ሩማቲክ የልብ በሽታ

ሩማቲክ የልብ በሽታ (Rheumatic heart disease) የሩማቲክ ትኩሳት (rheumatic fever) በተደጋጋሚ በመከሰቱ ምክንያት የሚመጣ በልብ ዉስጥ ያለ የደም ፍሰትን የሚቆጣጠሩ የልብ በሮች(heart valves) ስር የሰደደ ጉዳት ነዉ።

 

የሩማቲክ የልብ በሽታ መነሻ የቶንሲል በሽታ መሆኑን ያዉቃሉ ?

ይህ በሽታ ስትሬፕቶኮከስ ፓዮጂንስ (streptococcus pyogenes) በሚባል የባክቴሪያ ኢንፌክሽን በሚከሰት የቶንሲል በሽታ እና የጉሮሮ መቁሰል (tonsillopharyngitis) ይጀምራል። ይህ ኢንፌክሽን ከተከሰተ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሰዉነታችን ይህንን ኢንፌክሽን ለመከላከል አምርቶ የላካቸዉ ፀረ እንግዳ አካላት (antibodies) የልብ በሮችን ጨምሮ ሌሎች የሰዉነት ክፍሎችን በማጥቃት ባጠቋቸዉ የሰዉነት ክፍሎች ልክ የተለያዩ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራሉ። ይህ የሩማቲክ ትኩሳት (rheumatic fever) በመባል ይታወቃል። የሩማቲክ ትኩሳት በመደጋገሙ ምክንያት የሚከሰት የልብ በሮች መቆጣት እና ጠባሳ (inflammation and scarring of the heart valves) ደግሞ ሩማቲክ የልብ በሽታ (rheumatic heart disease) ይባላል።

 

የሩማቲክ ትኩሳት በአብዛኛዉ እድሜያቸዉ ከ 5 እስከ 15 በሆናቸዉ ሕጻናት እና ታዳጊዎች ላይ በይበልጥ ይታያል። ሩማቲክ የልብ በሽታ ደግሞ የሩማቲክ ትኩሳት ከተከሰተ ከ 10 እስከ 20 ዓመታት በኋላ የሚመጣ በመሆኑ ከ 25 እስከ 40 ዓመት የእድሜ ክልል ዉስጥ በሆኑ ሰዎች ላይ በአብዛኛዉ ይታያል፤ ይህ እንዳለ ሆኖ ሩማቲክ የልብ በሽታ የሩማቲክ ትኩሳት በአብዛኛዉ በሚከሰትባቸዉ እና ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሩማቲክ የልብ በሽታ ከፍተኛ ተጋላጭነት ባላቸዉ ሀገራት (high risk population) ላይ ሕጻናትን ጨምሮ ከተጠቀሰዉ የእድሜ ክልል በታች በሆኑ ሰዎች ላይ ሊከሰት ይችላል።

 

“በዚህ ሕመም ምክንያት በየአመቱ 288,348 የሰዉ ሕይወት ያልፋል፤ አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸዉ ሀገራት ከዚህ ቁጥር አብዛኛዉን ድርሻ ይይዛሉ።” የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)

 

አጋላጭ ሁኔታዎች

  • የመኖሪያ ክፍል መታፈን፡- የዚህ በሽታ ዋና መንስኤ የሆነዉ የጉሮሮ ኢንፌክሽን የሚተላለፈዉ ልክ እንደ ጉንፋን በትንፋሽ በመሆኑ መስኮት የሌለዉ የቤት ክፍል(መስኮትም ኖሮ በላስቲክ የታሸገ ሲሆን)፣ በአንድ ክፍል ዉስጥ ብዙ ሆኖ መኖር እና የመሳሰሉት የመኖሪያ ክፍል መታፈንን የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ኢንፌክሽኑ ከሰዉ ወደ ሰዉ በቀላሉ እንዲተላለፍ በማገዝ ለበሽታው ያለንን ተጋላጭነት ይጨምራሉ።
  • ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ፡- አነስተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ይህን በሽታ ለሚያጋልጡ ሁኔታዎች መነሻ በመሆን በሽታዉ የሚከሰትበትን እድል ያሰፋል፤ ለምሳሌ በድህነት ምክንያት በአንድ ክፍል ዉስጥ በብዛት መኖር (የመኖሪያ ክፍል መታፈንን በማምጣት)፣ ሕመም ሲኖር ወጪዉን በመፍራት ወደ ጤና ተቋም አለመሄድ (የጉሮሮ ኢንፌክሽኑ ሳይታከም እንዲቆይ በማድረግ) የሩማቲክ ትኩሳት ብሎም ሩማቲክ የልብ በሽታ የመከሰት እድሉን ያሰፋሉ። ለዚህ ነዉ በዚህ በሽታ ምክንያት ከሚሞቱ ሰዎች ዉስጥ አብዛኞቹ መካከለኛ እና አነስተኛ ገቢ ካላቸዉ ሀገራት ዉስጥ የሆኑት።
  • የሕክምና አገልግሎት እጥረት፡- ኢንፌክሽኑ በተገቢዉ ሁኔታና ጊዜ እንዳይታከም በማድረግ የአጋላጭነት ሚናን ይጫወታል።

 

ምልክቶቹ ምንድን ናቸዉ?

የጉሮሮ ኢንፌክሽን በተከሰተ በሁለተኛዉ ሳምንት የሩማቲክ ትኩሳት የያዘዉ ሰዉ የሚከተሉትን ምልክቶች ያሳያል፡:

  • ትኩሳት
  • ከአንድ መገጣጠሚያ ወደ ሌላ የሚሸጋገር የመገጣጠሚያ ሕመም(migratory polyarthritis)
  • ለመቆጣጠር የሚያስቸግር የሰዉነት አካላት መንቀጥቀጥ (Chorea)
  • ሕመም የለሽ የቆዳ ስር እብጠት (Subcutaneous nodule)
  • ክብ ቅርጽ ያላቸዉ ቀያይ ሽፍታዎች (‘ፍ’ ይጠብቃል)፤ በአብዛኛዉ በደረት ላይ የሚከሰቱ ሲሆን ከፊት ዉጭ ሌሎች ኣካላት
    ላይም ሊከሰቱ ይችላሉ (Erythema marginatum)

 

የልብ በር ስርየሰደደ ጉዳትሲያጋጥመዉ (ሩማቲክ የልብ በሽታ ሲከሰት) የምናያቸዉ ምልክቶች ደግሞ፡

  • የደረት ሕመም
  • የትንፋሽ ማጠር
  • ከእግር የሚነሳ የሰዉነት እብጠት
  • ከመጠን በላይ የፈጠነ የልብ ምት ፣ ወዘተ ናቸዉ።

 

እንዴት ሊታከም ይችላል?

በሩማቲክ የልብ በሽታ የሚከሰት የልብ በሮች ጉዳት ቋሚ በመሆኑ ሩማቲክ የልብ በሽታ አንዴ ከተከሰቱ በመድኃኒት መዳን ከማይችሉ በሽታዎች ዉስጥ አንዱ ነዉ፤ ስለዚህ ምንም እንኳን ምልክቶቹን ለመቋቋም እና ሕመምን ለማስታገስ የተለያዩ መድኃኒቶች ቢታዘዙም በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች የተጎዳዉን የልብ በር ለመቀየር ወይም ለማስተካከል የልብ ቀዶ ሕክምና ያስፈልጋችዋል።

 

ይህንን ሕመም እንዴት መከላከል ይቻላል? ከሕብረተሰቡስ ምን ይጠበቃል?

ሩማቲክ የልብ በሽታ የሩማቲክ ትኩሳት ከተከሰተ በኋላ የሚመጣ ስለሆነ የሩማቲክ ትኩሳትን መከላከል ይህንን ሕመም የመከላከል ዋነኛ መንገድ ነዉ። የሩማቲክ ትኩሳትን ለመከላከል ደግሞ በባክቴሪያ ምክንያት የሚመጣዉን የጉሮሮ ኢንፌክሽን በጸረ ባክቴሪያ በመታከም መከላከል ይቻላል። የጉሮሮ ኢንፌክሽኑን ለመከላከል ደግሞ አጋላጭ ሁኔታዎችን ማጥፋት ወይም መቀነስ አስፈላጊ ነዉ፤ በተለይ የመኖሪያ ወይም የሕጻናት መዋያ ክፍል መታፈን እንዳይኖር ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።

 

ለመጀመሪያ ጊዜ በጉሮሮ ኢንፌክሽን የተጠቃ ሰዉ ወይም የሩማቲክ ትኩሳት አጋጥሞት የማያዉቅ ሰዉ የጉሮሮ መቁሰል፣ የመዋጥ ችግር፣ ትኩሳት እና የመሳሰሉት የጉሮሮ ኢንፌክሽን/ቶንሲል ምልክቶችን በተመለከተ በመጀመሪያዎቹ ስምንት ቀናት ዉስጥ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ተገቢዉን የጸረ ባክቴሪያ ህክምና በማግኘት የሩማቲክ ትኩሳትን መከላከል ይችላል። የሩማቲክ ትኩሳት ያጋጠመዉ ሰዉ ደግሞ ሕመሙ በመደጋገም ወደ ሩማቲክ የልብ በሽታ እንዳያመራ ተጨማሪ የጉሮሮ ኢንፌክሽን/ቶንሲል እንዳይኖር በተገቢዉ የጸረ ባክቴሪያ መድኃኒት ለረጅም ጊዜያት በመታከም ሩማቲክ የልብ በሽታን መከላከል ይችላል። ስለዚህ ሕብረተሰቡ ከላይ የተጠቀሱትን የሩማቲክ ትኩሳት ምልክቶች ሲመለከት ወዲያዉኑ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ተገቢዉን ሕክምና መጀመር ይኖርበታል።

 

እ.አ.አ በ 2017 ጅማ አካባቢ በዶክተር ታደሰ ዱኬሳ መሪነት የተሰራዉ ሩማቲክ የልብ በሽታ ላይ የሚያተኩር ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚያሳየዉ በአካባቢዉ መድኃኒትን ጊዜዉን ጠብቆ የመዉሰድ ባህል በጣም ዝቅተኛ ሲሆን ለበሽታዉ አለመጥፋትና መስፋፋትም ከፍተኛ ሚና አለዉ፤ ስለዚህ ሕብረተሰቡ የታዘዘላቸዉን መድኃኒት በጊዜዉና በተገቢ ሁኔታ በመዉሰድ በሽታዉን በመከላከል ሂደት ዉስጥ የድርሻቸዉን ሊወጡ ይገባል።

በተጨማሪም ለሕክምና አገልግሎት እጥረት፣ ለዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ እና ለመሳሰሉት መሠረታዊ ችግሮች መፍትሄ ማበጀት በበሽታዉ የመያዝ እድልን ይቀንሳል።

 

ዋቢ ማጣቀሻዎች

  1. Behrman RE, Vaughan III VC. Nelson textbook of pediatrics. WB Saunders company; 1983.
  2. World Health Organization. Rheumatic Heart Disease: News room, fact sheets, detail. World Health Organization; 2020 November 6
  3. Gemechu T, Mahmoud H, Parry EH, Phillips DI, Yacoub MH. Community-based prevalence study of rheumatic heart disease in rural Ethiopia. European journal of preventive cardiology. 2017 May 1;24(7):717-23.