ሪዩማቲክ የልብ በሽታ

ሪዩማቲክ የልብ በሽታ

በአፎሚያ ሰይፈ () የተዘጋጀ

 

ሪዩማቲክ የልብ በሽታ በልብ ውስጥ ደምን ከአንዱ ክፍል ወደሌላው ለማሳለፍ የሚረዱ የልብ በሮች/ቫልቮችን የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በሽታው የሚጀምረው እድሜያቸው ከ 5 እስከ 15 አመት ያሉ ታዳጊዎች ላይ ነው።

ይህ በሽታ ባደጉት ሃገራት በመጥፋት ላይ ያለ ቢሆንም እንደሃገራችን ባሉ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት ግን ከልብ በሽታዎች መሃል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። Pan African Society of Cardiology(PASCAR) ባወጣው ጥናት መሰረት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2017 በኢትዮጵያ ከነበሩት አጠቃላይ የልብ በሽታዎች ትልቁን ድርሻ የያዘው (33.7%) የሪዩማቲክ የልብ በሽታ ነበር።

 

የጤናማ ልብ አሰራር

ልብ በጡንቻዎች የተገነባ በሰውነታችን ያሉ ደምስሮች ሁሉ መነሻ እና መድረሻ የሆነ አካል ነው። ስራውም እንደሚከተለው በአጭሩ ሊጠቃለል ይችላል።

  • በቅድሚያ ከመላው ሰውነታችን የሚመጣውን ካርቦንዳይኦክሳይድ ያዘለ ደም በቀኝ በኩል ያለው የልብ ጎን ይቀበላል።
  • በመቀጠልም ይህን ደም ወደሳንባ ይረጫል።
  • ሳንባም ካርቦንዳይኦክሳይድን በኦክሲጅን ይቀይራል።
  • በግራ በኩል ያለው የልብ ጎንም የታደሰውን ኦክሲጅን ያዘለ ደም ከሳንባ በመቀበል መልሶ ወደሰውነት ይረጫል።

 

ልብ ይህንን ስራ በአግባቡ እንዲከውን የሚያደርጉ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት። እነርሱም

1. ዙሪያቸውን በልብ ጡንቻ ግድግዳነት የተሰሩ አራት ክፍሎች

  • በቀኝ ያሉት ሁለቱ ካርቦንዳይኦክሳይድ ያዘለ ደምን ከሰውነት ተቀብለው በመጭመቅ ወደሳንባ ሚረጩ ሲሆኑ
  • በግራ ያሉት ሁለቱ ደሞ ኦክሲጅን ያዘለ ደምን ከሳንባ ተቀብለው በመጭመቅ ወደ ሰውነት መልሰው የሚረጩ ናቸው።

 

2. የአራቱ ክፍሎች መግቢያ እና መውጫ በሮች/ቫልቮች

  • እነኚህ ደግሞ ደምን ከአንዱ የልብ ክፍል ወደሌላው ተከፍተው ካሳለፉ በኋላ በፍጥነት ይዘጋሉ።
  • ይህም ደም ወደመጣበት ክፍል ተመልሶ እንዳይፈስ በማገድ ወደፊት ብቻ እንዲጓዝ የሚያግዝ ነው።
  • በዚህ ጽሁፍ የምንቃኘው ሪዩማቲክ የልብ በሽታ እነዚን በሮች በማጥቃት የደም ፍሰትን የሚያስተጓጉል እና የልብን ስራ የሚያደናቅፍ በሽታ ነው።

 

 የበሽታው አመጣጥ እና ሂደት  

ሪዩማቲክ የልብ በሽታ የሚመጣው በሚከተሉት ሶስት ደረጃዎች ነው

1. በባክቴሪያ የሚመጣ የጉሮሮ ህመም እና የቶንሲል መቆጣት

  • ባክቴሪያው ግሩፕ ኤ ስትሬፕቶኮከስ(Group A beta-Hemolytic Streptococcus) የሚባል ነው።

 

2. እሱን ለመከላከል ሰውነት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ከባክቴሪያው ጋር መመሳሰል የታየባቸው የሰውነት ህዋሳት አብሮ መጠቃት(ሪዩማቲክ ፊቨር)

  • የባክቴሪያው ፕሮቲኖች ከልብ ውስጥ በሮች/ቫልቮች ጋር የተወሰነ መስተጋብር ያደርጋሉ። በዚህም ምክንያት በልብ ቫልቭ እና በባክቴሪያው ህዋሳት መሃል መመሳሰል ይፈጠራል።
  • ከዛም ባክቴሪያውን ኢላማ ያደረጉ የሰውነት በሽታ ተከላካይ ህዋሳት የገዛ የልብ ቫልቮችን ያጠቃሉ
  • በተመሳሳይ ሁኔታ መገጣጠሚያዎች፣ ቆዳ፣አንጎል እና ጅማት ሊጠቁ ይችላሉ
  • ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ ግን ለረጅም ጊዜ የሚቆይና የከፋ ጉዳት የሚያመጣው የልብ በሽታው ነው።

 

3. በሪዩማቲክ ፊቨር መደጋገም የሚመጣው ሪዩማቲክ የልብ በሽታ

  • በጊዜ ሂደት ጉዳቱ ሲደጋገም የልብ በሮች/ቫልቮች ጠባሳ ይፈጥራሉ። ይህም ከተገቢው በላይ እንዲሰፉ ወይም እንዲጠቡ ምክንያት ይሆናል።
  • ተያይዞም በልብ በሮቹ የሚያልፈው ደም እንደበፊቱ በቀላሉ ለመፍሰስ ይቸገራል።
  • ይህ ጉዳት በጊዜ ሂደት ሲባባስ የልብ ድካም ያመጣል። ማለትም ልብ ሠውነታችን የሚያስፈልገውን ያህል ደም መርጨት የማይችልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል።

                                                  ምስል 2.  የጤናማና የተጎዱ የልብ ቫልቮች ልዩነት                                                     

                                                  

ለሪዩማቲክ የልብ በሽታ የሚያጋልጡ መንስኤዎች

  • ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ
  • በሰው የተጨናነቀ ቤት ውስጥ መኖር
  • ተደጋጋሚ የጉሮሮ ህመም እና የቶንሲል መቆጣት

 

ምልክቶች

የሪዩማቲክ ፊቨር ደረጃ ላይ ሳለ

  • ትኩሳት
  • ተደጋጋሚ የጉሮሮ ህመም
  • የመገጣጠሚያዎች ህመም በተለይ የጉልበት እና የቁርጭምጭሚት
  • ቀያይ የቆዳ ሽፍታዎች በተለይ በደረት ሆድ እና ጀርባ ላይ
  • በመገጣጠሚያዎች አከባቢ የሚወጡ እብጠቶች
  • ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ የሰውነት እንቅስቃሴዎች

የሪዩማቲክ የልብ በሽታ ደረጃ ላይ ሲደርስ

  • በቀላሉ ወይም በትንሽ እንቅስቃሴ የድካም ስሜት መሰማት
  • የደረት ውስጥ ህመም
  • ያለምንም አነሳሽ ምክንያት ፈጣን የልብ ምት መሰማት

እንዲሁም በሽታው ብሶ የልብ ድካም ሲያመጣ

  • የትንፋሽ ማጠር
  • ደረቅ ሳል
  • በትንፋሽ ማጠር ምክንያት ከእንቅልፍ መንቃት
  • የእግር ማበጥ

 

ምርመራዎች

በጤና ባለሞያዎች ማዳመጫ(ስቴትስኮፕ) የሚደረግ ምርመራ

  • ይህ የልብ ትርታን በመስማት ጤናማ እንደሆነ የሚጣራበት ምርመራ ነው።
  • ጤናማ ትርታ የልብ በሮች ሲዘጉ የሚፈጠር ነው።
  • ታዲያ በሮቹ በሚጠቡበት ወይም በሚሰፉበት ጊዜ ለመዘጋት የሚያደርጉት ጥረት የተጨናነቀ ይሆናል።
  • ይህም እንደየብልሽቱ አይነትና እንደተበላሸው በር አይነት የተለያዩ ተጨማሪ ድምጾችን ይፈጥራል።
  • ስለዚህ እነዚህ ተጨማሪ ድምጾች ካሉ የልብ በሮች ጉዳት መኖሩን አመላካች ይሆናሉ።

ኢኮካርዲዮግራም

  • ይህ የአልትራሳውንድ ሞገዶችን በመጠቀም ልብ ያለበትን ይዘት በቀጥታ የሚያሳይ ምርመራ ሲሆን የተጎዱ የልብ ቫልቮችና ከዚህ ጋር ተያይዘው የመጡ ለውጦችን ለማየት ይረዳል። ከለውጦቹም መሃል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።
  • ወደፊት መሄድ ሲኖርበት ወደኋላ የሚመለስ ደም
  • የስራ ጫናው በመጨመሩ ምክንያት የተለቀ ልብ
  • ከተገቢው በላይ የሰፉ ወይም የጠበቡ የልብ ክፍሎች

ኤሌክትሮካርዲዮግራም

  • ይህ ምርመራ ልብ ጊዜውን ጠብቆ እንዲመታ ሚያደርገውን የኤሌክትሪክ ስርጭት ጤናማነት ለማየት የሚረዳ ነው።

የደረት ኤክስ–ሬይ

  • በልብ ውስጥ ደም ፍሰት መዛባት ምክንያት ጫና የበዛበት ሳንባን እና የተለቀ ልብን የሚያሳይ ነው።

የደም ምርመራዎች

  • የልብ ቫልቮችን መጎዳት ተከትሎ የመጣ የልብ ቫልቭ እና የውስጠኛው የልብ ግድግዳ ኢንፌክሽን ካለ ይጠቁሙናል።

 

ህክምና

  • በቅድሚያ በሽታው በሪዩማቲክ ፊቨር ደረጃ እንዳለ በጸረ–ባክቴሪያ መድሃኒት ማከም ይቻላል።ይህ የልብ ቫልቮች ከመጎዳታቸው በፊት ባክቴሪያውን ስለሚያስወግድ የተሻለው አማራጭ ነው።
  • በሽታው ተባብሶ የልብ ድካም ካመጣ የልብን ስራ ሚያግዙ መድሃኒቶች ይሰጣሉ።
  • ነገር ግን የልብ ቫልቮች በከፍተኛ መጠን ከተጎዱ በሰው ሰራሽ ቫልቮች የሚተኩበት የቀዶ ጥገና ህክምና ይደረጋል።

                                                               ምስል 3.  የልብ ቫልቭ መተካት                                                               

 

መከላከያ መንገዶች

ሶስት ዋና ዋና የመከላከያ ደረጃዎች አሉ

አንደኛ

  • አስስቀድሞ ተጋላጭነትን መቀነስ ማለትም
  • ድህነትን መቅረፍ
  • በአንድ ቤት የሚኖሩ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ
  • የተሻለ የጤና ተቋማት ተደራሽነትንና የመድሃኒት አቅርቦትን ማመቻቸት

ሁለተኛ

  • የጉሮሮ ህመም እና የቶንሲል መቆጣትን ሳያከርሙ በጸረ–ባክቴሪያ መታከም
  • ይህ በሽታው ወደ ሪዩማቲክ ፊቨር አድጎ የልብ በሮች መጎዳት ከመጀመራቸው በፊት ማስቆም የሚቻልበት መንገድ ነው።

ሶስተኛ

  • አንዴ የልብ ቫልቮች መጎዳት ከጀመሩ ተደጋጋሚ የሪዩማቲክ ፊቨር ተጨማሪ ጉዳት በማድረስ የከፋ ጠባሳ እንዲፈጥሩ ያደርጋል። ስለዚህ በየወሩ የሚሰጠውን የሪዩማቲክ ፊቨር ድግግሞሽ መከላከያ መርፌ በአግባቡ መወጋት ይገባል።

 

ምንጮች

  1. Dejuma Yadeta, Wubaye Walelgne, Jean M Fourie, Wihan Scholtz, Oana Scarlatescu, George Nel, Mussie Gebremichael. January/February 2021. PASCAR and WHF Cardiovascular Diseases Scorecard project: Ethiopia Country Report. https://www.google.com/url?sa=t&source=web&rct=j&url=http://www.cvja.co.za/onlinejournal/vol32/vol32_issue1/files/assets/common/downloads/page0039.pdf&ved=2ahUKEwigj4zv64z7AhUzQ_EDHbLVCsYQFnoECAwQAQ&usg=AOvVaw1AaPZcdGsynUMd9eZUKkbr
  2. Johns Hopkins Medicine [online] 2022 https://www.google.com/url?sa=t&source=web&rct=j&url=https://www.hopkinsmedicine.org/health/conditions-and-diseases/rheumatic-heart-disease%23:~:text%3DKey%2520points-,Rheumatic%2520heart%2520disease%2520is%2520a%2520condition%2520in%2520which%2520the%2520heart,a%2520person%2520at%2520increased%2520risk.&ved=2ahUKEwiVoNeR7oz7AhW5QPEDHWkRAGUQFnoECAoQBQ&usg=AOvVaw2pyZtp5zbqYLroovkxVVmn
  3. Johns Hopkins Children’s Hospital [online]. 2022. Your Heart & Circulatory System.  https://www.hopkinsallchildrens.org/Patients-Families/Health-Library/HealthDocNew/Your-Heart-Circulatory-System-(1)
  4. The Royal Children’s Hospital Melbourne [online].  Heart problems in children.
  5. https://www.rch.org.au/kidsinfo/fact_sheets/Heart_problems_in_children/
  6. World Health Organization. 12 April 2018. Rheumatic fever and rheumatic heart disease: Report by the Director-General. https://www.google.com/url?sa=t&source=web&rct=j&url=https://apps.who.int/gb/ebwha/pdf_files/WHA71/A71_25-en.pdf&ved=2ahUKEwjX89fH7Yz7AhXBOHoKHQw-BBUQFnoECA4QAQ&usg=AOvVaw2hB6zUByYrp0YVutW7pBlT
  7. World Health Organization [online]. 6 November 2020. Rheumatic Heart Disease.
  8. https://www.google.com/url?sa=t&source=web&rct=j&url=https://www.who.int/news-room/fact-sheets/detail/rheumatic-heart-disease&ved=2ahUKEwjonu3t0pL7AhWVvYsKHdKtAH8QFnoECEwQAQ&usg=AOvVaw2znDd4pW9OVcMmv2p5j4v6