ኦሚክሮን ፡ የኮቪድ 19 ሌላኛው ገፅታ

 በዶ/ር ነህሚያ አንዳርጋቸው (በሚሌኒየም የኮቪድ ህክምና ማዕከል ጠቅላላ ሀኪም)

የኮቪድ 19 ወረርሺኝ የአለም ህዝብን ያሸበረበትን የፈረንጆቹ 2020 እና 2021 አልፎ በአሁኑ ሰአት ከሞላ ጎደል የተለመደ ‘አስደንጋጭ’ ዜና ለመሆን በቅቷል። በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ውስጥ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችም ለወረርሺኙ የሚሰጡት ትኩረት እና ክብደት እየለዘበ ይገኛል። በተቃራኒው የዓለም የጤና ድርጅት እንዲሁም የጤና ሚንስትሮች ወረርሺኙ አሁንም አሳሳቢ መሆኑን ለማስረጽ አድማጭ ባገኙበት ቦታ ሁሉ ውትወታቸውን ተያይዘውታል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ከወረርሺኙ እኩል የተዛመቱት የክትባት ሴራ ትንተናዎች እንዲሁም የተሳሳቱ/ያልተሟሉ ግንዛቤዎች ከኮቪድ 19 ነባራዊ ድባብ መገለጫዎች ውስጥ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

እነዚህ እና መሰል ሃሳቦችን አብላልተን እና አንጥረን ስንጨርስ ግን ሁላችን የምንጠይቀው አንድ ጥያቄ አለ።

‘ከዛስ?’

ይህን ጥያቄ በተለያዩ ምልከታዎች በኩል ለመመለስ መሞከር እንችላለን። የመጀመሪያው ምልከታ አዳዲስ የቫይረሱ ዝርያዎች (ከዚህ በኋላ የሚመጡትንም ጨምሮ) ለወረርሺኙ የሚሰጡት መልክ ነው። ከእነዚህ አዳዲስ ዝርያዎች ውስጥ ተጠቃሹ የኦሚክሮን ዝርያ እንደምሳሌ እናንሳ።

ኦሚክሮን

ኦሚክሮን ተብሎ የሚጠራው አዲሱ የኮቪድ 19 ዝርያ በጥቅምት ወር መጨረሻ በዓለም የጤና ድርጅት ‘አሳሳቢ ዝርያ’ ተብሎ ተፈርጇል። ለዚህም የበቃው በተለመዱት የዝርያ መፈረጃ መስፈርቶች ነው። በተለይም ደግሞ የኦሚክሮን ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ከፍተኛ አቅም ለአሳሳቢነቱ ዋናው ምክንያት ነው። በሃገራችንም ተከስቶ የነበረው (በዳቦ ስሙ ‘የሰሞኑ ጉንፋን‘) ምናልባትም ኦሚክሮን እንደሚሆን፤ ከሆነም ደግሞ ለኦሚክሮን እጅግ ከፍተኛ የመዛመት አቅም ዋቢ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል። ደግነቱ ኦሚክሮን የሚያሳያቸው የህመም ምልክቶች ከቀደሙት ዝርያዎች አንጻር ለስለስ ያለ መሆኑ ነው። ለዚህም ጥሩ ማስረጃ የሚሆነው በቫይረሱ ከተያዙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መካከል ወደ ጽኑ ህመም የተሸጋገረባቸው ሰዎች ውድር ዝቅተኛ መሆኑ ነው። ነገር ግን እርግጡ የጽኑ ህሙማን ቁጥር አሁንም ቢሆን ለሃገራች የጤና ዘርፍ ፈታኝ ሆኖ ቀጥሏል። 

ኦሚክሮን የመጨረሻው ዝርያ አይደም። ከዚህም በኋላ ተጨማሪ አይነቶች መምጣታቸው አይቀርም። ቫይረሶች ሲለዋወጡ በተለምዶ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ አቅማቸውን እየጨመሩ፣ በአንጻራዊነት ገዳይነታቸውን እየቀነሱ ይመጣሉ (ይቀንሳል ማለት ለሞት አይዳርግም ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል)። ኮቪድም ይሄንን መስመር ይዞ ከቀጠለ ችግይ የሚፈጥረው ብዙ ሰዎችን በተመሳሳይ ሰዓት ለህመም በመዳረግ የህክምና ስርዓቱን በማናጋት ነው። የጤና ማእከሎች ከአቅማቸው በላይ ታካሚ ለማስተናገድ በሚገደዱበት ጊዜ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር አብሮ መጨመሩ አይቀሬ ነው። ስለዚህም በቀጣይነት ይህን ክስተት ለመግታት ቁልፍ ሚና የሚጫወቱት የመከላያ መንገዶች እና ክትባት ይሆናሉ ማለት ነው። በዚህ ሃሳብ ላይም ተንተርሰን ወደ ሁለተኛው ምልከታ፤ ማለትም የኮቪድ 19 ክትባቶች በቀጣይነት የሚኖራቸው ሚና እንዲሁም ገደብ ዙሪያ ጥቂት እንበል።

 

ክትባት፤ ሚና እና ገደብ

 

የኮቪድ 19 ክትባት ግኝት የወረርሺኙን ሂደት የቀየረ ወሳኝ አንቀጽ ነበረ። ከክትባቱ ግኝት እና ስርጭት ወዲህ ኮቪድ 19 ያመጣውን ምስቅልቅል ለመቀልበስ አመቺ ሁኔታ ተፈጥሯል። ምንም እንኳን ስለክትባቱ የተሰጡት በርካታ አስተያየቶች ለክትባቱ ስርጭት ተግዳሮት ሆነው ቢገኙም የህክምና ባለሙያዎች አሁንም ቢሆን ክትባቱን እንደ ዋነኛ የመከላከያ መሳሪያ እንድንቀም ይመክራሉ። ይህንንም ሲመክሩ ከሚከተሉት ማስታሻዎች ጋር ነው፤

  1. ክትባቱ የኮቪድ 19 ህመምን እንድንቋቋም የተሻለ አቅም እንደሚሰጠን
  2. ክትባቱ በጊዜ ሂደት የሚሰጠን የመከላከል አቅም እየቀነሰ እንደሚመጣ
  3. ክትባቱ የሚሰጠን የመከላከል አቅም በአዳዲስ አይነቶች አውድ አንጻር የተገደበ ሊሆን እንደሚችል
  4. ግራም ነፈሰ ቀኝ  የተከተበ ሰው ካልተከተበ ሰው አንጻር የመከላከል አቅሙ የተሻለ እንደሚሆን እሙን ነው

እነዚህን ማስታወሻዎች ይዘን ወደፊት ስንቀጥል ከእኛ ጋር ሊቀር የሚገባው ሃሳብ አሁንም ሆነ በቀጣይነት ክትባቱ ለጤንነታችን እንዲሁም አጠቃላይ ደህንነታችን ያለውን ትልቅ ዋጋ ነው። ያልተከተብን በመከተብ፣ የተከተብን ደግሞ ለክትባቱ ጥቅም እና ህንነት አምባሳደር በመሆን የበኩላችንን ግዴታ መወጣት ይኖርብናል።

 

ይህ ሁሉ ተብሎ ካለቀ ኋላም ግን ‘ከዛስ’ የሚለው ጥያቄ አሁንም ሊነሳ ይችላል። በታሪክ አለም አቀፍ ወረርሺኞች ሁልጊዜም በሚባል ደረጃ ወደ ውስን ወረርሺኞች ሲለወጡ እና ከአሰቃቂ ህመም መለስ ብለው ወደ ተራ ህመም ደረጃ በጊዜ ሂደት ይሸጋገራሉ። ካለው ማስረጃም አንጻር የኮቪድ 19 መንገድ ከዚህ የተለየ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። ጥያቄው ‘መቼ??የሚለው ነው። 

 

ቸር እንሰንብት!