ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች (Neglected tropical diseases)

ዶ/ር ፍስሃ ሙልጌታ -ሚዮንግሳንግ የህክምና ኮሌጅ (Medical Intern)

አርትኦት  እና እርማት – በ ዶ/ር ቸርነት አደራ (Senior Market Access Manager at Drugs for Neglected Diseases Initiative, Nairobi)

 

ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች እጅግ ደሃ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በዋናነት የሚያጠቁት ሲሆን በአለም ላይ ከ1 ቢሊዮን በላይ ሰዎችን ያጠቃሉ፡፡ የአለም ጤና ድርጅት ወደ 20 የሚሆኑ ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች በአለም ዙሪያ እንዳሉ በመለየት እነዚህን በሽታዎች በመቆጣጠር፣ በማስወገድና፣ ጨርሶ በማጥፋት ላይ ያነጣጠረ የ10 አመት ፍኖተ-ካርታ በማዘጋጀት እየሰራ ይገኛል፡፡ በሽታዎቹ የሚከሰቱት በተለያዩ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን (ቫይረሶች፣ ባክቴሪያዎች፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትሎች፣ ፈንገሶች) እና በእባብ ንድፊያ መመረዝን  ያካትታል። እነዚህ በሽታዎች አካላዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያስከትላሉ። ችግሮችም፦ በበሽታው መሰቃየት፣አይነ ስውርነት፣ አካለ-ስንኩልነት፣ የአካል እና የአእምሮ እድገት መዘግየት(ዉስንነት) ብሎም ሞት ያካትታል። በተጨማሪም  በበሽታዎቹ የተጠቁ ግለሰቦች  መገለል እና አድልዎ ይደርስባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ከ70 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ቢያንስ ለአንድ ትኩረት የሚሻ ሃሩራማ በሽታ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ጤና ጥበቃ  በኢትዮጵያ ከሚገኙ ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች መካከል  የሚከተሉትን  ለመቆጣጠር፣ ለማስወገድና፣ ለማጥፋት የ5 አመት ፍኖተ-ካርታ በማዘጋጀት እየሰራ ይገኛል። እነርሱም ትራኮማ፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትሎች፣ ስጋ ደዌ፣ ቢሊሃርዚያ(ሺስቶሶሚያሲስ)፣ ዝሆኔ፣ ፎከት (እከክ) ፣ ጊኒ ዎርም፣ ሌሽማንያሲስ (ካላዛርና ቁንጭር)፣ የእብድ ውሻ በሽታና የዴንጊ በሽታ ናቸው።

ዓለም አቀፉዊ የጤና አጀንዳን  በምንመለከትበት ጊዜ ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች ከሌሎች ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች አንፃር  የተሰጣቸው ትኩረት በጣም ውስን ነው። ይህ ውስን ትኩረትም የችግሩ ተጠቂ በሆኑ ሃገራት መንግስታት እና በአለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ይስተዋላል ።   ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች አብዛኛውን ጊዜ በድሃ ሀገሮች እና ማህበረሰቦች ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች  በዋነኝነት የሚገኙት  በገጠር፣ በግጭት ቀጣና ፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁና ተፋፍገው በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ፣ እና ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ  አካባቢዎች ነው። በቂ እና ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የግል ንፅህና አጠባበቅ ጉድለት እና የአካባቢ ጽዳት እጥረት ባለባቸው አካባቢዎችም ይገኛሉ። በአየር ንብረት ለውጥም ይባባሳሉ። በተጨማሪም፣ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ውስንነት ባለባቸው  አካባቢዎች ላይ የበለጠ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፣ ፤ እንዲሁም በሽታዎቹን አስተላላፊ የሆኑ ነፍሳቶች ባሉበት አካባቢ በስፋት ሊከሰቱ ይችላሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ  በሽታዎች ላይ ጣልቃ ገብቶ ከዓለም አቀፍ እስከ ማህበረሰብ ደረጃ በማቀድ፣ ፋይናንስ፣ ትግበራ፣ ክትትል እና ግምገማን ለመደገፍ አጠቃላይ የሆነ መደበኛ መመሪያ በማዘጋጀት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እየደገፈ ይገኛል።

በማህበረሰቡ ውስጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደ በጅምላ የሚሰጥ መድሃኒት ወይም ቀላል የውሃ ማጣሪያ  ያሉ አማራጮችን በመጠቀም እንዲሁም የግልና የአካባቢን ንፅህና በመጠበቅ በርካታ  ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች  መቆጣጠር ወይም ማስወገድ ይቻላል።

የዓለም ጤና ድርጅት ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎችን ለማጥፋት አምስት ዋና ስልቶች ይመክራል።

  • አዳዲስ እና የተጠናከረ የበሽታ መቆጣጠሪያ ፣
  • የመከላከያ መድሀኒት ፣
  • የበሽታ አስተላላፊ ትንኞች ቁጥጥር,
  • የእንስሳት ህክምና እና
  • የንጹህ ውሃ አቅርቦት, የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና አጠባበቅ

ጥር 22 (January 30th) ቀን በየአመቱ  አለም አቀፍ ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች መታሰቢያ ቀን በመባል ኢትዮጵያን ጨምሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል። ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎችን ለመቆጣጠር፣ ለማስወገድና፣ ለማጥፋት የሁሉንም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከፍተኛ ርብርብ ይጠይቃል።

 

Source

  1. https://www.cdc.gov/globalhealth/ntd/
  2. https://www.who.int/news-room/questions-and-answers/item/neglected-tropical-diseases
  3. Ending the neglect to attain the Sustainable Development Goals: a road map for neglected tropical diseases 2021–2030. Geneva: World Health Organization; 2020. Licence: CC BY-NC-SA 3.0 IGO.
  4. The Third National Neglected Tropical Diseases Strategic Plan 2021-2025 (2013/14 – 2017/18 E.C.), Ministry of Health, Ethiopia.