ሪህ – GOUT

ሪህ በመገጣጠሚያዎች ላይ ህመም እና እብጠት ሊያስከትል የሚችል የአርትራይተስ(የአንጓብግነት) አይነት ነው። በደማቸው ውስጥ ሥር የሰደደ ከፍተኛ መጠን ያለው ዩሬት (ዩሪክ አሲድ ተብሎም ይጠራል) ባላቸው አንዳንድ ሰዎች ላይ ይከሰታል።ዩሬት በቲሹዎች(የህዋሳት ስብስብ) ውስጥ የሚቀመጡ የዩሬት ክሪስታሎችን(ክምችት) ሊፈጥር ይችላል። ይህ ከፍተኛ ዩሬት ካለባቸው ሰዎች ውስጥ እስከ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት የሕመም ምልክቶችን አያሳዩም ፣ ግን ይህ ለምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም።

መገጣጠሚያዎች በአብዛኛው የሚጎዱት የሰውነት ክፍሎች ቢሆኑም ተያያዥነት ያላቸው የዩሪክ አሲድ ክሪስታሎች በኩላሊት እና በሌሎች የሽንት ቱቦ ክፍሎች ውስጥ ሊፈጠሩ ይችላሉ።

 

ሪህ አብዛኛውን ጊዜ በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚመጣ ሲሆን በልጆች ላይ እምብዛም አይከሰትም። ብዙውን ጊዜ አዋቂ ወንዶች (በአብዛኛው ከ30 እስከ 45 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ) ከሴቶች ይልቅ (ብዙውን ጊዜ ከ55 ዓመት በላይ የሆኑ) በበሽታው ይጠቃሉ። ይሁን እንጂ ጾታቸው ወንድም ይሁን ሴት ከ65 በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ በሽታው ይበልጥ የተለመደ ነው።

 

ለሪህ አጋላጭ የሆኑ ምክንያቶች

ምንም እንኳን የጄኔቲክስ ምክንያቶች (የሴረም ዩሬት መጠን ውርስ 63% ሆኖ ይገመታል) ከከፍተኛ የደም የዩሬት መጠን ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ቢሆኑም ሌሎች የጤና ሁኔታዎች እና የአኗኗር ዘይቤዎች ለአብዛኛው የሪህ በሽታ ምክንያቶች ናቸው።

እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡

  • ከመጠን ያለፈ ውፍረት
  • ከፍተኛ የደም ግፊት
  • ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ
  • ረዘም ላለ ጊዜ መጾም ወይም ከመጠን በላይ መብላት
  • ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥ
  • ከፍተኛ የፕሮቲን (ገንቢ ምግብ) መጠን ያላቸውን ምግቦች (ስጋ፣ የባህር ምግቦችን) አብዝቶ መመገብ።

የዩሬትን የደም መጠንን ከፍ የሚያደርጉ መድኃኒቶችን መውሰድ (በተለይም የሚያሸኑ(ዳዩሬቲክስ) መድኃኒቶች) ቀደም ሲል ሪህ ያለባቸው ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ የሪህ በሽታ እንዲያገረሽ የሚያደርጉ አንዳንድ ምክንያቶች አሉ። እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ:

  • ጉዳት ወይም የቅርብ ጊዜ ቀዶ ጥገና
  • ውሃአነስነት(ዲሀይድሬይሽን)
  • መጾም ወይም ከመጠን በላይ መብላት
  • ከመጠን በላይ አልኮል መውሰድ
  • የዩሬትን የደም መጠን የሚጨምሩ መድኃኒቶችን መውሰድ

 

የሪህ በሽታ ምልክቶች

  • ድንገተኛ እና ከባድ የመገጣጠሚያ ህመም፣ መቅላት እና እብጠት
    • ምንም እንኳን የሪህ እብጠት በአብዘሃኛው አንድን መገጣጠሚያ(በተለይ አውራ ጣት) የሚጎዳ ቢሆንም አንዳንድ ሰዎች ላይ በተመሳሳይ ጊዜ ከአንድ በላይ መገጣጠሚያዎችን ሊያጠቃ ይችላል። የሪህ እብጠቶች በአብዘሃኛው ከቀን ይልቅ በሌሊት እና በማለዳ ሰአታት (ከእንቅልፍ
      ስንነሳ) ይከሰታሉ። ህመሙ እና እብጠቱ ብዙውን ጊዜ ከጅማሬው አንስቶ ከ12 እስከ 24 ሰአታት ውስጥ ከፍተኛ የህመም ጥንካሬ ላይ ይደርሳል።ከዚያም በኋላ ህክምና እንኳን ባይደረግ ከጥቂት ቀናት እስከ ሳምንታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ህመሙ ይሻሻላል።
  • ትኩሳት እና ብርድ ብርድ ማለት
  • የዩሬት ክሪስታሎች ከመገጣጠሚያ ውጭ ከቆዳ ስር ተሰብስበው ሊታዩ ይችላሉ ። እነዚህም ቶፊ(Tophi) ይባላሉ።ይህም የሚሆነው ከፍተኛ መጠን ያለው ዩሬት ያለባቸው እና በተደጋጋሚ በሽታው ያገረሸባቸው ሰዎች ላይ ነው። በአብዛኛውም ከጣቶች ጫፍ በላይ፣ ከተረከዝ ጀርባ፣ከጉልበት ፊት ለፊት፣ ከጣቶች እና ከእጅ አንጓዎች ጀርባ ፣በክርን ዙሪያ እና በጆሮዎች ላይ ይከሰታሉ። ብዙውን ጊዜ ግን ህመም አያስከትሉም። ግን በተለመደው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ እክል ሊይስከትሉ ይችላሉ።

 

 

የሪህ በሽታ ውስብስብ ውጤቶች

  • ሪህ ያለባቸው ሰዎች ለኩላሊት ጠጠር የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ ነው። ይህ በኩላሊት ወይም በሌሎች የሽንት ቱቦዎች ውስጥ የዩሪክ አሲድ ክሪስታሎች ከተፈጠሩ ሊከሰት ይችላል. ይህም የተለመደውን የኩላሊት ጠጠር ምልክት የሆነውን የጀርባው ጎን (“የጎን ህመም”) ህመምን ያስከትላል።
  • የደም ቧንቧ መጥበብ – ለስትሮክ ፣የልብ ድካም ወይም ለሌሎች የልብ ችግሮች የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።
  • የአጥንት መልፈስፈስ(Osteomalacia)
  • ለአንዳንድ ነቀርሳዎች በተለይም ለፕሮስቴት ካንሰር የመጋለጥ እድልን ይጨምራል
  • ለመንፈስ ጭንቀት ያጋልጣል።
  • ለኢንፌክሽን የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።
  • በወንዶች ላይ ስንፈተ-ወሲብን ሊይስከትል ይችላል።

 

የሪህ ምርመራ (ዲያግኖሲስ)

የመገጣጠሚያ ህመም እና እብጠት ሊያስከትሉ የሚችሉ ብዙ በሽታዎች አሉ። ጎጂ ሊሆኑ የሚችሉ መድሃኒቶች ለረጅም ጊዜ ሳያስፈልግ እንዳይወሰዱ ለማረጋገጥ የሪህ ምርመራን ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ሪህ ለመመርመር በጣም ጥሩው መንገድ ሐኪሙ የዩሬት ክሪስታሎችን ለመፈለግ በአጉሊ መነጽር
የተጎዳውን መገጣጠሚያ ውስጥ ያለውን ፈሳሽ(ሲኖቪያል ፈሳሽ) መመርመር ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ በመገጣጠሚያው ውስጥ ትንሽ ፈሳሽ ለማውጣት መርፌ ይጠቀማል. ከቆዳ ስር ከሚገኘው ቶፊ ላይም ሪህ በሽታን ለመመርመር በመርፌ ናሙና ሊወሰድ ይችላል።

የሲኖቪያል ፈሳሽ ትንተና ማድረግ የማይቻል ከሆነ, ዶክተሩ በምልክቶችዎ, በአካላዊ ምርመራ እና በደም ምርመራዎች ላይ በመመርኮዝ የሪህ በሽታን በጊዜያዊነት ምርመራ ሊያደርግ ይችላል። ሪህን ለመጠራጠር ከሚያስፈልጉት ክሊኒካዊ መመዘኛዎች መካከል፡-

  • ከፍተኛ የሆነ የመገጣጠሚያ ህመም እና እብጠት በተለይም በትልቁ የእግር ጣት ስር ያለውን መገጣጠሚያ የሚያጠቃ።
  • በሁለት ተከታታይ የሪህ በሽታ ጥቃቶች (Episodes) መካከል ሙሉበሙሉ ከምልክቶች ነጻ መሆን
  • በደም ምርመራ ከፍተኛ መጠን ያለው ዩሬት መገኘት

 

ሪህ እንዴት ይታከማል?

  • በሪህ የሚመጣውን ህመም እና እብጠት የሚቀንሱ መድሃኒቶች አሉ።የሪህ መድሃኒቶች ምልክቶቹ እንደጀመሩ ወዲያውኑ ከተወሰዱ በተሻለ ሁኔታ ይሰራሉ።
  • NSAIDs (ህመም ማስታገሻ) – ይህ አይቡፕሮፊን (Ibuprofen) [ናሙና ብራንድ ስሞች: አድቪል, ሞትሪን] እና ኢንዶሜታሲን (Indomethacin) [ብራንድ ስም: ኢንዶሲን] የሚያካትቱ መድኃኒቶች ቡድን ነው. NSAIDs የኩላሊት ወይም የጉበት በሽታ ላለባቸው ሰዎች ወይም የደም መፍሰስ ችግር ላለባቸው ሰዎች ደህና ላይሆን ይችላል።
  • ኮልቺሲን – ይህ መድሃኒት ለሪህ ይረዳል ነገር ግን አንዳንዴ ተቅማጥ፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እና የሆድ ህመም ሊያስከትል ይችላል ።
  • ስቴሮይድ – ስቴሮይድ እብጠትን እና ህመምን ይቀንሳል፡፡

 

የረጅም ጊዜ ህክምና

  • አመጋገብን ማስተካከል
  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማዘውተር
  • የዩሬትን መጠን የሚቀንሱ መድሃኒቶችን (አሎፑሪኖል፣ፕሮቤኒሲድ) በጤና ባለሙያ ትእዛዝ መሰረት መጠቀም

 

የማጣቀሻ ምንጮች

  •  https://www.uptodate.com/contents/gout-beyond-thebasics?search=gout&source=search_result&selectedTitle=3~150&usage_type=default& display_rank=3
  • https://emedicine.medscape.com/article/329958-overview?icd=ssl_login_mismatch_gg_221125
  • https://www.versusarthritis.org/about-arthritis/conditions/gout/
  • https://next.amboss.com/us/article/YT0n62?q=gout#Z37ad7ac85fa0ad7afcffc8647f8ea
    9c6