YetenaWegLogo

የደም ካንሰር (ሉኪሚያ)

Nov 07, 2022

የደም ካንሰር (ሉኪሚያ)

ሉኪሚያ ከደም ሴሎች (ህዋሳት) የሚነሳ የካንሰር አይነት ነው፡፡ በሰውነታችን ውስጥ የተለያዩ አይነት ስራዎችን የሚያከናውኑ የደም ሴል አይነቶች የሚገኙ ሲሆን በአጥንት መቅኔ ውስጥ ተመርተው ወደተለያዩ የአካል ክፍሎች በመሰራጨት እስኪሞቱ ድረስ ስራቸውን ያከናውናሉ፡፡ የደም ካንሰር (ሉኪሚያ) በሚከሰትበት ጊዜ በመቅኔ ውስጥ በዋነኝነት የሚመረቱት በካንሰር የተጠቁት የደም ሴል አይነቶች ስለሚሆኑ ለሰውነታችን የሚያስፈልጉትን ጤነኛ እና ጠቃሚ የደም ሴል አይነቶች በበቂ መጠን እንዳይመረቱ በማድረግ የተለያዩ ምልክቶችን ሊያመጣ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ የካንሰር ሴሎች ከመቅኔ ወጥተው በደም አማካኝነት ራቅ ወዳሉ የሰውነት ክፍሎች ሊሰራጩ አልያም ሊከማቹ ይችላሉ፡፡

የደም ካንሰር (ሉኪሚያ) አይነቶች

ብዙ የደም ካንሰር አይነቶች ሲኖሩ ከነዚህም አንዳንዶቹ በዝግታ የሚባዙ (የሚያድጉ) ሲሆኑ Chronic Leukemia ተብለው ይጠራሉ፡፡ አንዳንድ የደም ካንሰር አይነቶች ደግሞ በፍጥነት የሚያድጉ ይሆኑና Acute Leukemia ተብለው ይጠራሉ፡፡ በተወሰኑ ሁኔታዎች ደግሞ በዝግታ የሚያድጉ የነበሩ የደም ካንሰር አይነቶች የእድገት ፍጥነታቸውን ጨምረው በፍጥነት ወደሚያድጉ የሉኪሚያ አይነት ሊቀየሩ ይችላሉ፡፡ የደም ካንሰር (ሉኪሚያ) በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት ቢችልም አንዳንድ የደም ካንሰር አይነቶች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በእድሜ ወይም በጾታ ለይተው በዋነኝነት ሊያጠቁ ይችላሉ፡፡

የደም ካንሰር (ሉኪሚያ) አምጪ ምክኒያቶች

የደም ካንሰርን የሚያመጡ ምክንያቶች በእርግጠኝነት ባይታወቁም ተጋላጭነት ከሚጨምሩ ሁኔታዎች መካከል ለተለያዩ ኬሚካሎችና ጨረር መጋለጥ፣ ከዚህ በፊት የኬሞቴራፒ መድሃኒት አልያም የጨረር ህክምና መውሰድ፣ አንዳንድ ከዘረመል ችግር ጋር የተያያዙ ከመወለድ ጀምረው አብረው የሚኖሩ በሽታዎች እንዲሁም የተወሰኑ በቫይረስ ኢንፌክሽን የሚመጡ በሽታዎች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡

የደም ካንሰር (ሉኪሚያ) ምልክቶችና ምርመራ

የደም ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ ምልክት ሳያሳይ ሊቆይ ይችላል፡፡ ምልክቶች መታየት በሚጀምሩበት ወቅት ከወትሮ የተለየ የድካም ስሜት፣ ማዞር፣ በቀላሉ ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች መድማት፣ በተደጋጋሚ በተለያዩ ኢንፌክሽኖች መጠቃት ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተወሰኑ ህሙማን ላይ በተለያዩ የሰውነት ክፍል የሚገኙ ንፍፊቶች ማበጥ፣ የጉበትና የጣፊያ እብጠት እንዲሁም በአጥንት ላይ የሚሰማ ህመም ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ምልክቶች ከሌሎች ህመሞች ጋርም ተያይዘው ሊታዩ ስለሚችሉ በቶሎ ወደጤና ተቋም ሄዶ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የደም ካንሰር (ሉኪሚያ) በሰውነት ውስጥ መኖሩን ለማወቅ፣ የካንሰሩን አይነትና ያለበትን ደረጃ ለመለየት እንዲሁም ከህክምናው ጋር ተያይዘው በተለያዩ የሰውነት አካሎች ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለመከታተል እንዲረዱ የተለያዩ የደም፣ የመቅኔ፣ የአልትራሳውንድ፣ የራጅና ሲቲስካን ምርመራዎች በሀኪም ይታዘዛሉ፡፡

የደም ካንሰር (ሉኪሚያ) ህክምና

የደም ካንሰር በሰውነት ውስጥ መኖሩ ከታወቀና የካንሰሩ አይነትና ያለበት ደረጃ በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ በሀኪምዎ የተለያዩ የህክምና አማራጮች ይቀርብሎታል፡፡ አንዳንድ በዝግታ የሚያድጉ የደም ካንሰር አይነቶች ለህይወት አስጊ የሆኑ ምልክቶችን ማሳየት እስኪጀምሩ ድረስ የህክምና ምርመራና ክትትል በማድረግ ብቻ ያለምንም መድሃኒት ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ለተቀሩት የደም ካንሰር አይነቶች በተለይም ለአጣዳፊ የሉኪሚያ አይነቶች (Acute Leukemia) ግን እንደአይነታቸውና ያሉበት ደረጃ የኬሞቴራፒ ህክምና፣ የመቅኔ ንቅለ ተከላ (Stem cell transplant) እና የኢሙኖቴራፒ ህክምና ሊሰጥ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከደም ካንሰሩ ወይም ከህክምናው ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ ተጓዳኝ ህመሞችን ለማከም የሚሰጡ የህክምና እርዳታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ከነዚህም ውስጥ የኢንፌክሽን መከላከያ እና ማከሚያ መድሀኒቶች እንዲሁም የደምና የደም ተዋፅኦ ድጋፍ በዋነኝነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የደም ካንሰር ለህክምና የሚያሳየው ምላሽ እንደ ታካሚው እድሜ፣ አጠቃላይ የጤና ሁኔታ፣ የካንሰሩ አይነትና ደረጃ፣ ከህክምናው ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተጓዳኝ ህመሞች ፅኑነትና እንደከናወነው የህክምና አይነት ሊለያይ ይችላል። በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች ሲታዩ በቶሎ በሀኪም መመርመር እና የህመሙን አይነት መለየት የህክምናውን ውጤት የተሻለ ያደርገዋል።

 

በዶ/ር ኤዶም ገ/መድህን (የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሀኪም)

Recent Posts