YetenaWegLogo

የደም መርጋት በሽታ

Sep 15, 2021

የደም መርጋት በሽታ
በዶ/ር ኤዶም ገ/መድህን (በጥቁር አንበሳ ሆ/ል የውስጥ ደዌ ስፔሻላይቬሽን ሲኒየር ሬዝደንት)

በሰውነታችን ውስጥ የሚዘዋወረው ደም በተለያዩ አጋላጭ ምክንያቶች የተነሳ በደም ወሳጅ ወይም የደም መላሽ የደም ስሮቻችን ውስጥ ሊረጋ ይችላል፡፡ ይህ የደም መርጋት ሁኔታ በደም መላሽ የደም ስሮች ውስጥ በሚከሰትበት ወቅት ለቆዳችን ቅርብ የሆኑትን የደም ስሮች ወይም ጥልቅ ሆነው የሚገኙትን የደም ስሮች ሊያጠቃ ይችላል፡፡ በአብዛኛው ጊዜ ይህ የደም መርጋት በሽታ ከእግሮቻችን ወደ ልብና ሳንባ የሚመለሰውን ደም የሚወስዱ ጥልቅ የደም መላሽ የደም ስሮችን የሚያጠቃ ሲሆን በህክምናው ቋንቋ Deep Venous Thrombosis (DVT) ተብሎ ይጠራል፡፡ ደም በእግሮቻችን ጥልቅ የደም መላሽ የደም ስሮች ውስጥ በሚረጋበት ወቅት ተገቢውን የደም ዝውውር ከመግታቱም ባሻገር የረጋው ደም ተቆርጦ ወደሌሎች የሰውነት ክፍሎች በመሄድ ጉዳትን ሊያስከትል ይችላል፡፡
ለደም መርጋት በሽታ ተጋላጭነትን ከሚጨምሩ ሁኔታዎች መካከል፡-

 ለረዥም ጊዜ አለመንቀሳቀስ ለምሳሌ በህመም ወይም በስብራት ምክንያት በአልጋ ላይ ከ3 ቀን በላይ መቆየት፣
በቅርብ ጊዜ የተደረገ ከፍተኛ ቀዶ ጥገና እና ረዥም የአውሮፕላን ጉዞ
 የተለያዩ የካንሰር አይነቶችና ተጒዳኝ በሽታዎች
 እርግዝና
 የተለያዩ መድሀኒቶች ለምሳሌ አንዳንድ የወሊድ መከላከያ እንክብሎች፣ ለሆርሞን መተኪያ የሚሰጡ መድሃኒቶች
ወዘተ.
 ሲጋራ ማጨስ
 ከፍተኛ የሰውነት ክብደት መጨመር እና የእድሜ መግፋት (ከ65 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች)
 ከዚህ በፊት የደም መርጋት ህመም ተከስቶ ከነበረ ወይም በዘር የሚመጡ የደም መርጋት ህመም አይነቶች መኖር
በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡

የደም መርጋት በሽታ ምልክቶች

በእግሮቻችን ጥልቅ የደም ስሮች ውስጥ የደም መርጋት በሚከሰትበት ወቅት የደም ዝውውርን ስለሚገታ ከዚህ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ምልክቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ለምሳሌ በደም መርጋት በተጠቃው እግር ላይ ጎልቶ የሚታይ እብጠት፣ የቆዳ መሞቅና በንክኪ ወቅት የሚሰማ ህመም ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የረጋው ደም ተቆርጦ ወደ ሳንባ ደም ስሮች በሚሄድበት ወቅት የትንፋሽ ማጠር፣ በደረት ላይ የሚሰማ ከትንፋሽ ጋር የተያያዘ ውጋት ፣ ደም የተቀላቀለበት አክታና የልብ ምት ፍጥነት መጨመር ሊከሰት ይችላል፡፡

የደም መርጋት በሽታ ህክምና

ከላይ የተጠቀሱትን የደም መርጋት በሽታ ምልክቶች በምናይበት ወቅት በቶሎ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የህክምና ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የደም መርጋት በሽታ መኖሩን ለማረጋገጥ የተለያዩ የደምና የእግር አልተራሳውንድ እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ የሚታዘዙ የሲቲ ስካን ምርመራዎች ከተደረጉ በኃላ በተለምዶ የደም ማቅጠኛ ተብለው የሚጠሩ መድሀኒቶች በሀኪም ሊታዘዝልን ይችላል፡፡ እነዚህ መድሀኒቶች በመርፌ እና በሚዋጥ ኪኒን መልክ የተዘጋጁ ሲሆን ስራቸውን የሚሰሩት ሰውነታችን በተፈጥሯዊው ሂደት የረጋውን ደም አሟሙቶ እስኪያስወግደው ድረስ አዲስ ደም እንዳይረጋ በመከላከል ነው፡፡ ለደም መርጋት ህክምና የሚታዘዙ መድሀኒቶች አብዛኛውን ጊዜ ከ3-6 ወር ለሚሆን ጊዜ የሚሰጡ ሲሆን ቀጣይነት ያላቸው ለደም መርጋት የሚያጋልጡና ሊቀረፉ የማይችሉ ሁኔታዎች በምርመራ በሚገኙበት ወቅት በሀኪም ትዕዛዝ ለእድሜ ልክ ድረስ መውሰድ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ መድሀኒቶች በሀኪም ትዕዛዝ መሰረት በአግባቡ መውሰድና ተገቢውን ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ሲሆን መድሀኒቶቹን በሚወሰዱበት ወቅት ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በቀላሉ የሚከሰት የደም መፍሰስ ካስተዋሉ በቶሎ ለጤና ባለሙያ ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡

የደም መርጋት በሽታን ለመከላከል ማድረግ የሚገባን ጥንቃቄዎች፡-

  • ሲጋራ ማጨስ መቆም
  • ክብደትን መቀነስና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ
  • እንዲሁም የደም መርጋት ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ለሆኑ ታካሚዎች ለምሳሌ የካንሰር ህመምተኞች ወይም በህመም ምክንያት ሆስፒታል ለተኙ ታካሚዎች የደም መርጋትን ለመከላከል ለደም መርጋት ህክምና የሚታዘዙ መድሀኒቶች በአነስተኛ መጠን በሀኪም ሊታዘዙ ይችላሉ፡፡

Recent Posts