YetenaWegLogo

እሳት አደጋና የመተንፈሻ አካላት በጢስ መጎዳት

Nov 05, 2021

እሳት አደጋና የመተንፈሻ አካላት በጢስ መጎዳት
በሳባ ሀብቱ (በአ.አ.ዩ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ የ3ኛ ዓመት የህክምና ተማሪ)

የእሳት አደጋ በሚከሰትበት ወቅት በቃጠሎው ከሚደርሰው ቀጥተኛ ጉዳት በተጨማሪ በጢሱ ምክንያት የሚፈጠሩት አደጋዎች ብዙ ናቸው። አንድ ሰው በቃጠሎ ወቅት የመተንፈሻ አካላቱ ለቀጥተኛ ሃይለኛ ሙቀት እንዲሁም በቃጠሎው ምክንያት ለተፈጠሩ መርዛማ ኬሚካሎች ሊጋለጥ ይችላል። የጢሱ አይነትና የሚይዛቸው ንጥረ ነገሮች እንደተቃጠለው ቁስ እና በአከባቢው እንደነበረው የአየር ሁኔታ የሚለያይ ሲሆን በአብዛኛው አየር እንደልብ የማይዘዋወርበት ከሆነና ቃጠሎው የተከሰተበት የአከባቢው ሙቀት ቀዝቀዝ ያለ ከሆነ የጢሱ መጠን ከፍ ያለ ይሆናል። በዚህም ወቅት የሚፈጠረው ጢስ ካርቦን ሞንኦክሳይድ፣ አሞንያ እና ሌሎችም የተለያዩ ጐጂ ንጥረነገሮችን የያዘ ሲሆን እነዚህ ንጥረነገሮች በሚደባለቁበት ጊዜ የሚፈጠረው መርዛማ ድብልቅ በመተንፈሻ አካላት ላይ ጉዳት ያመጣል።
የጢስ መተንፈስ አደጋ በእሳት ቃጠሎ አደጋ ጊዜ ለሞት ከሚዳረጉ አደጋዎች ውስጥ በቀዳሚነት ይመደባል።
ለዚህ አደጋ ተጋላጭ ከሆኑት ውስጥ
በአደጋ ጊዜ ራሳቸውን ለማዳን የማይችሉ የማህበረሰባችን ክፍሎች ( ህፃናት፣ አዛውንትና አረጋዊያን፣ የአካል ጉዳተኞች ፣ የአዕምሮ ህመምተኞች ወዘተ)
የአልኮልና የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚዎች፣
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች እና
የጢስ መጠን መጠቆሚያ የሌላቸው መኖሪያ ቤቶች ተጠቃሾች ናቸው።
አደጋው በሰውነታችን ውስጥ በሶስት መንገዶች ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።
ሃይለኛ ሙቀት– በአፍንጫና በአፍ መተንፈሻ አካላት ላይ ጉዳት ያመጣል። በሙቀቱ የሚፈጠረው እንፋሎትም በጉሮሮአችን ላይ እብጠት በማምጣት በሳንባችን አየር በደንብ እንዳይተላለፍ ያደርጋል።
ጥቃቅን ብናኞች እና ንጥረ ነገሮች– በአየር ማስተላለፊያ ቱቦዎች ላይ በመሰብሰብ የአየር ዝውውሩን ከባድ ያደርጉታል። ብናኞቹ የሚፈጥሩትን ስብስብ ለመከላከል የአየር ማሰተላለፊያ ቱቦዎቻችን የተለያዩ ኬሚካሎችን ወደ ህዋሳቶቻችን ይለቃሉ። እነዚህም ኬሚካሎች ለህዋሳቶቻችን ጐጂ ናቸው።
አጠቃላይ የሰውነት መመረዝ – በጢስ ወቅት የሚፈጠሩት መርዛማ ኬሚካሎች ወደ ተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች በመዘዋወር የሰውነታችን አካላት እና ህዋሳት ከደማችን ማግኘት ያለባቸውን ጠቃሚ ነገሮች እንዳያገኙ ያደርጋሉ። ከነዚህም አንዱ ካርቦንሞንኦክሳይድ የተባለው መርዛማ ኬሚካል ሲሆን ይህም በደማችን እየተዘዋወረ ለሰውነታችን ህዋሳት የሚያስፈልጋቸው ኦክሲጅንን ቦታ በመያዝ ህዋሳቶቻችን እንዲሞቱ ምክንያት ይሆናል።
ምልክቶች
ራስን መሳት፣
የራስ ምታት ህመም፣
ግራ መጋባት ፣
በአፍንጫ በአፍ እና በጉሮሮ መተንፈሻ አካላት ላይ የማቃጠል ስሜት፣
ሲውጡ የጉሮሮ ህመም፣
አክታ የቀላቀለ ሳል፣
የትንፋሽ ማጠር ወይም ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣
ሲተነፍሱ ድምፅ ማሰማት፣
የፊት ማበጥ እንዲሁም
በአፍንጫና በአፍ አከባቢ የቃጠሎ ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ።
አንዳንድ ጊዜ ለጢስ መተንፈስ አደጋ የተጋለጡ ሰዎች ምልክት እስኪያሳዩ ድረስ ምንም ጉዳት ያልደረሰባቸው ሊመስለን ቢችልም ውስጣዊ የመተንፈሻና ሌሎች አካላቶቻቸው ተጠቅተው ሊሆኑ ስለሚችል ወደ ህክምና ተቋም ከመውሰድ መታቀብ የለብንም።

ህክምና እና መከላከል
ተጠቂዎችን ከቦታው በቶሎ ማስወጣትና ከአከባቢው ማራቅ ያስፈልጋል። በመቀጠልም በአፋጣኝ የመጀመሪያ እርዳታ የሚሰጥ አምቡላንስ በመጥራት ወደ ህክምና ተቋም እንዲሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል። ለቃጠሎ አጋላጭ የሆኑ ሁኔታዎችን ቀድሞ መለየትና ማስወገድ እንዲሁም ለአደጋው ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን ክትትልና እንክብካቤ ማድረግ ሊፈጠር የሚችለውን ጉዳት እና ሞት በእጅጉ ይቀንሰዋል።

Recent Posts