ምግብን መሰረት ያደረገ የአመጋገብ መመሪያ 

በሀገራችን ቁጥሩ እያሻቀበ የመጣው ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነትና ተጠቂነት ለብዙሀን ህይወት መጥፋት እና የአካል መጉደል ምክንያት ሁኗል። ከጥቂት አመታት በፊት የምዕራባውያን በሽታ ተደርገው ይቆጠሩ የነበሩት ስር የሰደዱ የልብና የአተነፋፋስ ስርዐት በሽታዎች፣ የስኳር በሽታ፣ ካንሰር፣ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደት እንዲሁም በነዚህ በሽታዎች አማካኝነት የሚከሰቱ የተለያዩ አካላት (ዓይን፣ ኩላሊትና ጉበት ወዘተ) ጤና መዛባት ዛሬ ላይ የእያንዳንዳችንን ቤት ማንኳኳት ጀምረዋል። እነዚህ በሽታዎች በዋነኝነት ድህረ ዘመናዊነት ባስከተለው የአኗኗር ዘይቤ መቀየር ምክንያት ከተከሰቱት የአመጋገብ እና የሰውነት እንቅስቃሴ ልምድ ለውጥ ጋር ይገናኛሉ። ይህ ችግር በሌላ በኩል በአብዛኛው በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ጋር ከሚታየው የተመጣጠነ ምግብ እጦት ጋር በተያያዘ ከሚከሰቱት የዐዕምሮና ሰውነት እድገት መቀንጨር፣ የክብደት ማነስና ተያያዥ በሆኑ የጤና ዕክሎች ከሚደርሱ ጉዳቶች ጋር ሲደመር ዜጎች ለአመጋገብና የሰውነት እንቅስቃሴ ተገቢ ትኩረት እና ግንዛቤ ሊኖራቸው እነደሚገባ ያመላክታል። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያውያንን የኑሮ ዘይቤ፣ የገቢ መጠንና ንጥረ ነገሮችን ያገናዘበ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ምግብን መሰረት ያደረገ የአመጋገብ መመሪያ
በመጋቢት 6/ 2014 ዓም በጤና ሚኒስቴር እና አጋር ተቋማት ይፋ ሆኗል።

 

ምግብን መሰረት ያደረገው የአመጋገብ መመሪያ ምንድን ነው? በዋነኝነትስ ምን ላይ ያተኩራል ?

ምግብን መሰረት ያደረገ የአመጋገብ መመሪያ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተዘጋጀ ጤነኛ የሆነ የአመጋገብ ባህልን ለማዳበር ለማህበረሰቡ
ስለ ምግብና ንጥረ ነገሮች ግንዛቤ የሚሰጥ መርሆ ነው።

 

ምግብ ለሰውነታችን ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን ያካተተና በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ማንኛውም የሚበላ ነገር ነው። ንጥረ ነገር ደግሞ ለሰውነታችን ሀይል እና ብርታት የሚሰጥ በምግብ ውስጥ የሚገኝ ነገር ነው። ንጥረ ነገሮች ሰውነታችን እንደ መተንፈስ፡ ምግብን መፍጨት፡ የሰውነት ሙቀትን ማመጣጠን ፡ በሽታ የመከላከል አቅምን ማጎልበት ወዘተ የመሳሰሉ ሂደቶችን ለማያከናውን ይረዳሉ።

በምግብ ውስጥ ስድስት ዓይነት ንጥረ ነገሮች አሉ። እነሱም ሃይል ሰጪ ንጥረ ነገር [ካርቦሃይድሬት]፣ ገንቢ ንጥረ ነገር [ፕሮቲን]፣ ስብ [ፋት]፣ ቫይታሚን፣ ሚኒራል እና ውሀ ናቸው። የአመጋገብ መመሪያውም በምግብ ውስጥ ያሉትን ንጥረ ነገሮች ተመሳሳይነት መሰረት አድርጎ ምግብን በሰባት ደልድሎዋል።

 

  1. ጥራጥሬ፣ ያልተፈተጉ እህሎች ና ስራስር፡ በዚህ ስር በኢትዮጵያ ተዘውትረው ለመብልነት የሚውሉት ጤፍ፡ ማሽላ፡ በቆሎ፡ ገብስ፡ እንሰት ተጠቅሰዋል። ጥራጥሬና ስራስር በሃይል ሰጪ ንጥረ ነገር [ካርቦሃይድሬት]፣ ገንቢ ንጥረ ነገር [ፕሮቲን]፣ ቫይታሚን ቢ፣ ሚኒራል እና ፋይበር የበለጸጉ ናቸው።
  2. አባዝርት [ሌግዩም] ፡ እንደ ባቄላ፣ አተር፣ አኩሪ አተር፣ ምስር የመሳሰሉት ገንቢ ንጥረ ነገር [ፕሮቲን]፣ ቫይታሚን እና ሚኒራል ይይዛሉ።
  3. የቅባት እህሎች፡ እንደ ሱፍ፣ ኑግ፣ ለውዝ እና ተልባ የመሳሰሉት በስብ [አን ሳቹሬትድ ፋት]፣ ሚኒራል እና ቫይታሚን ኢየበለጸጉ ናቸው።
  4. ስጋ፣ አሳ፣ እንቁላል፣ ወተት እና የወተት ተዋፅኦ፡ እነዚህ ደግሞ በስብ፣ ገንቢ ንጥረ ነገር [ፕሮቲን]፣ ቫይታሚን ኤ፣ እና ሚኒራል የበለጸጉ ናቸው። ወተት እና የወተት ተዋፅኦ የልጆች እድገት መቀንጨርን ያስቀራል።
  5. አትክልት እና ፍራፍሬ፡ እንደ ፓፓዬ፣ ሙዝ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ የመሳሰሉት ፍራፍሬዎች ቫይታሚን ኤ፣ ቫይታሚን ሲ እና ሚኒራል ሲይዙ እና ቀይስር፣ ሰላጣ፣ ጎመን፣ ቆስጣ የመሳሰሉት አታክልት የተለያዩ ቫይታሚኖችንና ሚኒራሎችን ይይዛሉ።
  6. ስብ እና ቅባት፡ እነዚህ ለሰውነታችን ከፍተኛ ሃይል የሚሰጡ ሲሆኑ ልክ በሆነ መጠን ለሰውነታችን እድገት ያስፈልጋሉ። በዚህም ስር የምግብ ዘይት እና ቅቤ ይካተታሉ።
  7. ውሀ፡ ውሀ የሰውነታችንን ስልሳ እጅ የሚሸፍን ሲሆን የተለያዩ ንጥረነገሮችን በሰውነታችን ውስጥ እንዲዘዋወሩ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች ብዙ ስራዎችን ያከናውናል።

 

ምግብን መሰረት ያደረገው የአመጋገብ መመሪያ ማንን ይመለከታል ?

ሴቶችንና ህፃናትን ጨምሮ ማንኛውንም ዕድሜው ከሁለት ዓመት በላይ የሆነውን አጠቃላይ የማህበረሰብ አካል ይመለከታል።

 

ምግብን መሰረት ያደረገው የአመጋገብ መመሪያ አብይ መርሆች ምንድን ናቸው ?

መርህ 1 ፡ በቀን ውስጥ የምንመገባቸውን ምግቦች ቢያንስ አራት የምግብ ዓይነቶችን እንዲያካትቱ ማድረግ

  • ከላይ በጉልህ እንደተመለከትነው ሁሉንም የንጥረ ነገር ዓይነት የያዘ አንድም የምግብ ዓይነት የለም። ስለዚህ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን እያደበላለቁ መመገብ ለጤናማ ኑሮ ተገቢ ነው። ለአብነት ያህል የተዘጋጀው ምግብ ድንች ወጥ በጤፍ እንጀራ ከሆነ ካጠገቡ ሰላጣ፣ አይብ ወይም ጎመን ማድረግ እንዲሁም ሌሎች የምግብ ዓይነቶች ማካተት ተገቢ ነው።

 

መርህ 2 ፡ በየቀኑ አባዝርት [ሌግዩም] ፡ እንደ ሽሮ ወጥ ፣ ቆሎ፣ ምስር ወጥና ባቄላ ያሉትን መመገብ

  • እነዚህ በገንቢ ንጥረ ነገር [ፕሮቲን] የበለጸጉ ሲሆኑ እነዚህን መመገብ ክብደትን ለመቆጣጠረ እና ጤነኛ የሆነ የልብና የአተነፋፋስ ስርዐት እንዲኖረን ያደርጋል።

መርህ 3 ፡ በየቀኑ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ መመገብ

  • አትክልትና ፍራፍሬ ከፍተኛ የሆነ የቫይታሚን፣ ሚኒራል እና ፋይበር ይዘት ስላላቸው በሽታ የመከላከል አቅምን ያጎለብታሉ እንዲሁም ለጤነኛ ዕይታ የጎላ አስተዋጾ አላቸው።

መርህ 4 ፡ በየቀኑ የተለያዩ የቅባት እህሎች መመገብ

  • እነዚህን ምግቦች በ ቆሎ፣ ሱፍ ፍትፍት፣ ለውዝ ቅቤና ተልባ ፍትፍት መልኩ መመገብ ይቻላል። እነዚህ እህሎች ጤነኛ የሆነ የልብና የአተነፋፋስ ስርዐት እንዲኖረን ያደርጋሉ።

መርህ 5 ፡ ስጋ፣ እንቁላል፣ የተፈላ ወተት እና የወተት ተዋፅኦ መመገብ

  • ከእንስሳት የሚገኙ ምግቦች በገንቢ ንጥረ ነገር [ፕሮቲን] የበለጸጉ ሲሆኑ ጤናማ ለሆነ እድገት አስተዋጾ ያደርጋሉ። ጉበት፣ ኩላሊት የመሳሰሉት የውስጥ አካላት ደግሞ አይረን ስለሚይዙ ደም ማነስን ይከላከላሉ። ወተት በ ካልሲየም የዳበረ ሲሆን ጤነኛ ጥርስ እና አጥንት እንዲኖረን ያደርጋል። ስጋን ስንመገብ አብስለን መመገብ እንደሚገባ መዘንጋት የለበትም።

መርህ 6 ፡ በቀን ከ ስምንት እስከ አስር ብርጭቆ ውሃ መጠጣት

  • ውሃ ለተለያዩ የሰውነት ተግባራተ ትልቅ ሚና አለው። ለምሳሌ ለተስተካከለ የደም ግፊት፣ በሰውነት ውስጥ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን ለማዘዋወር፣ የምግብ መፈጨትን ለማሳለጥ፣ ድርቅትን ለመከላከል፣ የቆዳን ልስላሴና ውበት ለመጠበቅ ወዘተ ይረዳል።

መርህ 7 ፡ በቀን ቢያንስ ለ ሰላሳ ደቂቃ የሰውነት እንቅስቃሴ ማከናወን

  • የእግር መንገድ፣ ሩጫ፣ ገመድ ዝላይ እንዲሁም የተለያዩ የቤት ውስጥ ስራዎችን የመሳሰሉ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን ማከናውን ከልብ በሽታ፣ ስኳር በሽታ፣ ስትሮክ እና ከአንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች ይታደጋል። በተጨማሪም ቀናችንን በንቃት እና ቅልጥፍና እንድናሳልፍ ይረዳናል።

መርህ 8 ፡ በየቀኑ መጠነኛ የሆነ ስብና ቅባትን መጠቀም

  • ስብና ቅባት ለሰውነታችን ሃይል ይሰጣሉ እንዲሁም ሰውነታችን ቫይታሚኖችን እንዲጠቀም ይረዳሉ። ከእንስሳት ተዋጽኦ ከሚገኙ ቅባቶች (ቅቤ) ይልቅ ከዕፅዋት የሚገኙ ቅባቶችን (የኑግ፣ ሱፍ፣ አኩሪ አተር ወዘተ ዘይት) መጠቀም ይመረጣል።

መርህ 9 ፡ ስኳር፣ ጣፋጭ እና ለስላሳ መጠጦችን አብዝቶ አለመጠቀም

  • በአሁኑ ሰዓት በምንወስዳቸው ትኩስ መጠጦች ውስጥ፣ በታሸጉ ምግቦችና መጠጦች ፣ ኬክ፣ ኩኪስና የተለያዩ የተዘጋጁ ምግቦች ውስጥ ጣፋጮችን አብዝተን እንጠቀማለን። ስኳር ከመጠን ላለፈ ውፍረት፣ ለጥርስ መቦርቦርና የስኳር በሽታ ለመሳሰሉት ተጋላጭ ያደርጋል። እንደ ቡናና ሻይ ያሉ ትኩስ መጠጦችን ያለ ስኳር የመጠጣት፣ ከለስላሳ መጠጦች ይልቅ ውሀን የመጠጣትና ከታሸጉ ጣፋጮች
    የመቆጠብ ልምድን ማዳበር ጤነኛ ሰውነት እንዲኖረን ያደርጋል።

መርህ 10 ፡ አነስተኛ የሆነ የጨው መጠንን መጠቀም

  • በቀን ውስጥ የምንወስደውን የጨው መጠን ከአንድ የሻይ ማንኪያ በታች በማድረግ ከደም ብዛት እራስን መጠበቅ ይቻላል። የምንጠቀመው ጨው ደግሞ አዮዲን ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብናል። እንደ ቡና በመሳሰሉ ትኩስ መጠጦች ውስጥ ጨውንከመጠቀምና በጨው የተሰሩ የታሸጉ ምግቦችን ከመመገብ መቆጠብ ላላስፈላጊ ከፍተኛ የጨው መጠን ተጋላጭ እንዳንሆን ያደርገናል።

መርህ 11 ፡ የአልኮል መጠጥ አለመጠቀም ቢቻል በሳምንት ከ ሁለት ብርጭቆ በላይ አልኮል አለመጠጣት

  • በቤት ውስጥ የተዘጋጁትንም ሆነ በፋብሪካ የተቀነባበሩ የአልኮል መጠጦችን መጠቀም የተለያዩ አካላቶቻችን ላይ ጉዳት ከማድረሱም በላይ ለሱሰኝነትና ላልተፈለገ ማህበራዊ ኪሳራ ይዳርጋል። በተለይ ደግሞ በእርግዝና ወቅት አልኮልን መጠቀም በጽንሱ ላይ የእድገት መቀንጨር፣ የማየትና የመስማት ችግር፣ ያለግዜ መወለድ እና የልብ በሽታን ያስከትላል።

 

ዋቢ

  • Federal Government of Ethiopia, Ministry of Health, Ethiopian Public Health Institute (2022). Ethiopia: Food-Based
    Dietary Guidelines–2022. Addis Ababa, Ethiopia.
  • WWW.ENA.ET. Ethiopian news agency official webpage
  • WWW.MOH.GOV.ET. Minister of Health official webpage