አካል ጉዳተኞችን አካታች የሆነ የስነተዋልዶ ጤና

በዓለም ዙሪያ ከ1 ቢሊዮን በላይ ሰዎች (የዓለም 15% የሚሆነው ሕዝብ) ከአንድ ወይም ከዚያ በላይ የአካል ጉዳት አይነት ጋር ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። ይህ ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ ሳለ የብዙ አካል ጉዳተኞች ስለ ጾታዊ ግንኙነት እና ስነ ተዋልዶ ጤናቸው ያሏቸው መብቶች ፣ ምኞቶች እና ስጋቶች በአሳዳጊዎቻቸው፣ በቤተሰብ አባላት፣ በማህበረሰቡ እና በጤና አገልግሎት አቅራቢዎች ችላ ይባላሉ።

አንድ ሰው ሙሉ ጤነኛ ነው ስንል አካላዊ፣ አእምሯዊ እና ማኅበራዊ ጤንነቱን እያረጋገጥን እንደመሆኑ የስነተዋልዶ ጤና ስንልም አንድ ሰው ጾታን አስመልክቶ ያለውን አካላዊ፣ አእምሯዊ እና ማኅበራዊ ጤንነት ያመለክታል፡፡ የስነተዋልዶ ጤና የጾታ ግንኙነትን፣ መራባትን፣ የጾታ ማንነትንና ሚናን የሚያካትት ጉዳይ ነው፡፡ ከዛም ባለፈ ለፆታ እና ለጾታዊ ግንኙነት በጎ እና ክብር የተላበሰ አመለካከት መያዝን እንደዚሁም ከግዴታ፣ ከአድልዎ፣ ከኃይል ነጻ በሆነ መንገድ አስደሳችና ያለፍርሃት የሚደረግ ጾታ ግንኙነትን ያመለክታል፡፡ እነዚህ መብቶች ስነተዋልዶ ጤናን አስመልክቶ ሀገራት በየራሳቸው ባወጧቸው ሕጎች ላይ የሰፈሩትን ብቻ ሳይሆን በዓለምአቀፍ ደረጃ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ያሏቸውን መብቶች በማስመልከት የወጡ ድንጋጌዎችና ሰምምነቶችንም ያጠቃልላሉ።

 

የግንዛቤ ማነስ እና የተዛቡ አመለካከቶች

እነዚህን መብቶቻቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዳይችሉ ከሚከላክሏቸው ተግዳሮቶች መካከል ከስነተዋልዶ ጤና ጋር በተያያዘ ማህበረሰቡ ስለአካል ጉዳተኞች ያሉት የተሳሳቱ አመለካከቶች ዋነኞቹ ናቸው። ከሰማኋቸው ውስጥ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡

  • አካል ጉዳተኞች ለጾታ ግንኙነት ስሜቱም ፍላጎቱም የላቸውም።
  • አካል ጉዳተኞች የጾታ ግንኙነት መፈጸም አይችሉም።
  • አካል ጉዳተኛ ሴቶች ድንግሎች ስለሆኑ ከነሱ ጋር ወሲብ መፈጸም ለኤችአይቪ/ኤድስና ለአባለዘር በሽታዎች አያጋልጥም።
  • አካል ጉዳተኞች የፍቅር እና የጾታ ግንኙነት የሚኖራቸው እርስ በርሳቸው ብቻ ነው።
  • አካል ጉዳተኞች መጸነስና ልጅ መውለድ አይችሉም።
  • አካል ጉዳተኞች ካረገዙ ከፍተኛ የእርግዝናና የወሊድ መወሳሰብ ስለሚያጋጥማቸው ከወሲብ መቆጠብ አለባቸው።
  • ከአካል ጉዳተኛ የሚወለድ ልጅ አካል ጉዳተኛ ይሆናል።
  • አካል ጉዳተኞች የወሲብ ስሜታቸው ቀዝቃዛ ነው።
  • አካል ጉዳተኞች የወሲብ ስሜታቸው በጣም ከፍተኛ ነው የሚሉ እና የመሳሰሉት የተሳሳቱ አመለካከቶች የአካል ጉዳተኞችን ሰብዓዊ መብቶች ከመጋፋት ባለፈ ለፆታዊ ጥቃትም ተጋላጭ ያደርጓቸዋል።

 

በተጨማሪም ፣

  • የጤና አገልግሎት ፖሊሲ አውጭዎችና ፕሮግራም ነዳፊዎች ስለአካል ጉዳተኞች ያላቸው ግንዛቤ አናሳ መሆን
  • የጤና ባለሙያዎች እና ሐኪሞች ግንዛቤ/ስልጠና ማነስ
  • የአገልግሎት ሰጪዎች የተሳሳቱ የግል አመለካከቶችና አቋሞች (ለምሳሌ፡ ወሲብ እንኳ ላንቺ አይጠቅምም፣ አያምርብሽምም፣
    ትጎጃለሽ፣ ወዘተ.)
  • የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተደራሽ አለመሆን (ወደ ሕንጻዎች እና ቢሮ መግቢያ ምቹ መተላለፊያዎች (Ramps)
    አለመኖር፣ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ አለመኖር፣ የሚለጠፉ ጠቃሚ የጤና መረጃዎችና አቅጣጫ ጠቋሚዎች ማየት
    ለተሳናቸው አለመዘጋጀት፣ ወዘተ.)
  • አገልግሎት አቅራቢዎችን የሚገዙ አስገዳጅ ሕጎችና መመሪያዎች አለመኖር
  • የአቤቱታ ማቅረቢያ ስርዓትና ተጠያቂነት አለመኖር
  • በዋነኝነት ደግሞ አካል ጉዳተኞች የስነተዋልዶ መብቶች ያሏቸው መሆኑን አለመገንዘባቸውና አለመጠየቃቸው ትልቅ
    እንቅፋቶች ናቸዉ።

 

የሥርዓተ-ጾታ ሚናዎች እና አካል ጉዳተኝነት

በሌላ በኩል ደግሞ የሥርዓተ-ጾታ ሚናዎች አካል ጉዳተኝነት ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተጽዕኖ መረዳት ተገቢ ነው። እነዚህ ሚናዎች እየጎሉና ቅርጽ እየያዙ የሚመጡት በጉርምስና እድሜ ላይ ሲሆን በአብዛኛው ማኅበረሰብ ውስጥ የወንዶች ሚና እየሰፋ፣ የሴቶች ደግሞ እየጠበበ የሚሄድበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በሴት ወጣቶች ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር እንደዚሁም በስነተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ ምርጫዎቻቸውንና መብቶቻቸውን የሚጋፋ ይሆናል፡፡

ሴት አካል ጉዳተኛ ወጣቶች ጉዳት ከሌለባቸው ወጣት ሴቶችና ወንድ አካል ጉዳተኞች የባሰ ምርጫዎቻቸውና መብቶቻቸው የሚጠብቡ ስለሆነ የተደራረበ የጾታ መድልዎ እና መገለል ያጋጥማቸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴት አካል ጉዳተኞች ቁጥር ከወንድ አካል ጉዳተኞች ይበልጣል፡፡ ነገር ግን ሴት አካል ጉዳተኞች በትምህርት፣ በሥራ ዕድልና በመሳሰሉት ያላቸው ተሳትፎ ከወንድ አካል ጉዳተኞች በጣም ያነሰ ነው፡፡ የሥርዓተ-ጾታ ሚና ለዚህ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

 

መፍትሄዎቹስ?

አካል ጉዳተኞችን አካታች የሆነ የስነ-ተዋልዶ ጤና ዘርፍን እንዴት መፍጠርና ማስቀጠል እንችላለን?

 

  • መብት-ተኮር መርሆችን ተጠቅሞ ስለአካል ጉዳተኞችና አለማቀፋዊ ስለሆኑ የስነ-ተዋልዶ ጤና መብቶቻቸው በስነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በማህበረሰቡና ራሳቸው አካል ጉዳተኞች ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር
  • ፖሊሲ አውጪዎችን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላትን በመሰብሰብ ስለጉዳዩ ያላቸውን ዕይታ ማጋራት የሚችሉበትን ነፃ የውይይት መድረኮችን መፍጠርና ማሳተፍ
  • ስልጠናዎች ላይ አካል ጉዳተኞች ጋር የሚሰሩ ተቋማትን በመጋበዝ ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ ዕድሉን ማመቻቸት እና ዘላቂ አጋርነትን መፍጠር
  • አካል ጉዳተኞች በጤና አገል

አካል ጉዳተኞችን አካታች የሆነ የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎትን ለመፍጠርና ለማስቀጠል ዘርፈ ብዙ ጥረትና ርብርብ ያስፈልጋል። ሳናውቃቸው አብረውን ከኖሩ አድልዎን ከሚደግፉ አመለካከቶችን መለየት እና መቀየር የእያንዳንዱ ግለሰብ ሃላፊነትሲሆን ከመንግስት፣ ከጤና ተቋማት፣ የሀይማኖትና የህብረተሰብ መሪዎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የአካል ጉዳተኞች ማህበርም ጭምር ንቁ ተሳትፎ እና ትብብር ያስፈልጋል።

 

ዋቢ/ማጣቀሻ

  • Learning from a disability-inclusive SRHR programme https://sharenetinternational.org/resources/learning-from-a-disability-inclusive-srhr-programme-wish2action/
  • Sexual and Reproductive Health: Layers of (in)Access https://link.springer.com/chapter/10.1007/978-3-03055567-2_8
  • Access to SRHR Information and Services: Perspectives of women and girls with disabilities in Uganda and Bangladesh https://share-netinternational.org/resources/access-to-srhr-information-and-servicesperspectives-of-women-and-girls-with-disabilities-in-uganda-and-bangladesh/
  • Disability inclusion in reproductive health programs – Ipas https://www.ipas.org/wpcontent/uploads/2021/06/VCATDSE21-Disability-inclusion-in-reproductive-health-programs.pdf