YetenaWegLogo

እስትሮክ (STROKE)

Oct 30, 2021

በዶ/ር ናታን ሙሉብርሃን (የድንገተኛና ፅኑ ህክምና ስፔሻሊስት)

በአለማችን ላይ ወደ 5.5 ሚሊዮን ህዝብ በየአመቱ በስትሮክ የሚጠቃ ሲሆን ከ 65 አመት በላይ ላሉ ሰዎች እስትሮክ ቀዳሚ የአካል ጉዳተኝነት መንስኤም ነው። እስትሮክ አጣዳፊ የሆነ የአንጎል ስራ መታጎል ሲሆን የሚከሰተውም ወደ አንጎል የሚሄደው ደም ሲገታ ነው። አንጎል ስራውን በትክክል ለመስራት በኦክስጅን የበለፀገ ደም እንዲሁም የተለያዩ ንጥረ ነገሮች (ግሉኮስ፣ አሚኖ አሲድ፣ ስብ ወዘተ…) ያስፈልጉታል። እነዚህ ነገሮች ከተቋረጡ ደግሞ የአንጎል ህዋሶች በደቂቃዎች ውስጥ ላይመለሱ ይሞታሉ።

እስትሮክን በሁለት ዋና ምድብ የምንከፍለው ሲሆን፤ ይህም

1) እስኬሚክ እስትሮክ (Ischemic Stroke)ይህ የሚፈጠረው የአንጎል ደም ፍሰት በደም ስር መጥበብ ወይም በረጋ ደም ምክንያት ሲገታ ነው። የረጋ ደም (ትሮምበስ) ከልብ እንዲሁም ከተለያዩ የደም ስሮች ግድግዳ ላይ ሊነሳ ይችላል። 80 በመቶ የሚሆነው ስትሮክ እዚህ ውስጥ የሚመደብ ነው።

2) ሄሞራጂክ እስትሮክ (Hemorrhagic Stroke) ፡ በአንጎል ውስጥ የሚገኙ የደም ስሮች በተለያየ ምክንያት ሲቀደዱና ደም በአንጎል ውስጥ ሲፈስ የሚከሰት ነው። በአብዛኛውን በእድሜ መግፋት፣ ተጓዳኝ ህመሞች (ደም ግፊት፣ የልብ ህመም፣ ኮሌስትሮል መብዛት፣ ስኳር ህመም፣ ከደም ጋር የተያያዙ በሽታዎች) ፣ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል በብዛት መጠጣት፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ለስትሮክ ተጋላጭነትን ይጨምራሉ።

የስትሮክ ምልክቶች፡

እስትሮክ የተለያዩ የአንጎል ክፍሎችን ሊያጠቃ ይችላል፤ ታማሚውም ጉዳት እንደደረሰበት የአንጎል ክፍል የተለያዩ ምልክቶች ያሳያል።

  • የንግግር መኮላተፍ (መተሳሰር)፣
  • የሰውነት መደንዘዝ (መዝለፍለፍ) እና የእጅና እግር አለመታዘዝ፣
  • የፊት በከፊል መዛነፍ፣
  • ሃይለኛ የሆነ ራስ ምታት፣
  • ራስን መሳት እና ንቃት መቀነስ፣ ትኩረት ማጣት
  • ለመዋጥ መቸገር፣ የስሜቶች መዘበራረቅ፣
  • አንድ ግለሰብ በስትሮክ መጠቃቱን ከጠረጠሩ
  • ግለሰቡን እንዲስቅ ወይም ጥርሱን እንዲያሳይ ይጠይቁ- እስትሮክ ካለ ፊቱ በአንድ በኩል ይዛነፋል።
  • ግለሰቡን ሁለቱንም እጆች ከፍ እንዲያደርግ ይጠይቁ፤ ሁለቱንም እጆች እኩል ማንሳት መቻላቸውን ይዩ- እስትሮክ ካለ ለማንሳት ይቸገራሉ።
  • ቀላል የሆኑ አረፍተ ነገሮችን መልሰው እንዲደግሙ ያድርጉ። ሲናገሩ መኮላተፍ ወይም መንተባተብ ካለ እስትሮክ ሊሆን ይችላል፡፡

ለስትሮክ ህመምተኛ የሚደረጉ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታዎች ምንድን ናቸው?

  • 911 (ኢትዮጲይ ውስጥ 907) ላይ ይደውሉና እርዳታን ይጠይቁ።
  • ተጎጂውን መቀመጥ ከቻለ እንዲቀመጥ ያድርጉ፤ መቀመጥ ካልቻለ ደግሞ በማገገሚያ አቀማመጥ (Recovery Position) ያስተኙት።
  • ተጎጂውን ያረጋጉት፤ እረፍት እንዲያገኙ ያድርጉ።
  • ምግብና ውሃ ለትንታ ስለሚያጋልጥ አይስጧቸው።
  • ተጎጂው ራሱን አለመሳቱንና በትክክል እየተነፈሰ መሆኑን ያረጋግጡ።
  • ተጎጂው መተንፈስ ካቆመ እስትንፋስ መስጠት(CPR) ይጀምሩ።
  • ወደ ህክምና ተቋም ከሄዱ በኃላም የተለያዩ ምርመራ እንዲሁም የጭንቅላት ሲቲ ስካን (Brain CT Scan) ምርመራ ይደረጋል። ሲቲ ስካን ለስትሮክ እጅግ ጠቃሚ የሆነ ምርመራ ሲሆን የስትሮክ አይነቱን ለመለየት እንዲሁም የተጎዳውን የአንጎል ክፍል ለመለየት ይጠቅመናል።
  • የስትሮኩ አይነት ከተለየ በኃላ ቀጣይ ህክምና ይደረጋል።
  • እስኬሚክ እስትሮክ ከሆነ የደም ፍሰቱን የገታውን የረጋ ደም ለማፍረስ የሚደረግ ህክምና በመድሃኒትቶች (Thrombolysis) ወይም በቀዶ ህክምና (በሰርጀሪ) ሊሰጥ ይችላል። በተጨማሪም እንደ አስፐሪን፣ ክሎፒዶግሪል ያሉ መድሃኒቶችን ተጨማሪ ስትሮክ እንዳይከሰት እንጠቅማለን።(በሐኪም ትእዛዝ ብቻ!!!)
  • ሄሞራጂክ ስትሮክ ከሆነ ደግሞ የተቀደደውን/የፈነዳውን የደም ስር በቀዶ ህክምና በመቋጠር ህክምና የሚሰጥ ሲሆን በተጨማሪም የፈሰሰው ደም ትልቅ ከሆነና በአንጎል ላይ ግፊትን የሚጨምር ከሆነ በቀዶ ህክምና ደሙ ይጠረጋል።
  • የተከሰተበት ምክንያት በደም ማቅጠኛ መድሃኒት (ዋርፋሪን፣ ሄፓሪን…) ምክንያት ከሆነ እሱን ለማርከስ የተለያዩ መድሃኒቶች (ቫይታሚን ኬ፣ ፕሮታሚን…) ይሰጣሉ።
  • ስትሮክ ክትትልን የሚፈልግ ህመም ሲሆን የኦክስጅን መጠን፣ የደም ግፊትን መቆጣጠር፣ የስኳር መጠን ማስተካከል፣ ትኩሳት እንዲሁም ኢንፌክሽን እንዳይከሰት እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ክትትሎች በጤና ተቋም ውስጥ ይሰጣሉ።
  • በተጨማሪም የዛለውን ክፍል ለማነቃቃት የፊዚዮቴራፒ ህክምና ክትትል ያስፈልጋል።

እስትሮክ እንዳይከሰት ለመከላከል ምን መደረግ አለበት?

  • የደም ግፊት በትክክል መቆጣጥርና የታዘዘን መድሃኒት በትክክል መውሰድ፣
  • የጨው መጠን ከምግብ ወስጥ መቀነስ፤
  • የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርአት መከተል፤(ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ፣ የእጽዋት ተዋጽኦ ዘይቶችን…)
  • የኮሌስትሮል መጠን መቀነስ፤
  • ስኳር ህመም ካለ በአግባቡ ክትትል ማድረግ፣
  • አደንዛዥ ዕፅ ከመጠቀም፣ ሲጋራ ከማጨስ፣ አልኮል ከመጠቀም መቆጠብ
  • ከመጠን ያለፈ ውፍረት ማስወገድ እንዲሁም አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል።

Recent Posts