YetenaWegLogo

የእብድ ውሻ በሽታ (Rabies)

Aug 27, 2022

በዶ/ር ናታን ሙሉብርሃን (የድንገተኛና ጽኑ ህክምና ስፔሻሊስት )

የእብድ ውሻ በሽታ በእንግሊዘኛው አጠራር ሬቢስ ከሒንዱ ሳንስክሪት ራብሐስ (Rabhas) ቃል የፈለሰ ሲሆን ይህ በሽታ ዝምተኛ፣ ለጌታው ታዛዥና ጓደኛ የነበረ ውሻ በድንገት ወደ አስፈሪ የአውሬነት ባህሪ የሚለወጥበት ሁኔታ ያሳያል። የእብድ ውሻ በሽታ (Rabies) በቫይረስ አማካኝነት በበሽታው ከተለከፈ እንስሳ ወደ ሌላ ጤነኛ እንስሳ ወይም ወደ ሰው በንክሻ የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን ውሻን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ደመ ሞቃትና አጥቢ የሆኑ እንስሳትን እንዲሁም ሰውን የሚያጠቃ በሽታ ነው።

ውሻን የሚያሳብደው በሽታ ራብዶቫይረስ በተባለ ቫይረስ የሚመጣ በሽታ ሲሆን፤ ሁሉንም ደመ ሞቃት አጥቢ እንስሳን፣ ሰውንም ጨምሮ የሚያጠቃ ነው። ቫይረሱ ወደ ተነካሹ አካል ከገባ በኃላ ለመራባት የግድ ራሱን ከነርቭ ሕዋስ ጋር ማጣበቅ ይኖርበታል። የዚህን በሽታ ቫይረስ ከሌሎች የቫይረስ አይነቶች ልዩ የሚያደርገው መኖሪያው ወይም መራቢያው በነርቭ ሕዋስ በአመዛኙ አንጎል ውስጥ መሆኑ ነው።

በሽታው ዋና መተላለፊያ መንገድ ንክሻ ነው፤ ነገር ግን በበሽታው ከተለከፈ እንስሳ ጋር በሚደረግ ጥንቃቄ የጎደለው ንክኪ በተለይ የአበደው እንስሳ ለሀጭ ባልተሸፈነ ቁስል ላይ ሲያርፍ የበሽታው ቫይረስ ወደ ጤነኛ ሰውም ሆነ እንስሳ አካል ገብቶ በሽታው ሊተላለፍ ይችላል። በአለም እስካሁን ድረስ በምርምር በሽታው ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ የተረጋገጠ መረጃ የለም።

ውሻን የሚያሳብድ በሽታ በተለምዶ ስሙ የእብድ ውሻ በሽታ እየተባለ ይጠራ እንጂ በበሽታው የሚጠቁ እንስሳት ብዙ ናቸው፡፡ ውሻን በሚያሳብድ በሽታ ከሚጠቁ የቤት እንስሳት ውስጥ ድመት፣ በሬ፣ ላም፣ በግ፣ ፍየል፣ አህያ፣ ፈረስና በቅሎ እንዲሁም ዱር እንስሳት ቀበሮ የለሊት ወፍ ተጠቃሽ ናቸው

የበሽታው ምልክቶች በሰውም ሆነ በእንስሳት ላይ የሚታዩት የቫይረሱ የመራቢያ ወይም የመደራጃ ጊዜውን በአንጎል ክፍል ከጨረሰ በኋላ ነው። ቅድመ ሕመም (Incubation Period) የምንለው አንድ ሰው ከተነከሰበት ቀን ጀምሮ የሕመም ምልክት እስከሚጀመረበት ያለውን የቫይረሱን የመደራጃ ጊዜ ነው። የቫይረሱን የመራቢያ ጊዜ አጭር ወይንም ረጅም መሆኑን የሚወስኑት የቁስሉ ጥልቀት ወይም ስፋት፣ በንክሻው ጊዜ የገባው የቫይረስ መጠን፤ የሰውየው በሽታ የመከላከል አቅም ናቸው። ቁስሉ እየሰፋና እየጠለቀ በሄደ ቁጥር የሚገባው የቫይረስ መጠን እጅግ የበዛ ሲሆን ወይም ቫይረሱ የነርቭ ሕዋስን የማግኘት እድሉ እየጨመረ ስለሚሄድ የመራቢያ ጊዜው አጭር ይሆናል።

በበሽታው የተጠቃ ሰው በመጀመሪያ ንክሻው የደረሰበት አካባቢ መለብለብ፣ መደንዘዝ፣ መዛል ያጋጥመዋል። እየቆየም ሲሄድ ሄድ መለስ የሚል የመዋጥ መቸገር፣ ለሃጭ መዝረክረክ፣ ራስን ችሎ መቆም አለመቻል፣ የማስታወስ ችግር፣ መቃዠት፣ ትኩሳት፣ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ ይኖረዋል፡፡ ወደ 10ኛው ቀን ላይ ደግሞ ራሱን ሙሉ ለሙሉ ይስትና ኮማ ውስጥ ይገባል።

 

የእብድ ውሻ በሽታ ህክምና

    • አንዳንድ ጊዜ ንክሻ የፈጸመው እንስሳ ወይም ውሻ ክትባት የተከተበ ከሆነና ወደ ምርመራ ተቋም መውሰድ ካልተቻለ እንስሳው ባለበት አስሮ ለ10 ቀናት መከታተል የሚቻል ሲሆን እንስሳው በተጠቀሰው ቀነገደብ ውስጥ ሰንሰለቱን በጥሶ ቢጠፋ እንስሳው ውሻን በሚያሳብደው በሽታ ተለክፎ ሊሆን ይችላል የሚለውን ግምት በከፍተኛ ደረጃ ስለሚያጠናክረው ተነካሹ ግለሰብ ሁኔታውን ለጤና ባለሞያ ማሳወቅ ይኖርበታል።
    • በዚህ አስር የክትትል ቀናት ውስጥ ምንም አይነት አካላዊም ሆነ ባህሪያዊ ለውጥ ካላሰየና ምግብ እየበላ፣ እየጠጣ በሕይወት ከቆየ ንክሻ በፈጸመበት ሰዓት ወደ ተነካሹ ሰው በሽታ አለማስተላለፉንና ተነካሹ ከበሽታው ነጻ መሆኑ ይረጋግጣል፡፡
    • እንስሳው ከሞተ ደግሞ ጭንቅላቱን ቆርጦ ለምርመራ ወደ ህክምና ተቋም መላክ ያስፈልጋል፡፡ በእንስሳትም ሆነ በሰዎች በበሽታው ለመያዛቸው ለማረጋገጥ የሚያስችል የቅድመ ምርመራ የለም።
    • ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ምልክት ለታየበት ሰው ከበሽታው ለመፈወስ የሚደረግ የሕክምና እርዳታ ስለሌለ ሰዎች የመዳን እድላቸው በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ለበሽታው ሊያጋልጥ የሚችል ንክሻ ወይንም ከእንስሳው ምራቅ ወይም ለሀጭ ጋር ንክኪ ካለው ጊዜ ሳይሰጡ ሀኪም ማማከር ያስፈልጋል።
  • የመጀመሪያ የሕክምና ዕርዳት
  1. የተነከሰው አካል በውሃና በሳሙና ወይም በአልኮል በደንብ ማጠብ፤ ይህም ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በመጠኑ ቫይረስ መጠን ይቀንሳል።
  2. ንክሻ የፈጸመው እንስሳ በሕይወት ካለ ለእንስሳት ሐኪም አሳይቶ ለ10 ቀን ክትትል እንዲደረግለት መደረግ አለበት።
  3. በልዩ ልዩ ምክንያት በክትትል ላይ ያለው እንስሳ ቢያመልጥ ተነካሹ ሰው ወዲያውኑ የመከላከያ ክትባት መውሰድ ይኖርበታል።
  4. ንክሻ የፈጸመው እንስሳ በበሽታው ተለክፏል ተብሎ የሚጠረጠር ከሆነ እንስሳውን ገድሎ ወይንም በ10 ቀን ክትትል ጊዜ ውስጥ ቢሞት ጭንቅላቱን ቆርጦ እንዲመረመር ማድረግ አለበት፡፡ የቀረውን የሰውነት ክፍል (በድን) ማቃጠል ወይም አርቆ መቅበር ያስፈልጋል። ይህም ከሚመለከታቸው የህብረተሰብና የእንስሳት ጤና ባለሞያዎች ጋር ቢደረግ ተመራጭ ነው።
  5. የእንስሳው ጭንቅላት ተመርምሮ በበሽታው ተጠቂ መሆኑ ከተረጋገጠ ተነካሹ ሰው በአስቸኳይ የመከላከያ ክትባት መከታተል ይኖርበታል።
  6. በበሽታው ተይዞ ሕመሙ የጀመረው ሰው ለሀጭ ማዝረብረብና ለመናከስም ስለሚከጅል በጥንቃቄ ማስታመም አስፈላጊ ነው፡፡ ከለሀጭ ጋር ከሚደረግ ንክኪ ባሻገር በሽተኛው አስታማሚው ፊት ላይ ሊተፋ ስለሚችል በሽተኛውን በጣም ባይቀርቡት ይመረጣል፡፡
  7. በተረፈ ግን የእጅ መሸፈኛ ላስቲክ ወይም ጓንት በማድረግ ማስታመምና የሚፈለገውን እርዳታ መስጠት ይቻላል፡፡ ለበሽተኛው የሚፈለገው እርዳታ ከተከናወነ በኋላ በደንብ እጅና ፊትን በሳሙና መታጠብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ለሚደረግ ማንኛውም ለበሽታው የሚያጋልጥ ንክኪ ሲኖር ሐኪም ማማከር ያስፈልጋል።

 

  • የመከላከያ ክትባት
    • የንክሻው ዓይነት ከበድ ያለ ከሆነ በተለይም ከአንገት በላይ የተፈጸመ ንክሻ ከሆነ እንዲሁም ንክሻው ሰፋ ያለ ቦታ የሚሸፍን ከሆነ የእንስሳው የ10 ቀን ክትትል ውጤት እስኪታወቅ ድረስ ተነካሹ የመከላከያ ክትባት መጀመር ይኖርበታል።
    • በተጨማሪም ኢሙኖግሎቡሊን (Rabies Immunoglobulin) በቁስሉ ዙርያ በመስጠት ቫይረሱ ወደ ነርቭ እንዳይሰራጭ እዚያው በተወሰነ ደረጃ ለማገድ ይረዳል፡፡
    • ውሻን ለሚያሳብደው በሽታ መከላከያ ክትባት ለሰዎች የሚሰጠው በሁለት አይነት ሁኔታዎች ነው፡፡ እነዚህም ቅድመ-ንክሻ እና ድህረ-ንክሻ መከላከያ ክትባት በመባል ይታወቃሉ፡፡
      • ቅድመ-መጋለጥ ክትባት (Pre-exposure) የሚባለው ከእንስሳት ጋር በቅርበት ለሚሰሩ ባለሞያዎች፤ ለእንስሳት ሀኪሞች፤ የበሽታው ምርመራ በሚከናወንበት ላብራቶሪ ውስጥ ለሚሰሩ፤ በዱር እንስሳት ጥበቃና ፓርክ ሰራተኞች፤ በሆስፒታል የጤና ባለሞያዎችና ተጓዦች በተለየ መልኩ ለበሽታው ሊጋለጡ ስለሚችሉ የሚሰጥ የመከላከያ ክትባት አይነት ነው፡፡
      • ድህረ-መጋለጥ መከላከያ ክትባት (Post-exposure) የሚባለው ደግሞ በተለይ የበሽታው አምጪ የሆነው ቫይረስ በንክሻም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ የሚሰጥ ክትባት ነው፡፡ ይህም የመከላከያ ክትባት መውሰድ የሚገባቸው በበሽታው ተለክፏል ተብሎ በተጠረጠረ ወይም በተረጋገጠ እብድ እንስሳ የተነከሱ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡

Recent Posts