የጤና ወግ የእለቱ መልእክት ማርች 18 2020 የኮሮና ቫይረስ (COVID 19) በሽታ መስፋፋትን ለመቀነስ የሀገራችንን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የማህበራዊ መራራቅን (social distancing) እንፍጠር ። ክፍል ሁለት
Mar 19, 2020
እንደ ኢትዮጵያ አይነት ጥብቅ የሆነ ማህበራዊ ትስስር ባለበት ሃገር እነዚህን ማስቀረት ቀላል ባይሆንም የማይቻል አይደለም።
Tweet
ብዙዎቻችን እንደምናውቀው አዲሱ የኮሮናቫይረስ የሚተላለፈው ቫይረሱ ካለበት ሰው ወደ ሌላ ሰው ከአፍና ከአፍንጫ በሚወጡ በጣም ትንንሽ ጠብታዎች ነው፤ ይህም ቫይረሱ ያለበት ሰው ሲያስል ወይም ሲያስነጥስ በቅርቡ ወዳለው ሰው በቀላሉ ይተላለፋል። በተጨማሪም ቫይረሱ እጅ ላይ በተለያየ መንገድ ሊቆይ ሰለሚችል በአግባቡና በሚገባ በሳሙና እጅን መታጠብ ይመከራል። እጅ በመጨባበጥ በመተቃቀፍና በመሳሳም ቫይረሱ በቀላሉ ይተላለፋል። ለዚህ ነው የጤና ባለሞያዎች እርስ በርስ መቀራረብን የማይመክሩት። ይህን አለመቀራረብ ባለሞያዎቹ ማህበራዊ መራራቅ (Social Distancing )ይሉታል። ማህበራዊ መራራቅ መፍጠር ማለት በተቻለው ነገር ሁሉ ከሰዎች ጋር ቅርርብን ማስቀረት ማለት ነው።
ከሃገራችን ባህልና ማህበራዊ ሁኔታ አንጻር እስኪ የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንይ፡
- የታመመን ሰው በምንንከባከብበት ጊዜ እንደሌላጊዜው ሳይሆን ጓንቶችን አድርገንና አፋችንን በማስክ መሸፈን አለብን። እንዲሁም በተቻለ መጠን ሆስፒታል ከመሄድ መቆጠብ አለብን። የታመመ ቤተሰብ ካለብን ልጆችና የእድሜ ባለጸጎችን ለጥየቃ ይዘን መሄድ የለብንም፤ እኛ ደሞ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን።
- የቫይረሱ ምልክት እርሶ ላይ ከታየ በጤና ጥበቃ መመሪያ መሰረት መጀመሪያ 8335 ወይም 952 ይደውሉ እንጂ በቀጥታ ወደ ጤና ጣብያው አይሂዱ፤ ይህን ማድረግ ሃኪሞችን ነርሶችን እና ሌሎች የጤና ባለሞያዎችን እንዲሁም በመንገድ ላይ የሚያጋጥሞትን ሁሉ ለቫይረሱ አጋለጡ ማለት ነው። ስለዚህ በስልክ መጀመሪያ ያሳዉና የሚነገሮትን መመሪያ ይከተሉ። በተቻለ መጠን በሽታው መጠነኛ ከሆነ ስልክ በመደወል ብቻ መረጃ ይጠይቁ። ይህም ባለሙያዎች የፀና በሽታላለባቸው ቅድሚያ እንዲሰጡ ያግዛል ። በኛ ሆስፒታሎች አና የተና ማአከላት ብዙ ጊዜ የጓንትና የማስክ እጥረት ስላለብ አርስዎ ካለዎት ይዘው ይሂዱ።
- ቫይረሱ በቀላሉ ከአንዱ ወደ ሌላው ስለሚተላለፍ መስኪድና ቤተክርስቲያን በአሁን ሰአት መሄድ አይመክርም። ይሄ ለብዙዎች የሚከብድ ቢሆንም በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ደግመን ደጋግመን እናሳስባለን። ፈጣሪም ይህን በማረጋችን አያዝንብንም፤ ፈጣሪ የሚያዝነው ለሌሎች የቫይረሱ ሰበብ ከሆንን እንጂ እራሳችንን ጠብቀን ከየቤታችን ስለጸለይን አይደለም። በተለያየ የአለማችን ቦታዎች የሃይማኖት አባቶች ወደ ሃይማኖት ቦታዎች ሰዎች እንዳይመጡ ክልክለዋል። እኛም ይህን ፈለግ መከተል አለብን።
- ከዚህ በተጨማሪ ስራና ሌሎች ስብሰባዎችን፣ በባህላችን መሰረት ሰብሰብ ብሎ ቡና መጠጣትን፣ የለቅሶ የሰርግ የልደት የክርስትና ዝግጅቶችን፣ ከጓድኞች ጋር ተገናኝቶ በምግብ ቤቶች ካፍቴርያዎችና ባሮች መሄድ ማቆምን ባጠቃላይ ማንኝውም ከሰዎች ጋር ተቀራርቦ የሚደረጉ ግንኙነቶችን ማስወገድን አለብን። ጊዜው የሰርግ ወቅት ባይሆንም ምናልባት የታሰቡ ሰርጎችና ሌሎች ድግሶች ለሌላ ግዜ መተላለፍ አለባቸው። ለቅሶ አለመድረስ ትልቁ ችግር ሊሆን ነው፤ ቢሆንም በምንም አይነት በአንድ ላይ ተሰብስበን መድረስ የለብንም። ይህን ማድረግ ለኛ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን መጠበቅም ነው፤ በዚህ ሰአት ብዙ ነፍሰጡሮች ህክምና ይፈልጋሉ፤ ለሃኪሞችም ማሰብ ያስፈልጋል፤ የታማሚውን ቁጥር ማብዛት የለብንም።
እንደ ኢትዮጵያ አይነት ጥብቅ የሆነ ማህበራዊ ትስስር ባለበት ሃገር እነዚህን ማስቀረት ቀላል ባይሆንም የማይቻል አይደለም። ጉዳዩ የራስ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ የሃገር እና የሰው ልጆች ጤንነት ስለሆነ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ከሁላችንም ይጠብቃል።
ከዚህ ርእስ ብዙ ሳንወጣ ቫይረሱ የእድሜ ባለጸጋዎች ላይና በተለያየ በሽታዎች በሽታ የመከላከል ሃይላቸው ደካማ የሆኑ ሰዎችን እንደሚያጠቃ አውቀን በቻልነው እነሱን መርዳት አንርሳ። አቅመ ደካማ ጎረቤቶች ካሉን አስቤዛ እንዲሁም ሌሎች አስፈገላጊ እለታዊ ነገሮችን በማድረግ እናግዝ እና በተቻለ መጠን ከቤት እንዳይወጡ እንተባበራቸው። ይህን ቫይረስ እርስ በርስ በመተሳሰብና በመረዳዳት በጋራ እናሸንፈው።

