YetenaWegLogo

የሚጥል በሽታ

Dec 01, 2021

የሚጥል በሽታ
በዶ/ር ናታን ሙሉብርሃን (የድንገተኛና ፅኑ ህክምና ስፔሻሊስት)

የሚጥል በሽታ አንጎላችን ድንገተኛ በሆነና በተዛባ መልኩ መልዕክቶችን ወደ ተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች መልቀቅና ይህንንም ተከትሎ ሰውነታችን ላይ የእንቅስቃሴ፣ የባህርይ ወይም የስሜት ለውጥ መከሰት ነው፡፡
የሚጥል በሽታ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፣ ከነዚህም መካከል ኢፒለፕሲ፣ ከፍተኛ ትኩሳት (በህፃናት ላይ) ፣ ኢንፌክሽን፣ የጭንቅላታት ላይ አደጋዎችና የሰውነት ንጥረ ነገሮች መዛባት የሚጠቀሱ ናቸው።
በአጠቃላይ የሚጥል በሽታ ለጥቂት ደቂቃ ብቻ ይቆያል፤ ነገር ግን ከአምስት ደቂቃ በላይ ማንቀጥቀጡ ከቆየ ወይም ደጋግሞ ካንቀጠቀጠና በመሃሉ ራስን እንደሳቱ ከቆዩ እስታትስ ኢፒለፕቲከስ (status epilepticus) ይባላል፡፡ ይህም አደገኛ ነው ምክንያቱም የአንጎላቸንን ህዋስ በቋሚነት ስለሚጎዳ፡፡
ብዙ አይነት የሚጥል በሽታ ሲኖር አጠቃላይ የተጠቃውን የአንጎል ክፍል አይተን ከውስን የአንጎል ክፍል የሚነሳ (focal) እና አብዛኛውን የአንጎል ክፍል የሚያካልል (Generalized) ብለን እንመድበዋለን። ከዚህም በተጨማሪ ራሱን የሳተና ያልሳተ ብለን እንከፋፍለዋለን። የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች ማንቀጥቀጡ ከመምጣቱ በፊት የሚሰማቸው ቅድመ ምልክት ይኖራል፤ ይህም ሲሆን አጠገባቸው ላለ ሰው ሁኔታውን በማስረዳት አደጋ በማይፈጥር ቦታ መቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡

የሚጥል በሽታ የመጀመሪያ እርዳታ
• ይረጋጉና ከታማሚው ጋር ይቆዩ፤
• ምግብ ወይም መጠጥ በታማሚው አፍ ውስጥ ካለ ወደ አየር ቱቦ እንዳይገባ ታማሚውን በጎን ያስተኙት፤
• የሚንቀጠቀጠውን ታማሚ መንቀጥቀጡን በእጅ ይዘው ለማቆም አይሞክሩ፤
• ማንቀጥቀጡ እስኪቆም እየጠበቁ አካባቢያቸው ካለ አደጋ ሊፈጥር የሚችል ነገር ይጠብቋቸው፤
• ለስለስ ያሉ ነገሮችን አንገታቸውና ጭንቅላታቸው ስር ያኑሩ፤
• በተለምዶ እንደሚደርገው የክብሪት ጭስ የመሳሰሉትን በፍፁም አይጠቀሙ
• ምላስ ይውጣል በሚል ምክንያት በጥርሶቻቸው መካከል እንጨትና የመሳሰሉትን ማስገባት ተገቢ አይደለም፣ ይበልጡኑ ለማስገባት በሚደረገው ትግል ጥርስ ሊሰበር ከመቻሉም በላይ እንጨቱም ተሰብሮ ወደ አየር ቱቦ በመግባት ትንታን እና መታፈንን ሊፈጠር ይችላል፡፡
• የማንቀጥቀጡን ርዝመት ከቻሉ ሰዓት ይዘው ይመዝግቡት፡፡
• ማንቀጥቀጡ ካቆመ በኃላ ታማሚውን በማገገሚያ (ሪከቨሪ) አስተኛኘት ያስተኟቸው። (ምስል ላይ እንድሚታየው)
• ከላይ እስከ ታች በማንቀጥቀጡ ምክንያት የደረሰ ጉዳት ካለ ይመርምሩ፤
• ታማሚው መተንፍስ ካቆመ ትንፋሽ መስጠት ይጀምሩ።

 

 

 

 

 

 

ከታች የተዘረዘሩት ካሉ በአፋጣኝ ወደ አንቡላንስ ይደውሉ ወይም ወደ ጤና ተቋም ይዘው ይሂዱ
• ማንቀጥቀጡ ከ 5 ደቂቃ በላይ የሚቆይ ከሆነ ወይም ተጠቂው ሳይነቃ ማንቀጥቀጡ የሚደጋገም ከሆነ
• በማንቀጥቀጡ ወቅት ታማሚው አደጋ ከደረሰበት
• ታማሚው የማይተነፍስ ከሆነ
• ነፍሰ ጡር ከሆነች
• ስኳር በሽተኛ ከሆነ
• ህጻናት ሆነው ማንቀጥቀጡ በሃይለኛ ትኩሳት ከመጣ
• በእድሜ የገፉ ከሆኑ
ያስታውሱ፡ የሚጥል በሽታ ተገቢውን ምርመራ እና ህክምና ከተደረገለት፤ ማንቀጥቀጡ የመከሰት እድሉን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እና መቆጣጠር ይቻላል።

Recent Posts