YetenaWegLogo

የኩላሊት እጥበት ሕክምና እና አመጋገብ

Mar 04, 2023

By: Fisseha Mulugeta(C2 student at Myungsung Medical College)

ፍስሃ ሙሉጌታ(ሚዩንግሱንግ ህክምና ኮሌጅ የ፬ አመት ተማሪ)

Reviewed/Approved by: Dr. Fitsum Tilahun (Editor at Yetena Weg/ Nephrologist)

 

ኩላሊት እና የኩላሊት ድክመት ምንድነው?

ኩላሊቶቻችን በሰዉነታችን ውስጥ የሚመረቱ ጎጂ እና መርዛማ ምርቶችን ያስወግዳሉ። በተጨማሪም ውሃ ፣ ፈሳሾች ፣ ማዕድናት ፣ ኬሚካሎች እና ኤሌክትሮላይቶችን(እንደ ሶዲየም ፖታስየም ወዘተ)መጠን ሚዛን በመጠበቅ ያገለግላሉ።

ኩላሊቶቻችን እንደበፊቱ መስራት ሲያቅታቸው ወይም ሙሉ በሙሉ መስራት ሲያቆሙ የኩላሊት ድክመት ይባላል።

  • የኩላሊት እጥበት (ዳያሊስስ)

የኩላሊት እጥበት (ዳያሊስስ) ማለት በኩላሊት መድከም ምክንያት ሰውነት ውስጥ የሚጠራቀመው መወገድ ያለበት ቆሻሻ ምርት እና ከመጠን በላይ የሆነን ውሃ ከሰውነት በሰው ሰራሽ መንገድ የማስወግድ ሂደት ነው።

  • የኩላሊት እጥበት አይነቶች
  1. በደም ስር የሚሰጥ (ሂሞ ዳያሊስስ)
  • ከደም ስር ወደ ዳያሊስስ ማሽን በተጣጣፊ ቱቦ ይገናኛል፡፡
  • ማሽኑ ደሙን ባሉት ማጣርያ አካላቶች እና ዲያልያዘር የሚባል ልዩ ብጥብጥ በመጠቀም ደምን ያጣራል።
  • ከተጣራ በኋላ በሌላ ተጣጣፊ ቱቦ ወደ ደም ስር ይመለሳል፡፡
  • ሄሞዳያሊስስ ከመጀመሩ 4-8 ሳምንታት በፊት በክንድ ላይ ደም ወሳጅ (Artery) እና ደም መላሽ (Vein) ቧንቧዎችን በቀላል ቀዶ ጥገና መገናኘት አለባቸው፡፡
  • ሄሞዲያልሲስ በአብዛኛው ጊዜ በሳምንት ሶስቴ ይካሄዳል፡፡
  • እያንዳንዱ እጥበት አራት ሰዓታትን አካባቢ ይፈጃል።

2.የሆድ ውስጥ የሚደረግ ኩላሊት እጥበት (ፔሪቶኒያል ዲያላሲስ)

  • በመኖሪያ ቤት ውስጥ የሚደረግ የኩላሊት እጥበት አይነት ነው። ታካሚው ስራውን እየሰራ ቤት ሆኖ ይሄን አይነት ዳያልሲስ ማድረግ ይችላል። ይህ ሕክምና አገልግሎት በሀገራችን ውስጥ በአሁኑ ሰዓት የለም።
  • ፔሪቶንየም የውስጠኛውን የሆድ ክፍል የሚሸፍን ሽፋን ነው።
  • ፔሪቶንየም ፈሳሽ በከፊል የሚያሳልፍ ወንፊት መሳይ ሲሆን በደም ውስጥ የሚገኙ አላስፈላጊ የሰውነት ቆሻሻዎችንና መርዞችን ማሳለፍ ይችላል።
  • በሆድ ውስጥ አነስተኛ ቀዳዳ መከፈት አለበት፡፡
  • ካቴተር የሚባል ቀጭን ቱቦ ወደ ተከፈተው ቀዳዳ ውስጥ ይገባል። ይህ የዲያሊሲስ ፈሳሽ (ዲያልያዘር) በሆድዎ ውስጥ እንዲገባ ያስችለዋል።
  • ፈሳሹ ከገባ በኋላ ፤ ቆሻሻ ምርቶች በፔሪቶንየም አልፈው በሌላ ካቴተር ይወጣሉ፡፡

ይህ የመለዋወጥ ሂደት አብዛኛውን ጊዜ ለማጠናቀቅ ከ30 እስከ 40 ደቂቃዎችን ይወስዳል።

  • የኩላሊት እጥበት የሚያደርግ ሰው ማድረግ የሚገባው ጥንቃቄ
    • የደም ወሳጅ (Artery) እና ደም መላሽ (Vein) ቧንባ መገናኛ
      • በሳሙና እና በሞቀ ውሃ በየቀኑ ይጠቡ፡፡
      • ከዲያሊሲስ ሕክምና በፊት አካባቢውን አይቧጭሩ ወይም አይንኩ፡፡
      • ማንም ሰው ይህንን ክንድ ደም ለመውሰድ ወይም ደም ግፊት ለመለካት እንዲጠቀምበት አለመፍቀድ፡፡
      • በመደበኛነት ሲሰራ በአካባቢው ላይ ንዝረት ሊሰማዎት ይችላል፤ ንዝረት ካልተሰማዎት ለሐኪምዎ ወይም ለነርስዎ ያሳውቁ።
    • ሐኪም ወይም ነርስ ካቴተርዎን በፋሻ ይሸፍናሉ– ይህ ኢንፌክሽንን ለመከላከል አስፈላጊ ነው፤ ይህንን ለማስወገድ ወይም ለመቀየር ቤት ውስጥ አይሞክሩ፡፡
    • በየቀኑ ኪሎ ይመዘኑ – ኩላሊትዎ በማይሰራበት ጊዜ ፈሳሽ በሰውነትዎ ውስጥ ይሰበሰባል። ኪሎዎ ከወትሮው የበለጠ ከጨመረ ለሐኪምዎ ወይም ለነርስዎ ያሳውቁ፡፡
  • ልዩ አመጋገብን ይከተሉ – የሚጠጡትን ፈሳሽ መጠን መወሰን ያስፈልግዎታል። እንዲሁም ብዙ ሶዲየም ፣ ፖታሲየም እና ፎስፎረስ የያዙ ምግቦችን መብላት የለቦትም፡፡

ለምን በዳያሊስስ ላይ ያሉ ሰዎች አመጋገባቸውን መከታተል አለባቸው?

  • ዲያሊሲስ የኩላሊትን ሥራ የሚተካ ሕክምና ነው።
  • ዳያሊሲስ ግን እንደ ጤናማ ኩላሊት ያህል አያጣራም።
  • በተጨማሪም መደበኛ ኩላሊቶች ቀኑን ሙሉ በየቀኑ ይሠራሉ ነገር ግን የኩላሊት ድክመት ያለባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ የኩላሊት እጥበት በሳምንት 3 ጊዜ ብቻ በማዕከል ያደርጋሉ።
  • በመብላትና በመጠጣት ብዙ ውሃ፣ ጨው ወይም ሌሎች ንጥረ ነገሮችን ስለሚያገኙ እነዚህ ነገሮች በሰውነት ውስጥ ሊከማቹ ይችላሉ።
  • ብዙ ፈሳሽ የደም ግፊትን ከፍ ሊያደርግ እና ልብ ከአቅም በላይ እንዲሠራ ያደርገዋል። የሰውነት ክብደት መጨመር ፣ እብጠት እና የመተንፈስ ችግርም ሊያስከትል ይችላል፡፡

በአመጋገብ ላይ ምን ለውጦች ማድረግ አለብኝ?

ፈሳሾች

  • አብዛኛዎቹ በዲያሊሲስ ላይ ያሉ ሰዎች ምን ያህል ፈሳሽ እንደሚበሉ እና እንደሚጠጡ መወሰን አለባቸው። ሲቀልጡ ፈሳሽ የሚሆኑትም (አይስ ክሬም) እንደ ፈሳሽ ይቆጠራሉ፡፡
  • አንዳንድ ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች በውስጣቸው ብዙ ፈሳሽ አላቸው። ከእነዚህም መካከል ሐብሐብ፣ ኮክ ፣ ዱባ እና ሰላጣ ይጠቀሳሉ።
  • እብጠትና የሽንት ፈሳሽ መቀነስ ያጋጠማቸው ታካሚዎች የሚወስዱትን የፈሳሽ መጠን እንዲገድቡ ይደረጋል። እብጠትን ለመቀነስ በ24 ሰዓታት ውስጥ የሚወሰደው የፈሳሽ መጠን በየቀኑ ከሚመረተው የሽንት መጠን ያነሰ መሆን አለበት።
  • እብጠት የሌላቸው ህመምተኞች ከመጠን በላይ ፈሳሽ እንዳይኖር እንዲሁም የፈሳሽ እጥረት እንዳይከሰት የሚወስዱት የፈሳሽ መጠን በቀን የቀደመውን ቀን የሽንት መጠን ላይ 500 ሚሊ ሊትር በመደመር ይሆናል።

ከተጠማሁስ?

  • ከተጠማቹ ነገር ግን ፈሳሽን መገደብ ካለባቹ እነዚህን ምክሮች ሞክሩ፡–
    • ከመጠጣት ይልቅ በረዶ ይምጠጡ። ምክንያቱም በረዶ ለረጅም ጊዜ ይቆያል(ነገር ግን በረዶም ፈሳሽ መሆኑን ያስተውሉ)።
    • ማስቲካ ያኝኩ ወይም ጠንካራ ከረሜላ ይምጠጡ፡፡
    • የቀዘቀዙ ወይኖች ይብሉ፡፡
    • አፍዎን በውሃ ይግሞጥሞጡ ነገር ግን አይዋጡ፡፡

ሃይል ሰጪ ምግቦች /ካርቦሃይድሬት

  • ካርቦሃይድሬት ለሰውነት ዋናው የሃይል ምንጭ ነው። ከስንዴ ፣ ጥራጥሬ ፣ ሩዝ ፣ ድንች ፣ ፍራፍሬዎች ፣ ስኳር ፣ ማር ፣ ኩኪሶች ፣ ኬኮች ፣ ጣፋጮች እና ከመጠጦች ውስጥ ይገኛሉ።
  • የስኳር ህመምተኞች እና ከመጠን በላይ ውፍረት ያላቸው ታካሚዎች ሃይል ሰጪ ምግቦችን መጠን መገደብ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ሶዲየም

  • ይህ በጠረጴዛ ጨው ውስጥ ዋናው ንጥረ ነገር ነው፡፡
  • አብዛኛዎቹ በዳያሊስስ ላይ ያሉ ሰዎች የሚበሉትን የሶዲየም መጠን መገደብ አለባቸው።
  • ምክንያቱም ብዙ ሶዲየም መብላት የደም ግፊትን ስለሚጨምር ነው።
  • እንዲሁም ከሚገባው በላይ ውሃ ሊያስጠማዎት እና ሊያስጠጣዎት ይችላል፡፡
  • የጠረጴዛ ጨው(የምግብ ጨው) ፣ የመጋገሪያ ዱቄት፣የታሸጉ ምግቦች፣ቅመማ ቅመሞች ፣ የሶያ ሶስ ፣ አኩሪ አተር እና ክኖር ፣ አትክልቶች(እንደ ጎመን ፣ አበባ ጎመን ፣ ስፒናች ፣ ራዲሽ ፣ ቢትሮት ፣ እና የበቆሎ ቅጠል) የመሳሰሉት በሶዲየም የበለጸጉ ምግቦች ናቸው፡፡

ፖታስየም

  • ይህ የልብ ምትዎን የሚቆጣጠር ንጥረ ነገር ነው።
  • ዳያሊስስ ላይ ያሉ ሰዎች የፖታስየም መጠን መወሰን አለባቸው፡፡
  • በጣም ብዙ ፖታስየም በሰውነት ውስጥ ከተከማቸ የልብ ምት መዛባት ሊያመጣ ይችላል፡፡
  • የበሰለ ሙዝ፣ኮኮናት ፣ ካስታርድ አፕል ፣ ጉስቤሪ ፣ ጉአቫ፣ ብሮኮሊ፣ጣፋጭ ድንች፣ ቀይ እና ጥቁር ባቄላ የመሳሰሉት በፖታስየም የበለጸጉ ምግቦች ናቸው፡፡

ፎስፈረስ

  • ይህ በብዙ ምግቦች ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ነገር ነው፡፡
  • እንደ ወተት፣ ሌሎች የወተት ተዋህጾዎች፣ ለውዝ፣ ባቄላ፣ ጉበት እና ቸኮሌትን የመሳሰሉት ምግቦች ከፍተኛ መጠን ያለው ፎስፈረስ አላቸው፡፡
  • በዲያሊሲስ ላይ ያሉ ሰዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ፎስፈረስ ያላቸውን ምግቦች መተው አለባቸው፡፡

የገንቢ /ፕሮቲን

  • ፕሮቲን ጡንቻዎ ጠንካራ ሆኖ እንዲቆይ ይረዳል፡፡
  • ብዙ ፕሮቲን ካላቸው ምግቦች መካከል ስጋ፣ ዶሮ፣ አሳ እና እንቁላል ይገኙበታል።

የኩላሊት ህመምተኞች ከፍተኛ የገንቢ/ ፕሮቲን አመጋገቦች ከመውሰድ መቆጠብ አለባቸው።

 

የጤና ወግ

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg

Recent Posts