የሃሞት ከረጢት መሽንቆር
. የሃሞት መተላለፊያ ዋና ቱቦ በመዝጋት በጉበት ላይ ጉዳት ማድረስ
. የሃሞት ከረጢት ካንሰር
. የቆሽት ብግነት ሊሆኑ ይችላሉ።
እንዴት ይታከማል?
በዋናነት ሃሞት ጠጠር ህክምና ጠጠሩን ከነሃሞት ከረጢቱ በቀዶ ህክምና ማስወገድ ሲሆን ይኸውም ሆድን በመክፈት አሊያም በሆድ ግድግዳ ላይ ትንንሽ ቀዳዳዎች በማበጀት በካሜራ እይታ እየታገዘ ሊሰራ ይችላል። ሌላኛው የህክምና አማራጭ በተለያየ ምክንያት የቀዶ ህክምና ማድረግ ለማይችሉ ህሙማን መድሃኒቶች
ወይም ጨረር በመጠቀም ጠጠሮቹን መሰባበር የሚቻል ቢሆንም ዘላቂው ጤታማነቱ አመርቂ ላይሆን ይችላል።
መከላከል ይቻላል?
. ልከኛ የሰውነት ክብደት እንዲኖረን በማድረግ በሃሞት ጠጠር የመያዝ እድላችንን መቀነስ ይቻላል:: ነገር ግን በአጭር ጊዜ ብዙ ክብደት መቀነስ የበለጠ ተጋላጭ ሊያደርግ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል::
. የአመጋገብ ስርዓትን በማስተካከል:
. የኤስትሮጅን (estrogen) ሆርሞን ያላቸው የእርግዝና መከላከያዎች:ለሃሞት ጠጠር ተጋላጭ የሚያደርጉ ተያያዥ ሁኔታዎች ካሉ የኤስትሮጅን ይዘት ያላቸው የእርግዝና መከላከያዎችን አለመጠቀም ይመከራል::


